የ”በቃ!” በራሪ ወረቀቶች አዲስ አበባን እያጥለቀለቋት ነው

“በቃ” በሚል መሪ ቃል በፌስ ቡክ ድረ ገጽ ላይ ግንቦት 20 2003 ዓ.ም በኢትዮጵያ ህዝባዊ አመጽ ለማካሄድ እንቅስቃሴ መደረግ ከጀመረ ወዲህ በርካታ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች እየተደረገ መሆኑ ተስተውሏል፡፡ ከሚያዝያ 1 2003 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባና አካባቢዋ “የኢትዮጵያ ወጣቶች ንቅናቄ ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ” በተባለ ቡድን ስም እየተበተነ ያለውም በራሪ ወረቀት የእንቅስቃሴው አንዱ አካል መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የድረገጻችን ሪፖርተር ተዘዋውሮ እንደተመለከተው በራሪ ወረቀቱ በአንድ ቀን ውስጥ (እሁድ ሚያዝያ 1 2003ዓ.ም) ብቻ ድፍን አዲስ አበባንና አካባቢዋን ማጥለቅለቅ መቻሉን ለማረጋገጥ ችሏል፡፡ በጉዳዩላይ አስተያየት እንዲሰጡን ያነጋገርናቸውና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንዳንድ ወጣቶች እንቅስቃሴው ጠንካራ መዋቅር እየፈጠረ ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የተበተነው በራሪ ወረቀት ህብረተሰቡ የግንቦቱን ህዝባዊ አመጽ እንዲደግፍ የሚቀሰቅስና መንግስት በአስቸኳይ ሊመልሳቸው ይገባል ያላቸውን ጥያቄዎች የያዘ ነው፡፡ በዚሁ በራሪ ወረቀት ላይ ለህዝባዊ አመጹ ጥሪ የተላለፈላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ወጣቶች፣የመከላከያና የፖሊስ ሰራዊት አባላት፣ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ሲሆኑ በተለይ ለወጣቶች፣ ለመከላከያና ለፖሊስ ሰራዊት አባለት ጠንከር ያለ መልዕክት ሰፍሯል፡፡ ወጣቶችን “እኛ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ዛሬ የግል ጥቅማችን የምናሳድድበት ጊዜ ሳይሆን ለእውነተኛው የዴሞክራሲዊ ለውጥ በጋራ የምንነሳበት ትውልዳዊ የሀላፊነት ጊዜ ነው፡፡” በማለት በህዝባዊ አመጹ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ያሳሰበ ሲሆን “በማንኛውም የዜጎች ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ መንግስት ላይ ሕዝቡ ተቃውሞ ቢያነሳ እንደ ሀገር ጠባቂነችሁ ወገናችሁንና ሀገራችሁን ከአደጋ በመከላከል የዜግነት ሀላፊነታችሁን እንድትወጡ፡፡ ስለዚህም ካለፈ ስህተታችሁ ትምህርት በመውሰድ እህትና ወንድሞቻችሁ ላይ ቃታ ባለመሳብና ቆመጥ ባለመሰንዘር የህዝብ ልጆች መሆናችሁን በተግባር አረጋግጡ፡፡ ከግብፅ መከላከያ ሠራዊት ተማሩ!!!!” የሚል ምክር አዘል መልእክትም ለመከላከያና ለፖሊስ ሰራዊት አባላት የሚያስተላልፍ ሀሳብ የያዘነው፡፡

በበራሪ ወረቀቱ ላይ መንግስት በፍጥነት ሊያስተካክላቸው የገባል ካላቸው ነገሮች መሀከል “በምግብ ሸቀጦች ላይ የተጣለው ቫት በሙሉ ይነሳ! የነዳጅ ዋጋ ድጎማ በአስቸኳይ ይጀመር ! ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት፣ የመናገር፣ የመጻፍና የፕሬስ ነፃነት ያለገደብ ይከበር! የግሉን ፕሬስ ማዋከብ ይቁም! የህትመት ዋጋ ጭማሪወው ይነሳ! በቅርቡ አመፅ ታነሳላችሁ በሚል በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የታሰሩና ቀደም ሲል የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ ይፈቱ!ለህዝብ በሚጠቅም መልኩ ሕገ-መንግስታዊ ማሻሻያ ይደረግ !” የሚሉ ጥያቄዎች የሚገኙበት ሲሆን ለአቶ መለስም “ይህንን ጥያቄ ባነሱ ወጣቶች ላይ በሚወስዱት ማንኛውም እርምጃ ጥያቄዎቹ ፈጣን ግልፅና አጥጋቢ መልስ እስካላገኙ ድረስ ህዝባዊ ማእበሉ እነደማይቀር አውቀው አስከ ግንቦት 20 ድረስ መልስ እንዲሰጡን እናሳስባለን!” የሚል ማስጠንቀቂያ በበራሪ ወረቀቱ ላይ ሰፍሯል፡፡ (የበራሪ ወረቀቱ ሙሉ ጽኁፍ ከዚህ በታች ያለው ነው፡፡)

የነፃነትና የለውጥ ጥሪ ለኢትዮጵያ ሕዝብ

ለኢትዮጵያ ወጣቶች በሙሉ፡-

እኛ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ዛሬ የግል ጥቅማችን የምናሳድድበት ጊዜ ሳይሆን ለእውነተኛው የዴሞክራሲዊ ለውጥ በጋራ የምንነሳበት ትውልዳዊ የሀላፊነት ጊዜ ነው፡፡

ወጣቶች ሆይ! ከራሳችን ጥቅም አሻግረን የወደፊቱን እንመልከት ፤ ነፃ፣ ዘመናዊና ከዘረኝነት የፀዳ ኢትዮጵያዊ አጀንዳ እናንግብ፡፡

በመቻቻልና በይቅርታ እንመን፣ ለምናምንበት አላማ በፅናት እንቁም፡፡

በተቃውሞ ወቅት ገዢዎቻችንን በማንኛውም ኀይል ብንበለጥ እንኳ ጉልበት ባለመጠቀም ሠላማዊ ታጋይነታችንን በተግባር እናረጋግጥ!!!

