አባይና የሰሞኑ ግርግር
ከመስፍን አማን
መቼም የአባይን መገደብ የሚቃወም ሃገሩን የሚወድ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም። ለሃገራችን መልካም እናስባለን የሚሉ አገር ወዳድ ሀይሎች፡ በጉዳዩ ላይ ያላቸው ተቆርቋሪነት ከወያኔ መሪዎች ቢበልጥ እንጂ የሚያንስ አይደለም። ሁላችንም ቀን ወጥቶ በጋራና በመግባባት ሃገራችን የሃብቷ ተጠቃሚ ሆና ከማየት የበለጠ ሌላ ትልቅ ምኞት የለንም። እንደውም ብቸኛው አብዩ ምኞታችን ያ ነው።
ከወደ ኢትዮጵያ ሰሞኑን የሚሰማው ወሬ ሙሉ ትኩረት አባይና የትልቁ ግድብ ግንባታ ብቻ ነው(የሚሊንየም/ህዳሴ ግድብ)። ወንዙ ብቻ ለምን ተብሎ ይመስላል ግድቡን የሚያሞካሹ ወደ ሶስት ዘፈኖች ከሰሞኑ ተለቀዋል። እረ እንዳውም ግድቡ ሲጠናቀቅ ሃገራችን ያሉባት ችግሮች እንደጉም ተነው እንደሚጠፉ መነገር ተጀምሮአል። እኔ ግን በሃገራችን ቅድሚያ መልስ ማግኝት ያለባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች እልባት ሳያገኙ ወደግድብ ግንባታው መሄድ ውጤቱ ሌላ ችግር መፈልፈል ነው የሚል አቋም ይዣለሁ። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በብዙ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተተብትባለች። እናም ለችግሮች መፍትሄ ሳንሰጥ ሌላ ነገር ማሰብ፣ ግመል ሰርቆ አጎንብሶ እንደሚባለው አይነት ነገር ይሆናል።
ነገሩ ተገልብጦ ሲታይ ወያኔ በድንገት ስለግድቡ ግንባታና ብሄራዊ ጥቅማችን መከበር ያዙኝ ልቀቁኝን ያበዛው ሌላ ማግኘት የፈለገው ጥቅም ስለመኖሩ ብዙ እንድንል ምክንያት ሆኖናል። በርግጥ የእውነት ከሆነ የግድብ ግንባታው ወሬ እስካሁን ለምን ዘገየ?፣ “ብልሁና አስተዋዩ” ጠቅላይ ሚኒስትራችን በትራንስፎርሜሽንና እድገት እቅዳቸው ውስጥ ለምን አላከተቱትም የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ተገቢና አስፈላጊም ነው። አስቡት ግድቡን ለመስራት 80 ቢሊዮን ብር ተመደቧል፣ የአምስት ዓመቱን የትራንስፎርሜሽንና እድገት አጠቃላይ እቅድ ለማሳካት አንድ ትሪሊዮን ብር በጀት ተይዞአል። በዚህ ስሌት ከሄድን ከአጠቃላይ እቅዱ አንድ አስረኛው ለዚህ ግድብ ወጪ መሸፈኛ ይውላል ማለት ነው።ይህ ከሆነ ደግሞ ሌሎች እቅዶችን ሳይጨምር ቢያንስ የግድብ ግንባታው በትራንስፎርሜሽን እቅዱ ውስጥ መኖር ነበረበት።
በአጋጣሚ የትራንስፎርሜሽን እቅዱን ሰነድ አግኝቼ ነጥብ በነጥብ መመልከቴን አስታውሳለሁ። ነገር ግን ስለ አዲሱ የሚሊንየም/ህዳሴ ግድብ የተገለጽ አንድም ነገር አላገኝሁም። እናም የግድብ ግንባታው ሃሳብ ከየት መጣ?፣ለምን በዚህ ወቅት ትልቅ የመነጋገሪያ ጉዳይ እንዲሆን ተፈለገ? የሚለው የዚህ ሃተታ መነሻና መድረሻ ይሆናል። ለአረዳድ እንዲመች በሚከተሉት ነገሮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ዳሰሳ ለማካሄድ ይሞከራል። አንደኛው የመለስ አገዛዝ የአባይን ውሃ ፖለቲካ (Hydro-politics) አጀንዳ በዚህ ወቅት ማካረር የፈለገው ለምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ሲሆን፣ ሁለተኛው ይሁን አባይ ይገንባ ቢባል እንኳን፡ ከዚህ ቀደም በሃገር ብሄራዊ ጥቅም ላይ ብዙ የከፋ ወንጅልን የፈጽመው መለስ ዜናዊና አገዛዙ፡ ይህንን አብይ ብሄራዊ ጉዳይ በተመለከተ የሚጫወቱት ሚና ላይ የሚነሳውን የተአማኒነት ጥያቄ የሚዳስስ ነው። አብረን እንቆይ።
