የወንጌል አብዮት ለቤተ ክህነቱና የቤተ ክህነቱ ሰዎች
በፍቅር ለይኩን ከደቡብ አፍሪካ
No Revolution has ever taken place in the society that has been compared to that which has been produced by the words of Jesus Christ” ~Mahatma Gandhi
የዛሬ መጣጥፌ መነሻ የሆነኝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባለሁበት ጊዜ ያጋጠመኝ አንድ አሳዛኝና ስደንጋጭ ክስተት ነው። ነገሩ እንዲህ ነው፦
በአዲስ አበባ ከተማ ወስጥ የሚገኘውን ጥንታዊውና የብዙ ታሪክ ባለቤት የሆነውን የእንጦጦ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ወኤልያስ ቤተ ክርስቲያን የተመሰረተበትን 125ኛ ዓመት ለማክበርና የቤተ ክርስቲያኑን ቅርስ፣ ታሪክና በዚህ ቦታ የተወለዱና በቤተ ክርስቲያኑ የተማሩ በአጼ ምኒልክና በኃይለ ሥላሴ ዘመን መንግስት በኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተቋማት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የነበራቸውን እንደ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ሥላሴ፣ አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ፣ ወንድማማቾቹ አክሊሉና መኮንን ሀብተ ወልድና እንዲሁም በዚህ ቤተ ክርስቲያኑ ፊደል ቆጥረው ለሀገራችው ባለውለታ የሆኑ ሌሎቹንም አሁን በስም የዘነገኃቸውን የቤተ ክርስቲያኗን ልጆች ለመዘከር ሲባልና እንዲሁም ለቤተ ክርስቲያኑ የሙዚየም ግንባታ ጭምር ለማድረግ በተቋቋመው የልማት ኮሚቴ አማካይነት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ተደርጎ ነበር በወቅቱ።
በዚህ ቤተ ክርስቲያን የበዓል አዘጋጅና የልማት ኮሚቴ ውስጥ አባል የነበረ ጓደኛዬ በዓሉን በማስመልከት የእንጦጦ ቅዱስ ራጉኤል ወኤልያስ ቤተ ክርስቲያንን ታሪክና በቦታው ተወልደው፣ አድገውና ፊደል ቆጥረው ሀገራቸውን ያገለገሉ ከላይ የጠቀስኳቸውንና ሌሎችንም ታዋቂ ሰዎች በቤተ ክርስቲያኒቷ፣ በሀገራችን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ውስጥ ስለነበራቸው ድርሻ በተመለከተ ለሚዘጋጀው መጽሄት ሙያዊ እገዛ በማድረግ የበኩሌን ድርሻ እንድወጣ ሲጋብዘኝ ጥያቄውን በደስታ ተቀብዬ የልማት ኮሚቴውን በሊቀመንበርነት ይመሩ ከነበሩት በደርግ ዘመን የፖሊስ ኮረኔል ከነበሩ ታሪክ አዋቂ አባትና እንዲሁም ነፍሱን ከቅዱሳኑና ከባለቅኔዎቹ ጎን ያሳርፍልንና የደራሲ አብርሃም ረታ ወንድም ከሆኑት ከአቶ እጅጉ ረታ ጋር በመሆን የመጽሄት ዝግጅቱን ጀመርን፤ መጽሄቱ ደረጃውን የጠበቀና ታሪክን ያዛባ እንዳይሆን ለማድረግ በማሰብ በቤተ ክርስቲያኑ ታሪክና በእነዚህ ታዋቂ ሰዎች ዙሪያ የተጻፉትን መዛግብት ለመመረምርና ለማጣቀስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋምን ቤተ መጻህፍት እንጠቀም ነበር፤ በጊዜው በዩኒቨርስቲው ውስጥ ስለነበርኩ መረጃዎቹን በማሰባስብና በማጥናቀር ዙሪያ ብዙው ኃላፊነት በእኔ ላይ የወደቀ ነበር።