ያለነፃነት የተገኘ ሀብትም ሆነ ልማት ባርነት እንደሆነ ለገዢዎቻችን በግልፅ ቋንቋ እንንገራቸው ፡፡ ስለሆነም ለዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ በአንድነት ተነሳ !!

ለኢትዮጵያ የመከላከያ ፖሊስና የደህንነት ኃይል በሙሉ፡-

በማንኛውም የዜጎች ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ መንግስት ላይ ሕዝቡ ተቃውሞ ቢያነሳ እንደ ሀገር ጠባቂነችሁ ወገናችሁንና ሀገራችሁን ከአደጋ በመከላከል የዜግነት ሀላፊነታችሁን እንድትወጡ፡፡ ስለዚህም ካለፈ ስህተታችሁ ትምህርት በመውሰድ እህትና ወንድሞቻችሁ ላይ ቃታ ባለመሳብና ቆመጥ ባለመሰንዘር የህዝብ ልጆች መሆናችሁን በተግባር አረጋግጡ፡፡ ከግብፅ መከላከያ ሠራዊት ተማሩ!!!!

ለኢትዮጵያ አርሶአደሮችና አርብቶ አደሮች በሙሉ፡-

የመሬትህ ሙሉ ባለቤት እንዳትሆን በማድረግ የስርዓታቸው ጭሰኛ ከማድረጋቸውም ባሻገር በማዳበሪያ እዳና በተለያዩ ማጥመጃ መንገዶች የአገዛዙ እስረኛ አድርገውህ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም ለሀገራዊና ዘላቂ ዴሞክራሲያዊለውጥ ከከተማ ነዋሪ ወገንህ ጋር በጋራ ተነሣ!!!!!!

የኢትዮጵያ ወጣቶች ጥያቄ ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ!

ለጠቅላይ ሚኒስተር አቶ መለስ ዜናዊ ግልባጭ ለኢትዮጵያ ህዝብ

በምግብ ሸቀጦች ላይ የተጣለው ቫት በሙሉ ይነሳ!

የነዳጅ ዋጋ ድጎማ በአስቸኳይ ይጀመር !

ሙሰኞች በሙሉ ለፍርድ ይቅረቡ!

ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት፣ የመናገር፣ የመጻፍና የፕሬስ ነፃነት ያለገደብ ይከበር!

የግሉን ፕሬስ ማዋከብ ይቁም!

የህትመት ዋጋ ጭማሪወው ይነሳ!

በቅርቡ አመፅ ታነሳላችሁ በሚል በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የታሰሩና ቀደም ሲል የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ ይፈቱ!ለህዝብ በሚጠቅም መልኩ ሕገ-መንግስታዊ ማሻሻያ ይደረግ !!

* ማሳሰቢያ ለአቶ መለስ፡- ይህንን ጥያቄ ባነሱ ወጣቶች ላይ በሚወስዱት ማንኛውም እርምጃ ጥያቄዎቹ ፈጣን ግልፅና አጥጋቢ መልስ እስካላገኙ ድረስ ህዝባዊ ማእበሉ እነደማይቀር አውቀው አስከ ግንቦት 20 ድረስ መልስ እንዲሰጡን እናሳስባለን!!!!!!!
* አደባባይ ወጥቶ መንግስትን በሰላማዊ መንገድ መቃወም ወንጀል ሳይሆን የዜጎች ህገ-መንግስታዊ መብት ነው!!!
* አምባገነንነትና ዘረኝነትን በሰላማዊ ትግል እንለውጣለን!!!!

ልማት ያለነፃነት ባርነት ነው!!!!!

ዓላማችን

* ነፃና ፍትኃዊ ምርጫ በሀገራችን ኢትዮጵያ እንዲኖር ማድረግ፣
* ሀገራዊና ብሔራዊ እርቅ እንዲፈጠር መታገል፣
* ነፃ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲፈጠሩ መታገል፣
* ሕገ-መንግስቱ ለሀገርና ለሕዝብ በሚጠቅም መልኩ ማሻሻያ እንዲደረግ መታገል፣
* ፍትሕ፣ ዴሞክራሲና ነፃነት በግለሰቦች የሚሰጥ ወይም የሚቀማ ሳይሆን ሕዝቦች በህገ- መንግስቱ እንዲረጋገጥላቸው መታገል፣
* እየተሸራረፈ ያለውን የሀገሪቱን አንድነትና ሉአላዊነት በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲጠበቅ መታገል፣
* በመጨረሻም ባነሳናቸው ጉዳዮች በሙሉ ሊተባበር ከሚችል ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆናችንን እናሳውቃለን፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!

የኢትዮጵያ ወጣቶች ንቅናቄ ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