አባይ፡ ኢትዮጵያና ግብጽ
ኢትዮጵያና ግብጽ አባይን ማዕከል አድርገው በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚያካሂዱት የጦፈ ፍትጊያ ከዘመን ዘመን ሲሸጋገር የመጣና ለታዛቢዎች እምብዛም እንግዳ ያልሆነ ጉዳይ ነው። እንዳውም ከመቶ ምናምን ዓመታት በፊት ግብጽ በተከታታይ ያደረገችውን የወረራ ሙከራ በዘመኑ በነበሩ ጀግኖች ተገቢው ምላሽ ተሰቶት ተመልሶአል። ከሰሞኑ ግብጽ በአባይ ጉዳይ ላይ ጦርነት አነሳለሁ ብትል ወየውላት በማለት አራት ኪሎ ከሚገኘው የመለስ ጽህፈት ቤት የሚሰማው ድንፋታ ግን ምን አዲስ ነገር ተገኝቶ ነው የሚያሰኝ ሆኖአል፡፡ ምክንያቱን ከዚህ ቀደም የዛቻ ቃላት የምንሰማው ከካየሮ ነበርና (እዚህ ጋር የአኑዋር ሳዳት ዛቻን ማስታወሱ ተገቢነት አለው)። በእርግጥ ግብጽ ሁልግዜ በ1929 እና በ1959 ዓም በተደረጉት የውሃ ስምምነቶች ካገኘችው የውሃ ድልድል ድርሻ አንዲት ጠብታ መቀነስ አይደለም፣ ቢቻላት ፍሰቱን መቶ በመቶ እንዲሆንላት ትፈልጋለች። የላይኞቹም ሃገራት ከላይ በተጠቀሰው ስምምነት መሰረት ወደ አንድ ወገን ያደላውን የውሃ ድልድል እንዲለወጥ ከመጠየቅ የቦዘኑበት ግዜ የለም። ይህ የላይኞቹና የታችኞቹን የአባይ ተፋሰስ ሃገራትን ለዓመታት ሲያነታርክ የነበረና ያለ ጉዳይ ነው። ባለፈው 2010 ዓመት፣ አስር አመት ከፈጀ ድርድር በሁዋላ የላይኞቹ ተፋሰስ ሃገራት የደረሱበት አዲስ የውሃ ድልድል የመፍጠር ስምምነት በጎ ጎኖች እንዳሉት ሆነው የነገሩ ሁሉ መጨረሻ አድርጎ መውሰዱ ግን ትልቅ ስህተት ነው።
ትኩረት ማስለወጥ ወይንስ የተጠና ግንባታ
የሰሞኑን ግርገር አንደኛውን ምክንያት እንይ፣ ከሰሞኑ የወያኔ አገዛዝ በቴሌቪዢን ሬዲዮና ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን በአባይ ወንዝ ላይ ያለንን ብሄራዊ ጥቅም በተመለከተ በተጠና መልኩ የሚያሰራጨው ፕሮፓጋንዳ መጠ-ነሰፊ ነው። እንደ ሰሞኑ የመናኛ ብዙሃኑ ዘመቻ ከሆነማ የአባይ ወንዝ ለመጀመሪያ ግዜ በኢትዮጵያ መኖሩ የታወቀው በዚህ ወቅት የሆነ ይመስላል።አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የግድቡን ግንባታ ደገፉ፣ የዚህና የዛ ሚኒስቴር መስሪያቤት ሰራተኞች መንግስት በአባይ ላይ የወሰደውን አቁዋም አደነቁ፣ የዚህ ከተማ ነዋሪዎች ለግድቡ ግንባታ ቦንድ ገዙ፣የህግ ታራሚዎች ከምግባቸው ቀንሰው ቦንድ ገዙ፣ በኦሃዮ የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት ድጋፋቸውን ገለጹ የሚሉት የኢቲቪ ዜና ዘገባዎች ትኩረት ናቸው። ልብ በሉ እነዚሁ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ የመናኛ ብዙሃን ከሶስት ሳምንት በፊት ስለ አባይም ሆነ ስለትልቁ ግድብ አንድም ነገር ትንፍሽ ብለው አያውቁም ነበር። ከትራንስፎርሜሽንና እድገት እቅዱ ወሬ በስቀር። ታዲያ ጥያቄው ያለው ለምን የትኩረት ለውጥ እንዲኖር ተፈለገ የሚለው ጉዳይ ላይ ነው። ስለ እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ተወርቶ ሳያልቅ፣ የሁለት አሃዝ (duble-digit growth) እድገትን ወሬ ሰምተን ሳንጠግብ እንደዱብዳ የግድቡ ወሬ ሃገሩን ለምን እንዲሞላው ተደረገ ማለቱ የበጎ አሳቢ ዜጋ ጥያቄ መሆን ይኖርበታል።
የትኩረት ለውጡን በተመለከተ ሊሰጥ የሚችለው አንዱ ምክንያት፣ ብዙ ግዜ መንግስታት አጣብቂኝ ችግር ውስጥ ሲገቡ ከሚወስዱዋቸው እርምጃዎች መሃከል በፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ህብረተሰቡን ከዋናው ጉዳይ ላይ ትኩረት መስረቅ ነው። የማስቀየስ/የማዘናጋት/የማደንዘዝ ስልት (politics of diversion/political ansthsia) ይሉታል የፖለቲካ ምሁራኖች። በምስራቁ ዓለም የነበሩ ኮሙኒስት መንግስታት አብዝተው ሲጠቀሙበት የነበረ ሲሆን፣ ስልቱ በአጠቃላይ መንግስታት እንደ ጭንቀት ማስተንፈሻ ወይንም ከገጠማቸው አጣብቂኝና ስጋት እንደ ማምለጫ ይጠቀሙበታል። የውስጥ ተቃወሞ ይነሳል የሚል ስጋት ሲኖር ያለና የሌለ የውጭ ጠላትን አጋኖ በማቅረብ ትኩርት መስረቅ የስልቱ አካል ነው። እንዳውም አንዳንዶቹ መንግስታት ኢኮኖሚውን ማስተዳደር አልሆን ሲላችው በውጭ ጠላት ማላከክ የለመዱት አሰራር ነው። ከሰሞኑ ወያኔ እያሳየ ያለው ባህሪም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነው።
ሁለት አሃዝ በማስመዝገበ እያደገ ነው የተባለው የሃገሪቱ ኢኮኖሚ መያዣ መጨበጫ በሌለው ቀውስ ውስጥ መዘፈቁ ለዘሞኑ ነጠላ ዜማ መለቀቅ (የአባይ ጉዳይ) በዋነኛ ምክንያትነት ይጠቀሳል። እንዳውም እየከፋና እየባሰበት የመጣው የኑሮ ውድነት፣ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ አልቀመስ ማለት፣ ጭራሹንም ከገበያ ድራሹ መጥፋት ፣ስራ አጥነት፣ አድሎአዊ የሃብት ስርጭት፡ ተገኘ የተባለውን ባለሁለት አሃዝ እድገት እርቃኑን የቆመ ባዶ ቁጥር ብቻ እንደሆነ በማያሻማ መልኩ አጋልጧል። ተገኘ የተባለው የቁጥር እድገት በአብዛኛው ሰው የቀን ተቀን ህይወት አንዳችም ለውጥ አለማሳየቱን በማየት የእድገቱን መኖር መሰከሩ የተባሉ አለም አቀፍ ተቁዋማት፡ የከዚህ ቀደም አስተያየታቸውን ዞር ብለው እንዲመረምሩ እየተገደዱ ነው። የመለስ አገዛዝ ከዚህ ቀደም ታይቶ ባልታወቀ ሁኔታ የተንሰራፋው ድህነትና ስራ አጥነት ምን እንደሚያስከትልና መዘዙን ከአቻወቹ የግብጽና ቱኒሲያ መሪዎች ውድቀት እንደተማረው ብዙ ማለት ይቻላል። ስለዚህ የኢኮኖሚ እድገቱን ረስተን በአባይ ላይ በምንሰራው ግድብ ብቻ “ትራንስፎርም” እናደርጋለን እያለን ነው። የግድቡ ግንባታና የአባይ ወሬ እንዲጋነን የሚፈለገው ድሆች ብንሆንም፣ የኑሮ ውድነት ችግር ቢኖርብንም ሆዳችንን አስረን፣ ወገባችንን ይዘን ግድባችንን እንገነባለን ነው። የውጭ ጠላቶቻችን ከመጡም እንመክታቸዋለን ወዘተ.. እና የመሳሰሉ ቀስቃሽ ብሄራዊ ስሜቶችን መፍጠር ነው።የልማት እቅዱ ባይሳካ ወይንም የኢኮኖሚ ቀውሱ ቢባባስ በአባይ ጉዳይ ላይ ያኮረፉ የውጭ ጠላቶቻችን ሴራና ተንኮል ሸርበው እንደሆነ በምክንያትነት ሊጠቀስ ነው። ማላከኪያ ተገኘ ማለት ነው።
