የተዋረደው ፍርድ ቤት

የአንተነህ ሙሉጌታ ድንቅ መፅሐፍ በሜልቦርን ይመረቃል

“የሁለት ዓለም ሰዎች”በሚል አብይ ርዕስ ስር በቅፅ 1 የተፃፈ “የተዋረደው ፍርድ ቤት”የተሰኘ ድንቅ መፅሀፍ በአውስትራሊያ-ሜልቦርን እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በመጪው ማርች 13 እንደሚመረቅ የዝግጅት ኮሚቴው አስታወቀ።

በግንቦቱ 1997 ዓ.ም ምርጫ ቅንጅትን በመወከል ተወዳድሮ ባሸነፈበት በአዲስ አበባ የመስተዳድሩ ዋና ፀሀፊ ሆኖ እንዲሰራ ተመርጦ በነበረው፣ ከቅንጅት መሪዎች ጋር ለሁለት ዓመታት በእስር ባሳለፈውና በህግ ባለሙያነቱ እጅግ በሳል በሆነው አንተነህ ሙሉጌታ የተፃፈው ይህ መፅሀፍ ፤በይዘቱም ሆነ በአቀራረቡ እስካሁን “የገዥውን ፓርቲ የፍትህ ቧልት” ለማሳየት ከተፃፉት ሁሉ ላቅ ያለና ታላቅ የታሪክ ምስክር እንደሆነ ረቂቁን የማንበብ ዕድል ያጋጠማቸው ይመሰክራሉ።

“የህግን ጉዳይ ቀለል ባለና ሳቢ በሆነ አቀራረብ ተፅፎ ሳነብ ይህ የመጀመሪያ ነው” ሲሉ ተመሳሳይ ሀሳብ የሰነዘሩት እነዚህ ወገኖች፤ኢትዮጵያውያን መፅሀፉን በማንበብ የአገራቸውን አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረስ በቅርበት ይመለከቱ ዘንድ አደራ ይላሉ።

“አንተነህ የህግ ባለሙያና ፖለቲከኛ ብቻ ሳይሆን በሳል ፀሀፊም መሆኑን እንናገራለን”የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፡ ከዚያም ባሻገር ብዙዎቻችን በእልፍኝ እንጅ በሰገነት የማናወራቸውን የማይደፈሩ እውነቶች “በሁለት ዓለም ሰዎች” መግቢያው ላይ በድፍረት ማስፈሩ እጅግ አስደንቆናል ብለዋል።

ከነዚህም መካከል፦“ራሳቸውን ማሸነፍ ያልቻሉ ተቃዋሚዎች፤ እንዴት ኢህአዴግን ያሸንፋሉ?”የሚለው የደራሲው አገላለፅ ልባቸውን እንደነካቸው ይገልፃሉ።

“ፀሀፊ በልቡ ያለውን እውነት ደፍሮ ያወጣል እንጂ በጭንቅላቱ ሂሳብ እየሰራ አይፅፍም፤እነ እገሌ ምን ይሉኛል? ከሚለው በላይ የሚጨነቀው እውነትን አዛብቼ ይሆንን? በሚለው ነው፤ጥብቅናውም ለሰዎች፣ለተቋማትና ለድርጅቶች ሳይሆን ለእውነት ነው፤ያች እውነት ልታሰቅለው ብትችል እንኳ አያፈገፍግም፤ አንተነህን ከእንደዚህ ዓይነት ፀሀፊዎች የሚመደብ ሆኖ አግኝቸዋለሁ” ብሏል-ከረቂቁ አንባቢዎች አንዱ።

በሜልቦርን ፉትስክሬይን በሚገኘው አፍሪካ ታውን ሬስቶራንት ከቀኑ 2፡00 ጀምሮ በሚከናወነው የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የክብር እንግዳ ሆነው የሚገኙት የቀድሞው የአካባቢው የኢትዮጵያውን ኮሚኒቲ ሊቀመንበርና “የኢትየጵያውያን ማንነት በባዕዳን ቅኝት”ደራሲ አቶ አዳሙ ተፈራ መሆናቸውን የዝግጅቱ መርሀ-ግብር ያመለክታል።

እንዲሁም የቀድሞው የብስራት ጋዜጣና የአሁኑ የቋጠሮ ድረ-ገፅ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ሶምሶን አስፋው በመፅሀፉ ዙሪያ ያደረገውን ግምገማ ያቀርባል።

በሜልቦርን እና አካባቢው የሚገኙ ሁሉ በተጠቀሰው ቦታና ሰዓት በመገኘት በዝግጅቱ ላይ መሳተፍ እንደሚችሉም የዝግጅት ኮሚቴው አስታውቋል።