አግአዚ ሰራዊት እና የአግአዚ ልጅ

ሲሣይ አጌና

PDF

መጋቢት20/2003 ምሽት ኮምፒውተሬን ስበረብር የታጋይ ዘርዑ ገሰሰ//አግአዚ ልጅ ትብለፅ ብቅ አለች፤ፎቶግራፉዋ ማለቴ ነው፤አግአዚን ሳስታውስ ደግሞ የሰኔ 1997ቱ እና የጥቅምት/ሕዳር 1998ቱ አረመኔያዊ ጭፍጨፋ መጣብኝ፤…የአግአዚ ክፍለጦር አባል የነበረውና ቃሊቲ ከእኛ ጋር አንድ ቤት ታስሮ የነበረው ሞላም ከፊቴ ድቅን አለ፤የጉዋደኛው ኪሮስ መገደልና የርሱ የእስር ሁኔታ እንዲሁም የአግአዚ ሰራዊት የተደራጀ ግድያም ትዝ አለኝ፡፡ትብለፅ በግድያው ሰሞን ለ ኢትኦጵ ጋዜጣ የሰጠችውን ቃለምልልስ ከ 5 ዓመት በኋላ ደግሜ ሳነብ ለዚህ አረመኔያዊ ድርጊት የሕወሓት ደጋፊዎች ጥብቅና ይበልጥ አናደደኝ፤የሕወሓት ደጋፊዎች ሥርዓቱን በፖሊሲው ቢደግፉት አመለካከት ነውና ዕዳው የሃሳብ ትግል ነው፣ለዚህ አረመኔያዊ ድርጊት አረመኔዎቹ ሰበብ ፍለጋ መዳከራቸው የሚጠበቅ ቢሆንም፣ደጋፊዎቹ ቢያንስ በዝምታ ፣ቢቻል በማውገዝ ሰው መሆናቸውን ማስመስከር ይጠበቅባቸው ነበር፤እየሆነ ያለው ግን ገዳይን ማውገዝ ሳይሆን ሟችን መውቀስ መለያቸው ሆኗል፤.አንድ አብነት ላንሳ፡፡

ሚሊዮኖች የሚያደምጡት የቮይስ ኦፍ አሜሪካ አድማጮች #በለው ነኝ ከካናዳ $እያሉ ዘወትር ለሕወሓት ጥብቅና የሚቆሙትን ሰው ያስታውሱዋቸዋል እና ለተነሳሁበት ጉዳይ ጥሩ ምሳሌ ናቸው፤የግብፅ ወታደሮች ጨዋነትና ገለልተኛነት እየተነሳ ከኢትዮጵያው የ1997 ጭፍጨፋ ጋር እየተወዳደረ መቅረቡ ያናደዳቸው እኚህ ሰው የሰጡት አስተያየት የአግአዚን ጦር ጀግንነት የሚያወሳና ቅንጀትን የሚከስ፣አደባባይ የወጣውን ሕዝብ የሚወቅስ ነበር፤የግብጽ ሕዝብ ሰላማዊ ስለመሆኑም ነግረውናል፡፡

ቅንጀት ሰልፍ ጠርቷል፣አልጠራም የሚለውን ለግዜው እሱን እንተወው፤የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ከግብጽ ሕዝብ በላይ ሰላማዊ መሆኑን የሚያዚያ 30/1997ን ሰልፍ ላየ ወይንም ለሰማ ሌላ ማረጋገጫ አያስፈልግም፤የሰኔ አንዱ ግድያ እንዴት እንደተቀነባበረ ታሪክና ምርመራ ያወጣዋል፤ከጥቅምቱ 22 ግድያ 1 ቀን በፊት የማዕከላዊ ምርመራ እስር ቤትን ባዶ በማድረግ የተደረገው ዝግጅትና ግጭቱ የተፈጠረበት ሁኔታ፣ሌላው ቀርቶ ፖሊሶቹ በማን እንደተገደሉ ኢትዮጵያ በሕግ መመራት ስትጀምር ይደረስበታል፤ሰልፍ የወጣው ዜጋ ፀረ ትግሬ እንደሆነ ተደርጎ እየተለፈፈ ብዙ ቀፋፊና ሃላፊነት የጎደላቸው ንግግሮች ከሕወሐት መሪዎች አንደበትም አድምጠናል፤ እነርሱና ደጋፊዎቻቸው ዘመን መሻገር አቅቷቸው ጎሳ ኩሬ ውስጥ ሲንደፋደፉ አዲሱ ትውልድ ሕብረብሔራዊነትንም ተሻግሮ ዓለማቀፋዊነትን እየዘመረ፣የዕውቀትን ባህር እየበረበረ በሉሲ ዘመን ሰዎች እያፈረ ይገኛል፡፡

