የኮንዶም ማስታወቂያ – ከአደፍርስ ተሰማ
አሁን ዓለምን የሚያውከው ቅስም ሰባሪው ህዋስ (ኤድስ)ና የኤድስ በሽታ ብቅ ከማለቱ በፊት በወሲብ ግንኙነት ሳቢያ የሚመጡ አእላፍ በሽታዎች ነበሩ ዛሬም አሉ ወደፊትም ይኖራሉ፤ እየበዙም ነው። የዛሬ የህክምና ጠበብቶችም ኮንዶምን በመጠቀም (AIDS and STD) እንዳይዛመት መቀነስ ይቻላል ይሉናል። ከሆነ መልካም ነው።
አንድ በዓለም ዙሪያ የኮንዶም ሽያጭን የሚከታተል ድርጅት ከስድስት እስከ ዘጠኝ ቢሊዮን ኮንዶሞች በአመት ይሽጣሉ ይለናል። በዋሻ ላይ የተሳሉ ምልክቶች እንደሚያመለክቱትም የሰው ልጅ ኮንዶም መሳይ ነገር እየሰካ መጠቀም የጀመረው ገና ዋሻ ውስጥ እያለ ነው። እነዚህም ኮንዶም መሳይ ነገሮች የተሰሩት ዘይት ከተቀባ የሃር ክር ውትብታብ፤ ጠንከር ካሉ ቅጠሎችና ለስለስ ያሉ የአናብስት ቆዳዎችን ሲጠቀሙ እንደነበር ጥለው ያለፉት የህይወት አሻራ ይመስክራል። ለምን ኮንዶም መሳይ ነገር ለመገልገል እንደመረጡ ግን እስካሁን አጥጋቢ መልስ አልተገኘም።
ለነገሩ እኔ ላጫውታቹህ የምከጅለው ጉዳይ ስለ ኮንዶም የግዙኝ ማስታወቂያ በመሆኑ ወደዛው ልመለስ። መቸውንም ቢሆን አለማችን ሰለጠንኩ እንጂ ደነቆርኩ ብላ አታውቅም። ከእኛ በሞት የቀደሙንን ሁሉ ኋላቀርና ጎጂ ባህል ነበራቸው እያለን እኛኑ ማቆለጳጰስ እናውቅበታለን። አስተውሎ ነገርን ለተመራመረ እኛ ከፍ ብለን የምንታየው በእነርሱ ትክሻ ስለቆምን በቻ ነው። በየብስና በባህር ፈጥነን መሽከርከራችንም ብቻውን የስልጣኔ ምልክት አይሆንም። እነርሱም በፈረስ፤ በበቅሎና በአህያ በመንቀሳቀስ እንዳመቻቸው ተፈጥሮን ለመግታት ታግለዋል። ባጭሩ ከእኛ በፊት የተሞከረውን ነው እኛ መልኩንና ሰሙን ለዋውጠን ብረታ ብረቱን በብረት፤ ፕላስቲኩን በፕላስቲክ አሽገን ለገብያ የምናበቃው። አቤት ጉድ ከዕቃው መጠቅለያው ሲያምር። እዚህ ላይ ያኔ የፕላስቲክ ቴክኖሎጂ ነበር አላልኩም የኮንዶሙ አጠቃቀምና አወቃቀር ግን ያው ነው።
ኮንዶም ዊዝ ፍሌበር (Condom with flavor) ይላል ማስታወቂያው። የሩቅ ዘመድ አይኑ እንደገባ ሰው አፍጥጨ ፊደላቱንና ከማስታወቂያው ጎን የቆመችውን አሻሻጭ ለጋ ልጅ በከፍታ ስፍራ የተለጠፈውን የግዙኝ የማስታወቂያ ወረቀት በአእምሮዬ ሰዕሉን ከተጻፈው ሃሳብ ጋር እያመሳከርኩ እመለከተው ጀመር። ትንሽ ግራ ገባኝ። በቡና፤ናና (Mint) በቀረፋ (Cinnamon) የተለወሰ ኮንዶም ይላል። እኔም አይኔን ማመን አቅቶኝ እንዴ እንዴ ቀረፋ እሱማ ሻሂ ውስጥ የሚገባው አይደለም እንዴ? ኮንዶምና ቀረፋን ምን አገናኘው። ደግሞስ ቡናን ከፕላስቲክ ጋር ማን አቆራኘው እያልኩ አሰላስል ገባሁ። በተለይም የቡና ስም ሲጠራ ከአቦል እስከበርካ ከቁርስ ጋር የምንጠጣው ቡናና ባህላችን ትዝ አለኝ።
ወሊድንና በሽታን ተከላክሎ ወሲባዊ ፍላጎትን ለማርካት የሰው ልጅ የማይሞክረው ብልሃት የለም። ዛሬ ክራራይሶ (የምጽዕት የልመና ጽሎት) የሚያስብለን ወንድና ወንድ ሴትና ሴት የሚላተሙበት ፍትወት በፊትም የነበረ ወደፊትም የሚኖር የሰው ልጅ እድምታ ነው። ካለፈው የሚለየው ተግባሩ ከምኝታ ቤት ወጥቶ ይፋ መሆኑና እኔን ምሰሉ መባላችን ብቻ ነው። የሰው ልጅም በወሲብ ሳቢያ የተለያዪ ዜይቤዎችን እየተጠቀመ ራሱን ለማርካት በከጀለ ቁጥር ይባሱን