ትኩረት መስረቅን/ማስቀየስን በተመለከተ ወያኔ ላለፉት ሀያ አመታት ሰምሮለታል። የሱን ያህል የሰመረለት ያለም አይመስልም።ያለፉትን 20 የወያኔ አገዛዝ ዓመታት ለተከታተለ ወያኔ ባንድም ሆነ በሌላ ምክንያት በቀውስ የውጥር ሲያዝ አጀንዳ እየፈጠረ በማዘናጋት አሁን አለንበት ወቅት ድረስ እንደደረሰ መናገር ይችላል። ተቃዋሚዎቹን ሳይቀር አጀንዳ እየፈጠረ በሚፈልገው የጨዋታ ክልል ውስጥ ማጫወት ተክኖበታል ቢባል አሌ የሚል ያለ አይመሰለኝም። እንዳውም አንዳንዶቹ በተዘጋጀላችው ወጥመድ ወስጥ ሰተት ብለው ገብተው ሰጥመው ቀርተዋል። አብዛኛው ህዝብማ ተቆጥረው የማያልቁ የማዘናጊያ ርእሶች እየተፈጠሩ ግዜውን በከንቱ እንዲያባክን የተፈረደበት ይመስላል። እያንዳንዱን እንዘርዝር ብንል ግዜና ቦታ ላይበቃን ይችላል ግን ዋና ዋናዎቹ፡- የግብርና መር ስትራቴጂ፡ የተሃድሶ መርሃግብር፡ የአምስት ዓመቱ እቅድ፡ የሚሊንየሙ ህዳሴ፡ ውሃ ማቆር፡ የሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት፡ የባንዲራ ቀን፡ የትራንስፎርሜሸንና እድገት እቅድ ወዘተ ወዘተ ……. እያለ ይቀጥላል። እነዚህ ሁሉ እቅዶችና መርሃ ግብሮች መሳካት አለመሳካታቸው ሳይረጋገጥ ሌላ የዳቦ ስም የወጣላቸው እቅዶች ይደረብባቸዋል። ለአንዳቸውም ስኬትም ሆነ ውድቀት ተጠያቂም ሆነ ተመስጋኝ ሳይኖር ነው ወደሌላ እቅድ ሽግግር የሚደረገው። ከመርሃ ግብሩ መተግበር ይልቅ ገና ሳይጀመር ስለስኬታማነቱ የሚለፈፈው ፕሮፓጋንዳ ግን አይጣል ነው። እንደ ፕሮፓጋንዳው መብዛትማ ከሆነ ኢትዮጵያ የዛሬ 15ዓመት ገደማ ነበር ከበለጽጉት አገራት ምድብ የተሰለፈችው።እውነቱ ከዚህ የተለየ ሆነ እንጂ።በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ማለት ቢቻልም ለጊዜው የምለውን እዚህ ጋር ብገታ ሳይሻል አይቀርም፣ ምክንያቱም በቅርቡ ለ20 ዓመታት ወደየትም ያልተኬደ የጥፋትና ውድመት ጉዞ /የባከኑ 20 ዓመታት/ (Twenty years on the road to no where) በሚል አንድ ርእስ አንድ መጣጥፍ ለማስነበብ ቃል እገባለሁ።
ወደርእሴ ፍሬ ነገር ስመለስ የአዲሱ ግድብ ግንባታና አባይን ፖለቲካ በተመለከተ ሰሞኑን የሚሰነዘረው “የወዮውላችሁ” ድንፋታ ከላይ ከተዘረዘሩት የወያኔ የማዘናጊያና መደናገሪያ ዘመቻዎች አንዱ እንደሆነ አንጂ የተለየ ምንም አዲስ ነገር የለውም። ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የሰሞኑን የወያኔ ባህሪ ከብዙ ምክንያቶችን አንጻር ማየት የሚቻል ሲሆን ከዚህ ውስጥ አንድ ሌላ እንደ ምክንያትነት ሊጠቀስ የሚገባ ጉዳይ ቢኖር ባለፈው ዓመት ምርጫ በ99.6% አሽነፍኩ ያለው ገዢው ህወሃት ወደ አንድ ፓርቲ የሚመራ ልማታዊ መንግስትነት (one party dominant developmental state) ለሚያደርገው ሽግግር ሀገራዊ ብሄረተኝነትን ማነቃቂያ የማድረግ አላማው ነው። “በዚህ አይነት ስርዓት የኢኮኖሚ እድገት ይገኛል፣ ሆኖም እድገት ለማምጣት ዋነኛው ማነቃቂያ የሃገራዊ ብሄረተኘነትን መቀስቀስ ነው” ከሚለው የስርዓቱ ደጋፊ ንድፈ-ሃሳባዊያን ቅመራ የመነጨ ነው። እንደነዚህ የአንድ አውራ ፓርቲ የጠንካራ መንግስት ስርአት ደጋፊ ምሁራን አስተሳሰብ ከሆነ ይህ አይነቱ ልምድ ቻይና በታይዋንና በአሜሪካ ላይ ያላት የባላንጣነት ስሜት፣ ደቡብ ኮሪያ በሰሜን ኮሪያ ላይ ያላትን የባላንጣነት ስሜት ተጠቅመውበታል እያሉ በመደርደር ክርክራቸውን ለማሳመር ይሞክራሉ።
በዚህ መነሻነት ከማን አንሼ ብሎ ሳይሆን አይቀርም መለስና አገዛዙ የሰሞኑን ግርግር መንስኤ። ለዚህም ነው ከግድብ ግንባታው ጋር ከሰሞኑን ወያኔ የለቀቀው የማጀቢያ ሙዚቃ (sound track)፡ “ኤርትራ ወየውላት” እና “ግብጽ ትጠንቀቅ” የሚሉ የዛቻ ቃላትን ነው።እንዳውም የውጭ ጠላት ያለህ የሚሉ ንግግሮች ከአውራው መለስ ጀምሮ እስከ ሎሌው ሃይለማርያም ድረስ መነገር ተጀምሮአል። አስገራሚው ነገር ፣ ከካየሮም ሆነ አስመራ እስካሁን በይፋ የተሰጠ ምላሽ አለመኖሩ ነው። ታዲያ ሃገራችንን በቀጥታ ስጋት ውስጥ የሚከት ትንኮሳ በዚህ ወቅት በሌለበት ያዙኝ ልቀቁኝን ምን አመጣው። ይህ ብቻም አይደለም ሃገራችን በውጭ ጠላት ተወጥራ ብሄራዊ ጥቅሟን የማያስጠብቅ በሄረተኛ መንግስት ባለበት የዲሞክራሲና የመብት ጥያቄ ማንሳት የክህደት ወንጀል እንደመፈጽም እንዲቆጠር ቅድመ ዝግጅት ውስጥም የተገባ ይመስላል። ባለፈው ሳምንት በፓርላማ ህጋዊ ለሚባሉት ተቃዋሚዎች የተሰጠው ማስጠንቀቂያ አላማ የመጀመሪያ ምልክት ሳይሆን አይቀርም። ሌላው የሰሞኑ የዳያስፖራ ዘመቻ አላማም አክራሪ የሆነው ዲያስፖራ በአባይ ጉዳይ ደፍሮ አይቃወመንምን ድጋፉንም ይሰጠናል፣ የባሰበት ቦንድ ገዝቶ ያለብንን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያቃልልናል የሚለው ከስሌቶቹ ውስጥ አንዱ ነበር። በተቃራኒው የዳያስፖራ ዘመቻው ውጤት በአጠቃላይ ውድቀት ሲጠናቀቅ፣ ወያኔም የከፋ ሽንፈትን ቀምሶ አፈግፍጎአል።
ብሄራዊ ጥቅምን በተመለከተ መለስና አገዛዙ ላይ የሚነሳ የተዓማኒነት ጥያቄ
በእርግጥ ወያኔ የአባይን ጉዳይ የሚያካርረው ለምንድን ነው? የዱብዳው ግድብ ግንባታስ ለምን የሰሞኑ አጀንዳ እንዲሆን ተፈለገ? የሚሉትን ጉዳዮች ከላይ በተነሱት ነጥቦች ለማሳየት ተሞክሮአል። ቀጣይ የሚሆነው የወያኔ መንግስት እና አውራው መለስ ዜናዊ በዚህ አብይ ሃገራዊ ጉዳይን በተመለከተ በሚጫወቱት ሚና ላይ የሚነሳ የተአማኒነት ጥያቄ ነው። ግልጽ ለመሆን መለስና አገዛዙ ከዚህ ቀደም የፈጽሙትን ሃገራዊ ክህደት ብዛትና ክብደት ስንመለከት በአባይ ወንዝ ላይ ያለንን ጥቅም በማስጠበቅም ሆነ በትልቁ ግድብ ግንባታ ሂደት የሚኖራቸውን ሚና እንዳንቀበል ምክንያት ይሆነናል። እንዳውም አንድም ለጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም፣ አልያም ሌላ ሃገራዊ ክህደት ለመፈጽም ካልሆነ በቀር የሰሞኑ መንደፋደፋቸውን በጤና አለመሆኑን እንድንጠረጥር ግድ ይለናል። አንድ ሁለት ብለን ጉዳዩን በስፋት እንመልከት።
