በኦሮሚያ ከ120 በላይ ከፍተኛ ኃላፊዎች ታሰሩ

(ሪፖርተር) — በጨፌ ኦሮሚያ በተካሄደውና ስምንት ቀናት በፈጀው የሰሞኑ የኦሕዴድ ከፍተኛ ኃላፊዎች ግምገማ ከ120 በላይ ከፍተኛ ኃላፊዎች ታሰሩ፡፡ ግለሰቦቹ የታሰሩት ቡራዩ አቅራቢያ በሚገኘው ሳንሱሲ ኦሮሚያ ማረሚያ ቤት መሆኑ ታውቋል፡፡ ፊት ለፊት በግልጽ ሲካሄድ በነበረውና በመሬት አስተዳደር ዙሪያ ራስን በመጥቀም ጉዳይ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በነበረው በዚህ ግምገማ፣ በርካታ ሹም ሽሮች ተካሂደዋል፡፡

እስካሁን የታሰሩትን ግለሰቦች ማንም እንዳይጠይቃቸው የተከለከለ ሲሆን፣ በቅርቡ በሙስና፣ መንግሥትን በመክዳትና የሕዝብን አደራ አለመወጣት የሚሉ የክስ ጭብጦች ሊቀርቡባቸው እንደሚችል ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በግምገማውም በሙስና ምክንያት ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ከተደረጉት ባለሥልጣናት መካከል፣ የኦሮሚያ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሁሴን ገልገሉ፣ የኦሮሚያ ገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቶሎሳ ደደፎና ምክትላቸው አቶ ተስፋዬ አበበ፣ የኦሮሚያ ክልል የባህልና ቱሪዝም ኃላፊ አቶ አሊዩ ኡመር፣ የኦሮሚያ ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ግርማ ሰንበታ፣ የኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ገላና ኑሬሳና የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ቢራቱ ሲገኙበት፣ ከሥልጣናቸው እንዲወርዱ ተደርጐ በምትካቸው አዳዲስ የኦሕዴድ አባላት መሾማቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

አብዛኞቹ በሳንሱሲ ኦሮሚያ ማረሚያ ቤት በቁጥጥር ሥር የዋሉት በሰበታ፣ በዓለም ገና፣ በወለቴ፣ በሻሸመኔ፣ በአዳማ (ናዝሬት) እና በቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ከተሞች የሠሩ ኃላፊዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡ የክልሉ የተለያዩ ዞኖችና ቢሮዎች ኃላፊዎች፣ ከንቲባዎች፣ ሥራ አስኪያጆችና ሌሎች በኃላፊነት ላይ የተሠማሩ የወረዳ አስተዳዳሪዎችም ይገኙበታል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በፌዴራል መንግሥት በአፈ ጉባዔነት የሚገኙት የቀድሞው የኦሕዴድ ሊቀመንበርና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አባዱላ ገመዳና ሌሎች ከፍተኛ የኦሮሚያ ባለሥልጣናት ግምገማ፣ የኢሕአዴግ ጥምር ፓርቲዎች ከመጋቢት 5 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ በሚያካሂዱት ግምገማ ላይ በድጋሚ ይነሳል ሲሉ ምንጮቹ አክለው ገልጸዋል፡፡

ይህንን የኦሕዴድ ግምገማ የመሩት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ሙክታር ከድርና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ መሆናቸው ታውቋል፡፡