የሚያዚያ 30ውን ሰልፍ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የእለቱ ዕለት የተመለከቱ እንደሚያስታውሱት ጓደኞቹ ተሸክመውት መፈክር ሲያሰማ እና ሼህ ሞሃመድ አላሙዲንን ሲያወግዝ የሚታየው ክብሮም ዮሃንስ አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገ፣እናቱም አባቱም የትግራይ ተወላጆች ናቸው፤እንደሌላው ሁሉ በመንግስት ግልበጣ እንዳያስሩት እድሜው ስላልደረሰ ከወራት በኋላ አደገኛ ቦዘኔ ብለው ሸዋ ሮቢት እስር ቤት በመስደድና ከትምህርቱ በማፈናቀል በቀለኛነታቸውን አሳይተዋል፤..ክብሮምን በዚያኑ ሰሞን ፈልገን አግኝተን በጋዜጣችን ላይ ቃለ ምልልስ ባደረግንለት ወቀት #አንዳንድ እናቶች ዘራችንን ሰደብክ ብለው ቅር ብሎአቸዋል፤ ሌላው ግን አድንቆኛል $ ነበር ያለው፡፡.እናቶቹስ ..ምን ያድርጉ በቀበሌ ካድሬ እየተጠቀጠቁ፤…ለመሆኑ አላሙዲን የሚባል ዘር በኢትዮጵያ አለ እንዴ;በአለምስ ላይ ቢሆን፤….

በዚሁ በምርጫ 97 ሰሞን አባት በኦነግነት ተጠርጥረው ቃሊቲ፣ልጅ በቅንጅትነት ታፍሶ ዝዋይ የተወሰደበትን ሁኔታ እዚህ ላይ ማንሳቱ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ቢጀመር የዘር ፍጅት ይፈጠራል በሚል ለሚያስፈራሩ እና በቅንነት ለሚሰጉ የራሱ መልዕክት አለው ብዬ አምናለሁ፤አውሮፕላን አስነስተው ሊጨፈጭፉን ይችላሉ በሚል ለሚሰጉ ወገኖቼ በተወሰነ ደረጃ ሥጋታቸውን የምጋራ ቢሆንም፣እንኩዋን በጄት ደብድበው ሽጉጥም ተኩሰው መሸሻ ስለማይኖራቸው ማሰብ እንደሚጀምሩ ይታመናል፡፡

አውሮፕላን አስነስቶ እንዲደበድብ ሲጠየቅ ምላሽ የሰጠ አብራሪ በትንሹ በራሱ ላይ የእድሜ ልክ እስራት መፍረድ በመሆኑ፣በራሱ ላይ ሞትን የሚጋብዝ ጤነኛ አብራሪ ይኖራል ተብሎ አይታመንም፤ዘረኝነት ከጤና የሚያወጣ በመሆኑ በጥላቻ ምላሽ የሚሰጥ አብራሪ አይኖርም ብሎ መደምደም ያስቸግራል፤…ለእንደዚህ ዓይነቱ ማሳሰብ የሚያስፈልገው አዲስ አበባ የ 170 ሺ የትግራይ ተወላጆች መኖሪያ ጭምር መሆኑዋን ነው፡፡#ልማታዊው መንግስታችን$ መቼም ብሄር ብሄረሰብ እየለየ የሚመታ ቦንብ እንዳልፈበረከ ይታመናል፡፡.እነ አቶ መለስ ወንበራቸው ጤና ይሁን እንጂ ማንም ቢያልቅ ግድ የሚላቸው ዕለቂቱ የሚያስከትለው ተጠያቂነት እንጂ ሰብዓዊነት እንዳልሆነ 20 ዓመት ሙሉ በደንብ ተናበናል፡፡…ይልቅ እንደ አቶ በለው ያሉት የሚሰጡት ጭፍን ድጋፍ፣የሕወሓት መሪዎች በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ የሚከተሉት ፍጹም ሚዛኑን የሳተ ዘረኝነትና አድሎዊነት የሕዝቡን ትዕግስት ከመጠን በላይ እየተፈታተነ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ማስገንዘቡ አይከፋም፡፡

መነሻዬ በአረመኔነቱ ሀገር አቀፍ ዕውቅናን ስለተጎናጸፈው አግአዚ ክፍለጦር የአግአዚ ልጅ በወቅቱ የሰጠችንን ቃለምልልስ በማቅረብ ጭፍን ደጋፊዎች ህሊናቸውን እንዲመረምሩ ለማገዝ ቢሆንም፣ብዙ ዝርዘዝር ውስጥ ገባሁ፤(የነሞላን ጉዳይ በሌላ ግዜ አመለስበታለሁ) እዚህ ላይ ይብቃኝና የ ኢትኦጵ ጋዜጣ ባልደረባ የነበረውና አሁን በሕንድ ሀገር የሚገኘው አርኣያ ተስፋማርያም ትብለጽ ዘሩን (የአጋዚን ልጅ) በማነጋገር አጠናቅሮት የነበረውን ዘገባ እንድትመለከቱት እጋብዛለሁ፡፡ እዚህ ላይ ይጫኑ