የሃገር ሉዐላዊነትና የብሄራዊ ጥቅም ነገር ሲነሳ በኢትዮጵያውያን ዘንድ መለስ እና አገዛዙ የሚታወቁት እንደ ከሃዲ ፣የሃገርን ጥቅምን አሳልፎ ሻጭ ወንጀለኛ እንጂ ከቶ እንደ አርበኛ አይደለም። ሌላ ሌላውን ትተን መለስ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚታወቀው ሃገሪቷ የራሷ ወደብ አያስፈልጋትም በሚለው ክርክሩ ከዓለም አስደናቂ መሪዎች ተርታ በመመደቡ ነው። መለስ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚታወቀው የአልጅርሱን ስምምነት በመፈረሙ የተቃወሙት የቀድሞ ህወሃት ትግል አጋሮቹ ከሃዲ፣ባንዳ፣ተንበርካኪ፣ወዘተ በሚሉ ውንጀላዎች ሲከሱት እንደነበር ነው።መለስ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚታወቀው ለግዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም ሲል ብቻ ኢትዮጵያውያን ወጣት ወታደሮችን በማይመለከታቸው ጦርነት በሶማሊያ በረሃዎች አዝምቶ በረሃ እንዲበላቸው ያደረገ መሪ በመሆኑ ነው ። መለስ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚታወቀው የሃገራዊ ሉዐላዊነት መገለጫ በሆኑ እንደ ባንዲራ፣ የጋራ ታሪክ እና የመሳሰሉት ላይ አጽያፊ ንግግሮችን በመናገር ነው። መለስ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚታወቀው ለትንሽ የገንዘብ ጥቅም ሲል ሰፋፊ መሬቶችን ለባእዳን በመሸጡ ነው። መለስ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚታወቀው የመሬት ይገባኛል ላቀረበ ጎረቤት ሃገር የሃገር ድንበር ሳይሰስት አሳልፎ መስጠቱ ነው።ለዚህም ይመስለኛል በዋሽንግተን ተቃወሞ ያሰሙ መገኖች በባድመ ያልታመነ፣በአባይ አይታመንም የሚል መፈክር ሲያሰሙ የነበረው። አዎን መለስንና ማመን ቀብሮ ነው።
ሌላውን ሁሉ ይቅር ብንለው እንኳ መለስ በራሱ በአባይ ወንዝ ላይ የፈጽመውን የክህደት ስራ አንድ ሁለት ብሎ መዘርዘር ከባድ አይሆንም። አንደኛው የቀድሞው መንግስት ለመውደቅ እየተንገዳገደ በነበረበት ወቅት ከጀመራቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች መሃከል አንዱ የአባይ ገባሪ በሆነው በለስ ወንዝ ላይ የጣና በለስ ፕሮጀክት ስራ ነው። ብድሩ የሚሸፈነው በአውሮፓ ህብረት (በተለይ የጣልያን መንግስት) እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ሲሆን ግንባታውን የጀመረው ሳሊኒ የተባለው የጣሊያን የግንባታ ካምፓኒ ነበር። በነገራችን ላይ የአዲሱን ሚሊኒየም ግድብ ግንባታ ስራ ያሸነፈው ይህው ሳሊኒ ካምፓኒ ነው። እናም በእቅዱ መሰረት የጣና በለስ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ዘመናዊ ቴክኖሎጂና መስኖ በመጠቀም ከዚያ ውስን አካባቢ የሚገኘው ምርት ሲሶ የሚሆነውን የሃገራችንን ህዝብ የምግብ ፍጆታ ይሸፍናል የሚል ነበር። በብድር በተገኘው ገንዘብ ግንባታው ተጀምሮ ሳለ ነበር ወያኔ አካባቢውን የተቆጣጠረው። ምን እንደሆነ ሳይታወቅ ግንባታው ቆመ።