በዚህ መዛግብትን በመመርመር ሥራ ላይ እያለሁ ለመጽሄቱ ዝግጅት ያግኘኍቸውን መረጃዎች እንዲያዩትና እንዲሁም እግረ መንገዴን በምርምር ተቋሙ ተሰባስበው ያሉትን በርካታ የቤተ ክርስቲያኒቱን የብራና መጽሀፍቶችና የተቋሙን ቤተ መዘክር/ሙዚየም ጭምር እንዲጎበኙ የቤተ ክርስቲያኑን አስተዳዳሪ ጋበዝኳቸው፤ ገና በአፍላ ጉልምስና እድሜ ላይ ይገኙ የነበሩት መነኩሴ ግብዣዬን በደስታ ተቀብለው ነበር ወደ ዩኒቨርስቲው የመጡት፤ ከዋናው በር መግቢያ ጀምሮ በትህትና የተቀብልኳቸው አባት በዩኒቨርስቲው ውበት እየተደነቁና ቤተ መንግስታቸውን ለዚህ ታላቅ ተግባር የሰጡትን ኃይለ ሥላሴን እያመሰገኑና እየተጨዋወትን ወደ ልኡል ራስ መኮንን አዳራሽ አመራን ወደ መግቢያው በር ልንደርስ አካባቢ ሰዎች እየተፈተሹ ሲገቡ ያዩት አባት ፍተሻ አለ እንዴ በማለት በአግርሞት ጠየቁኝ፦
እኔም መልሼ ያው የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንትና ታላላቅ ኃላፊዎች ያሉት በዚህ ሕንፃ ውስጥ ሰለሆነ ለድህንነታቸው ሲባል ነው በተጨማሪም በዚህ ሕንፃ ውስጥ በዋጋ የማይተመኑ ብዙ ቅርሶች ስላሉ ለዛም ጭምር ነው ብዬ አስረዳኍቸው። እኝህ መነኩሴ ቅሬታ በሚስተዋልበት ፊት መልሰው አይ እንደው ልጄ እንደምታውቀው የእንጦጦ ጫካ አያስተማምንም እናም ራሴን ለመጠበቅ ስል ሽጉጥ ቢጤ ይዤ ነበር አሉኝ እንደማፈር ብለው ታዲያ ፍቃድ የለውም እንዴ በማለት ጥየኳቸው፤ ለነገሩስ ፈቃድ አለው አሉኝ መልሰው አይ እንደዛ ከሆነ ችግር የለውም ደግሞም እርሰዎን ላይፈትሹዎት ይችላሉ አልኳቸው። እንዳልኩትም ባንዘረፈፉት ቀሚስ በአናታቸው ላይ በደፉት የማስመሰያ “የዓለም ለምኔ” የምንኩስና ቆብና በደረታቸው ላይ ባንዥረገጉት መስቀል ፍርሃትና ትህትና ያደረባቸው ሰሜናውያኑ የደህንነት አባል ፈታሾች መስቀላቸውንና እግራቸውን ለመሳም ሲሽቀዳደሙ አየሁና ልቤ በእጅጉ አዘነ በሚያሳልሙትና በሚሳለሙት መካከል ያለው ብቸኛው ልዩነት የለበሱት የደንብ ልብስ (uniform) እንጂ ተሳላሚዎቹ እንደሚያስቡት የመንፈሳዊነት ብቃት አልነበርም፤ የአባን ኮልት ሽጉጥ የያዘችው ጥቁር ሳምሶናይት ከጠባቂዎች ተሰውራ በኩራት የዩኒቨርስቲውን ፕሬዝዳንት ቢሮ አልፋ ወደ ቤተ መዘክሩ አመራን በጉዞችንም ሆነ በጉብኝታችን ወቅት ሥጋዬ እንጂ አእምሮዬ ከመንኩሴው ጋር አልነበርም ከራሴ ጋር ኃይለኛ ሙግት ውስጥ ነበርኩ።