ራሱን ውኃ ወደሌለበት በረሃ እየላከ ከመርካት ይልቅ ጥማቱ እየጨመረ እንደሚሄድ የወሲብ ሳይንስን ሙያ በለው የያዙት ጠበብቶች ይነግሩናል። አሁን ማጣፈጫ የታከለበት የኮንዶም ገቢያም የሚያረካው የኮንዶሙን ነጋዴ እንጂ ሽማቹን ተጠቃሚ አይደለም። እንዲያውም አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው በዓለም ላይ ከሚመረቱት የኮንዶም አይነቶች በጣፋጭ ነገር የተለወሱት በተግባር ላይ እያሉ የመቀደድ እድላቸው ሃምሳ በመቶ ነው ይለናል። ለምን ሲባል በላያቸው ላይ የተለቀለቀው ማጣፈጫ ነገር ከፕላስቲኩ ጋር አልጣጣም በማለት መሽፈኛውን ያመነምነዋል እና ነው። በዚህም የተነሳ በግዳጅ ላይ እያለ ኮንዶሙ የማፍሰስና ጭራሹኑ የመቀደድ እድሉ ላቅ ያለ ነው። ማጣፈጫ ነገር ያለተቀቡትም ኮንዶሞች እንደ ፍቅረኞቹ የአጠቃቀም እንዝህላልነት ከመከላከል ወደ ተጠቂነት ሊያሽጋግሩ ይችላሉ። በተለይም ደግሞ አደንዛዥ ዕጽና አልኮል እየመራቸው ወሲብ የሚያረጉ በዓለም ዙሪያ የተናኘውን ወሲባዊ አመጣሽ በሽታ ለመሸመት ያላቸው እድል – ፈንታ ከቶምቦላ (ሎተሪ) ትኬት የላቀ ነው።
አንድ ነገር ላክልበት ካነበብኩት – አንዲት ከአርጀንቲናዊ አባትና ከጣሊያን እናት የተዳቀለች ውብ ቆንጆን ስፔን (ማድረድ) የሚኖር የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋች አንድ የምሽት ጮቤ ረገጣ ስፍራ ያያትና ለፍቅር (ለወሲብ) ይጠይቃታል። እስዋም በበራፏ በዙ ሰው እንዳለፈ የተረዳችው አይ አይሆንም በማለት ሶስት ወር ደጅ ታስጠናዋለች። በሰውነቷ ለጋነት እና በውጭ ቁንጅናዋ የነሆለለው የቀድሞው ኳስ አንከባላይ ያገኛትና ይደሰታል። ጊዜአዊ ፈንጠዝያ! ስነባብቶም ይታመማል። ጉንፋን ነገር መስሎት ወደ ህክምናም መሄድ ይዘገያል። ያው ቀኑ ደርሶ ምርመራው ሲደረግለት የቫይረሱ ተሽካሚ መሆኑ ይነገረዋል። ለካ እሱም በመካከሉ ሌሎችን ሲቀባ ቀይቶ ከስ ተመስርቶበትና ለካፊውን በሽታም ማዛመቱ ተደርሶበት ዛሬ በእስር ይገኛል። በተመሳሳይ ሁኔታ ጀርመናዊዋን ክልስ የዓለም አጫዋች (ዘፋኝ) አፍቅሮ ተለከፍኩ ያለው ጀርመናዊ ክስና ፍርድ በጉግል ፈላልጎ ማንበብና ቪዲውን መመልከት ይቻላል። በዙ ትምህርት ይሰጣልና!
አለማችን ገሰገሰች ጨረቃን ዳበሰን ከድምፅ በፈጠነ መንገድ ከነፍን የኮምፒውተር ቅመራ ባመጣው ስሌት ቁጥርን ከቁጥር ጋር በማጋጨት አያሌ ነገርን ሰራን። ይሄው እኔም ይህን አማርኛ የምጽፈው በድብቅ ፕሮግራም በተደረጉ ቁጥሮች ኪቦርድን እየነካካሁ ነው። አንድ ነገር ግን የሰው ልጅ መቀየር አልቻለም። ያም የራሱን ባህሪ ነው። ከገዳይው ህዋስ ማምለጥ የሚቻለው የግል ባህሪን በመለውጥ ብቻ ነው። ያለዛ እንኳን በኮንዶም በብልኮም (ብርድልብስ) ሽፍነህም ፍትወት በትሰራ ከሃሳብና ብሎም ከመለከፍ አያድንህም። በኮንዶም መተማመን ብቻውን ከመከራ አይጠብቅም። ፍቅሩም (ወሲባዊው ግንኙነት)ም አብሲት እንደሌለው እንጅራ የሚኮመጥጥ ነው የሚሆነው። እርካታ የለውም። እንዲያው እንደ ሃገራችን የቆሎ ተማሪ አትቁም መባልን ጠልተን ሰፈር ለሰፈር በናዳርስም እርካታ አይገኝም። በህወታችን መቀለድን አቁመን እማኝ ያለበትና ዘላቂ የሆነ ፍቅረኛ እንፈልግ። የኮንዶም ጠቀሜታና ልክስክስነት ይቅርብን።