የፕሮጀክቱ ንብረት ተዘረፈ። እንደ አካባቢው ነዋሪዎች ምስክርነት ከሆነ የፕሮጀክቱ ንብረት ወደሌላ አካባቢ ተጭኖ ሄዶአል። የቀረውም ሙጃ በቅሎበት ተዝረክርኮ እንዲባክን ተደረገ።የጣና በለስ ፕሮጀክት ነገር እዚህ ጋር አበቃ፣ ነገር ግን ሃገራችን እስካሁን ከአበዳሪዎች ለፕሮጀክቱ የተበደረችውን ገንዘብ ከነወለዱ እየከፈልን እንገኛለን። ስለ ትልቁ ግድብ ስናነሳ መቅደም ያለባቸው ጉዳዮችን አንተው የምለውም ስለዚህ ነው።
ሌላው መለስና አገዛዙ በአባይ ላይ የፈጽሙት የክህደት ስራ ደግሞ የሚከተለው ነው። እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1985 ዓም የዛን ግዜው የሽግግር መንግስት ፕሬዚዳንት መለስ ዜናዊ ግብጽን በይፋ ጎብኝቶ ነበር። ከዛኔው አቻው ሙባረክ ጋር የአባይ ወንዝን አጠቃቀም በተመለከተ አንድ ሰነድ ላይ ፈርሞ አዲስ አበባ ተመለሰ። በወቅቱ የነበሩ የተቃዋሚ ድርጅቶችና አንዳንድ ሀገር ወዳድ ምሁራን ስምምነቱን ኮንነው ብዙ በለው ነበር። ተቃወሞአቸው ስምምነቱ ውስጥ ባለ አንድ አንቀጽ ላይ ያተኩር እንጂ ሁሉም በአጠቃላይ ስምምነቱን ተቃውመውታል። በአንቀጱ መሰረት፡ “ኢትዮጵያና ግብጽ ከአሁን በሁዋላ በአባይ ወንዝ ላይ በተናጥል ምንም አይነት ስራ ላለመስራት ተስማምተዋል” ይላል። ይህ ማለት ግብጽ እስካሁን በአባይ ወንዝ ላይ ያደረገችውን የግንባታ ስራ ህጋዊነት መቀበል ሲሆን፣ በሌላ መልኩ ምንም ስራ ያልሰራችው ኢትዮጵያ ለመስራት ብታስብ የግብጽን ፈቃድ እንድታገኝ የሚያስገድድ አሳሪ አንቀፅ ነው። (የሰነዱን የተሟላ ኮፒ ካለበት ተፈልጎ ይፋ ለማድረግ ይሞከራል)። ለዚህ ነው ግብጾች ስምምነታችንን አክብሩ የሚል መከራከሪያ የሚያስቀድሙት።
አዲሱ የግብጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰሞኑን ወደ አዲሰ አበባ ለጉብኝት ሲመጣ ከሚያነሳቸው ነጥቦች አንዱ ኢትዮጵያ ይህን የስምምነት ሰነድ እንድታከብር መጠየቅ ነው። ሳልጠቅሰው የማላልፈው በዛ ስምምነት ወያኔ ያገኘው ጥቅም ቢኖር ግብጽ ከፍተኛና መካከለኛ የወያኔ አባላትን በደህንነትና የመረጃ ባለሙያነት ስልጠና መስጠቱዋ ነው። እንግዲህ አስቡት ይህን ሁላ ጉድ የተሽከመ አገዛዝ ነው ዛሬ አባይ ወይንም ሞት የሚለን።የሚያሳዝነው ወያኔዎቹ የማጃጃያ ስልታቸውን እየቀያየሩ ሲመጡ ጥቂት የማይባሉ ወገኖች የነሱን ማጃጃያ ተከትለው ሲጃጃሉ መመልከት የግርግሩ አንድ አካል መሆኑ ነው።
ስለግድብ ከተነሳ አይቀር፡ አንዳንድ አስቂኝ የቀደሙ ምሳሌዎች፡
