የምርጫ ቦርድ ጥናት ለገዢው ፓርቲ የወገነ መሆኑ ተነገረ

ምርጫ ቦርድ የ2002 ዓ.ም ምርጫን በተመለከተ ያዘጋጀውን የዳሰሳ ረቂቂ ሰነድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደማይቀበሉት አስታወቁ፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ይህንን ያስታወቁት ባለፈው ቅዳሜ በምርጫ ቦርድ አዳራሽ በሰነዱ ላይ ከምርጫ ቦርድ ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡

ምርጫ ቦርድ በጠራው በዚሁ ስብሰባ ላይ የፓርቲዎቹ ተወካዮችን ለአራት ቡድን ከፍሎ እንዲወያዩና የደረሱበትን የጋራ ውሳኔ የተመለከተ ገለፃ እንዲያደርጉ አድርጓል፡፡ በዚህ ወቅት ከኢህአዴግ ተወካዮች የሀሳብ ልዩነት በቀር ሌሎች ፓርቲዎች በሙሉ በአንድ ድምፅ የምርጫ ቦርድን የዳሰሳ ጥናት “የአንድ ወገን የምርጫ ሪፖርት” ሲሉ አጣጥለውታል፡፡

ፓርቲዎቹ ይህንን እንዲሉ ያስደፈራቸውን ምክንያት በተመለከተ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የምርጫ ጉዳይ ሀላፊ አቶ ብሩ ብርመጂ “ምርጫ ቦርድ በምርጫው ወቅት የነበሩ ችግሮችን በተመለከተ ከተቃዋሚ ፓርቲዎቹ የተሰጠውን አስተያየት በረቂቅ ሰነዱ ውስጥ ከሞላ ጎደል ለማካተት ሞክሯል፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው? የመጀመሪያ ደረጃ የመረጃ ምንጭ የሆነውን አካላት አስተያየት በሁለተኛ ደረጃ የመረጃ ምንጮች እንዲስተባበል አድርጓል፡፡ ይሄ ደግሞ ልክ ያልሆነ አካሄድ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

የፓርቲዎቹን አስተያት ያስተባበሉትን የቦርዱ የመረጃ ምንጮች ማንነት ለማወቅ ላቀረብንላቸው ጥያቄም አቶ ብሩ “ሰባት ናቸው፡፡ የህዝብ ታዛቢዎች፣ የሲቪል ማህበራት፣ የምርጫ አስፈፃሚዎች፣ መራጮች፣ የአስተዳደር አካላት፣ የፍትህ አካላትና የመገናኛ ብዙሀን ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ እንደየ አስተዳደር አካላት ያሉት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የኢህአዴግ አጋር በመሆን ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ አካላት ናቸው፡፡ መራጮች ተብለው አስተያየታቸው የተካተተው ሰዎች ላይም ጥያቄ አለን፡፡ ምክንያቱም የተወሰደው ናሙና representative ለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡ ከቦርዱ የተለመደ ገለልተኛ ያልሆነ አካሄድ አንፃር ሲታይ ደግሞ አሰራሩን ለመጠርጠር እንገደዳለን፡፡

አስተያየት ሰጡ የተባሉት ሰዎችስ ምን ያህል ከስነልቦና ጫና ነፃ ሆነው ለቃለመጠይቁ መልስ ሰጡ? የሚለው ጥያቄም አነጋጋሪ ነው” በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡ በመጨረሻ ለአቶ ብሩ ሰነዱ ምንአይነት ማስተካከያዎች ቢደረጉበት እንደሚቀበሉት ጥያቄ ያቀረብንላቸው ሲሆን “በስብሰባው ላይ እንደነገርናቸው የምርጫው ዋነኛ ባለድርሻ አካላት የሆነው በምርጫ ተወዳዳሪ የነበርን ፓርቲዎችና ህዝቡ ነው፡፡ በመሆኑም እኛ ምርጫው ነፃና ፍትሀዊ እንዳልነበረ ገልፀናል፡፡ ከኢህአዴግ ጋር አብረው ምርጫ ላይ ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ አካላትን ገለልተኛ አካላት በማስመሰል የኛን አስተያየቶች ውድቅ ለማድረግ ምርጫ ቦርድ የሄደበትን አካሄድ ማስተካከል ይኖርበታል፡፡

ይህንን ካደረገ ወደፊት ተስተካከሎ የሚቀርብልንን ሰነድ የማንቀበልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ይህ ካልሆነና እውነተኛ ማስተካከያ ካልተደረገበት ግን የምርጫውን ኢፍትሀዊነት በአይናችን ያየን አካላት በቦታው ባልነበሩ ወይም ደግሞ ስለጉዳዩ የተዛባ አመለካከት ባላቸው አካላት እውነታችን ተምታቶ የቀረበበትን ሰነድ የምንቀበልበት ምክንያት አይኖርም” የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡

በምርጫ ቦርድ አዳራሽ በተካሄደው በዚህ ስብሰባ ምርጫ ቦርድ ከኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጋዜጠኞች በስተቀር ሌሎች ጋዜጠኞች እንዳይገቡ መከልከሉም የግል ጋዜጠኞችን ክፉኛ እንዳሳዘነ ታውቋል፡፡