በሰሜን ሸዋ አንድ አርሶ አደር 4 ፖሊሶችን ገድሎ ሞተ
በሰሜን ሸዋ አርጡማ ፉርሲ ወረዳ በተለምዶ ፍል ውሃ ተብሎ በሚጠራዉ አካባቢ በጥር ወር መጀመሪያ የተጀመረው የአርሶ አደሮች እና የክልሉ ባለስልጣናት አለመግባባት ተባብሶ እንደቀጠለ ነው፡፡ ያለመግባባቱ መነሾ በክልሉ ከብቶች ይውሉበት የነበረ ሰፊ መሬት ላይ የአካባቢው ነዋሪዎች ጤፍ መዝራታቸው መሆኑ ታውቋል፡፡ የተዘራዉ ጤፍ ለመሰብሰብ በደረሰበት ወቅት ተሸጦ አካባቢያቸውን ሊጠቅም በሚችል መልኩ በጥቅም ላይ የሚውልበትን ሁኔታ መንግስት ያመቻችላቸው ዘንድ ጥያቄያቸውን ያቀረቡት አርሶ አደሮች ያገኙት ምላሽ ፈፅሞ የጠበቁት አለመሆኑ ለግጭቱ ምክንያት ሆኗል፡፡ በአካባቢው የሚገኙ ምንጮቻችን ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት በወቅቱ የአካባቢው ባለስልጣናት ለነዋሪዎቹ ጥያቄ የሰጡት ምላሽ “ቦታው የከብቶች መዋያ እንደመሆኑ ጤፍ ሊዘራበት አይገባም፡፡ በመሆኑም ጤፉ በከቶች ሊበላ ይገባዋል” የሚል ነበር፡፡ ምንጮቻችን ጨምረው እንደገለጹት በዚህ መልስ ከተበሳጩት ነዋሪዎች አንዱ የሆነው አርሶአደር ሙሳ “ስንት ረሃብተኛ ባለበት አገር ጤፍ በከብት ሲበላ በዝምታ አላይም” የሚል አቋም ይዞ ማሳውን መጠበቅ ይጀምራል፡፡ ይህንን ድርጊቱን በማስገደድ ለማስቆም ሙከራ ሲያደርጉ ከነበሩ ፖሊሶች ጋር በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ በአርሶ አደሩ አራት ፖሊሶች ሲገደሉ አርሶ አደሩም ከፖሊሶቹ በተተኮሰበት ጥይት ሕይወቱ አልፏል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የአካባቢው ነዋሪዎች በቋጠሩት ቂም የተነሳ እንደተካሄደ በተነገረለት የጥቃት እርምጃ ምክትል ኢንስፔክተር ለገሰ ሰኜ ጥር 25 ቀን 2003 ዓ.ም ከሚሴ ከተማ ውስጥ በጥይት ተገሎ ተገኝቷል፡፡ ሁኔታው ያሳሰበው መንግስት ከዚህ ዕለት በኋላ ተከታታይ ስብሰባዎች በመጥራት አርሶ አደሮቹን ለማግባባት ቢሞክርም በስብሰባ ወቅቶች የአካባቢው ባለስልጣናት የሚሰነዝሯቸው ሀሳቦች ግጭቱን ከማብረድ ይልቅ የሚያባብሱ ሆነውበታል፡፡ ባለስልጣናቱ ጤፉን በከብቶቹ ያስበሉበትን ምክንያት በተመለከተ ከሰጡት ምላሾች ውስጥ በተለይ “ካለመንግስት ፈቃድ ምንም ነገር ማድረግ እንደማይቻል ለማሳየት የወሰድነው እርምጃ ነው” የሚለው ምላሽ አለመግባባቱን የበለጠ እንዳከረረው ለማወቅ ተችሏል፡፡ በከብቶች እንዲበላ የተደረገው ጤፍ ቢሸጥ ኖሮ 6,000,000.00 ብር ያወጣ እንደነበር ከአካባቢው ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