ስለ ግድብ ከተነሳ አይቀር ከዚህ ቀደም አገዛዙ ስለፈጽማችው አስቂኝ የሚባሉ ስህተቶች ጥቂት እንበል። በውሃ ሃብቱዋ ከአፍሪካ አንደኛ እንደሆነች የሚነገርላት ሃገራችን የኤሌትሪክ ሀይል አመንጭታ ለጎረቤት ሃገራት ልትሽጥ ነው። “የምስራች ምስር ብሉ” የሚል ዜና ሰምተን እያጣጣምን ወር ሳይሞላን ነበር ኤሌክትሪክ በፈረቃ መታደል የተጀመረው። አሁን በቅርቡ ደግሞ መለስ ዜናዊ የግልገል ጊቤ ሁለት የሃይል ማመንጫን መርቆ አዲስ አበባ ሳይገባ የግድቡ መደርመሰ ዜና የቀደመው፣ እስካሁንም ግድቡ ስራውን አልጀመረም። ከባለሙያ ጥናት ይልቅ በፖለቲካ ወሳኔ (ትግራይን ራስ ለማስቻል) ተከዜ ወንዝ ላይ ሶስት ተርባይነሮች ተገጥሞለት ትልቅ የሚባል የሃይል ማመንጫ ሙሉ ወጪው በኢትዮጵያ መንግስት ተሸፍኖ ተሰራ በተባለ። ይሁንና ከመጀመሪያው ጥናቱ ላይ ችግር ስለነበረበት ግድቡ መቋጠር ከሚችለው ውሃ በታች ስለሚያከማች አሁን በተግባር እየሰራ ያለው አንዱ ተርባይነር ብቻ ነው።ይህንን ያነሳሁት አነስተኛ በሚባሉ እኒህ ፕሮጀክቶችን በብቃት ማሰፈጽም ያልቻለ መንግስት ነው እንግዲህ፣ይህን ታላቅ ግድብ ለመስራት የተነሳው።
ማጠቃለያ፡
ባለው ጆኦ-ፖለቲካዊ ጠቀሜታ አባይ ላይ የሚሰራ ማንኛውም ፕሮጀክት ከምህንድስናና ቁሳዊ ጉዳዮች ባሻገር ታሳቢ ሊያደርጋቸው የሚገቡ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ጉዳዮች መኖራቸውን አንድ መንግስት ይቅርና በግለሰብ ደረጃ ለማሰብ የማይከብዱ ናቸው።ነገር ግን እነዚህ ጉዳዮች ሲታሰቡ የሰሞኑ ታላቁ የሚሊኒየም/ህዳሴ ግድብን ግንባታ ድንገተኝነት(ዱብዳነት) ለታዘበ የሌላ ፖለቲካዊ ፍላጎት መወጫ ይሆናል ወደሚለው ድምዳሜ ላይ ለመድረስ በቂ ምክንያት ይሆናል። ከዚሁ ጋር የኑሮው ውድነት መጦ የጨረሰውን መከረኛ ህዝብ ለግድቡ ቦንድ ግዙ ብሎ መነዝነዝ ለምን አስፈለገ ብሎ መጠየቅ ሌላው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ቦንድ ግዙ ውትወታውን በተመለከተ ነገሩን ግልጽ የሚያደርግ ከሰሞኑ በአንድ የፌስቡክ ወዳጄ ገጽ ላይ ያገኘሁትን የዜና ዘገባ ከዚህ ጽሁፍ መጨረሻ ላይ እንዲያነቡት እጋብዛለሁ።
ከሁሉ በላይ ግድብም ሆነ ግንብ ከመስራቱ በፊት መቅደም ያለበት አንገብጋቢ ነገር ቢኖር በሃገራችን መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ብሄራዊ የጋራ መግባባት መድረስ ነው። ብሄራዊ የጋራ መግባባት ሳይፈጠር አባይ ላይ አይደለም ቀበና ላይ ድልድይ ለመስራት መሞከር አስቸጋሪ ሁኔታን ሊፈጥር ይችላል። ሃገራችንን በተመለከተ በፖለቲካው፣ ኢኮኖሚውንና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ሁላችንንም አሳታፊ ያልሆነ አግላይ ስርአት ይዘን በብሄራዊ ጥቅም መከበር ጉዳይ ላይ የምናከናውነው ማንኛውም እንቅስቃሴ ሌላ ችግር ጠሪ እንጂ የሚያመጣው መፍትሄ የለም ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል። ቁም ነገሩ ያለው ከዚህ ቀደም በሃገር ብሄራዊ ጥቅም ላይ ክህደት የመፈጽም ልምድ ያለው አገዛዝ፡ ወጥሮ የያዘውን የኢኮኖሚ ቀውስ ለማስተንፈስ እንዲሁም ከሚመጣበት ህዝባዊ መነሳሳት ለማምለጥ በሚፈጥራቸው ማለቂያ የሌላቸው ግዜያዊ የማዘናጊያ ርእሶች ሳንዘናጋ ቅድሚያ መለስና አገዛዙን ማስወገድ በቀጣይነትም የግድብም ሆነ ሌላ ግንባታ ስራዎቻንን በጋራ መስራትን ግብ አድርገን መነሳት አለብን።