መንፈሴ በእጅጉ ሐዘን ተሰማው ለካ በወሬ የምሰማው ትክክል ነበር ማለት ነው? ታዲያ የእንጦጦ ጫካ ክፉ አውሬዎችን ለመከላከል የተያዘች ሽጉጥ ምን ስትል መሃል አዲስ አበባ ድረስ ሽርሽር አማራት? ደግሞስ እስቲ ወገኖቼ ፍርዱ የእንጦጦ ጫካ ተመንጥሮ አልቆ ያፈጠጠ የቋጥኝ ድንጋይና የተራቆተ መሬት እንጂ ምን ጫካ አለው? የትኛውስ አስፈሪ አውሬዎች አሉበት የእንጦጦ ጫካ ሽጉጥ ለማስታጠቅ የሚያደርስ??? ነው እኛ የማናውቀው የተሰወረብን ሌላ የእንጦጦ ጫካ ለመንኩሴው ተከስቶላቸው ይሆን? ወይስ ከጫካው ያመለጡ አውሬዎች ከቤት እንሰሳ ጋር ተመሳስለው ወደ መሀል አዲስ አበባ ገብተው ይሆን? አይ ነገሩ ሌላ መሆን አለበት! በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም የታጠቁና የተደራጁ የአባ ጳውሎስ ኃይሎች እንዳሉ በወሬ የሰማሁት አሁን በተግባር እውነታው ወለል ብሎ ታየኝ።
ይሁንና አቡነ ጳውሎስ በአድዋ ልጅነታቸው ብቻ የመረጧቸው መነኩሴ ብልጠት የጎደላቸው የዋኽ ቢጤ መሆናቸው ሲታይኝ ለሿሚውም ለተሿሚውም ለሁለቱም አዘንኩ፤ ከአለቃቸው የተሰጣቸውን ድብቅ መንታ ማንነትና ልዩ ሴራ በዚህ መልኩ ከሆነ እየፈጸሙ ያሉት፣ አቡነ ጳውሎስ በስም የዓድዋ ልጅነት ተታለዋል፤ እኝህ መነኩሴ ምስጢራቸውን ሁሉ የባቄላ ወፍጮ እንዲሆን አድርገውታልና ለነገሩ ምን ምስጢር ሊኖር ይችላል በጠራራ ጸሀይ የአቡነ ጳውሎስ ታጣቂዎች በእስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ነፋሳቸውን ስለነጠቋቸው ባህታዊ መነኩሴ የዶሮ ደም የፈሰሰ ያህል እንኳ መች ተሰማቸው? እናም በትክክል እንደታዘብኳቸው እኚህ መነኩሴ ነኝ ባዩ አስመሳይ በእጅጉ የተወሳሰበው የፖለቲካውና የቤተ ክህነቱ የስለላ ሂደት መርብ ውስጥ ገና በቅጡ ያልገቡና ያልገባቸው መሆናቸው ገባኝ፤ እናም በቆይታ ሲነቁና ሲበቁ ሊያከናውኑት የሚችሉት ስይጣናዊ የጥፋት ተልእኮና ውድመት ውሉ ከየት እስከየት ሊመዘዝ እንደሚችል ከወዲሁ ሲታየኝ አይኖቼን ወደ ታላቁና ቅዱሱ የበጎች እረኛ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ በማቅናት ኤሎሄ አልኩኝ በለሆሳስ! አቤቱ በክቡር ደምህ ፈሳሽነት ቤዛ የሆንካትን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን አስብልን በማለት!!!
እኝህ መነኩሴ በእንጦጦው ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ብዙም አልቆዩ ተወላጅና በቦታውም ሆነ በቤተ ክርስቲያኑ ሙሉ ባለመብት እኛ ነን በሚሉ ሰዎችና በመነኩሴው እንዲሁም እሳቸው ባደራጇችው ሰዎች በጦር መሳሪያ ጭምር በታገዘ በተፈጠረ ትልቅ ጠብ የተነሳ የቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር በፌዴራል ፖሊስ ተከቦ በመጨረሻ በብዙ ድካም ችግሩ እልባት አግኝቶ መንኩሴው ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ ተደረገ፤ በአቡነ ጳውሎስ የክብር እንግድነትና በፌዴራል ፖሊስ አጃቢነት የተጣለው የቤተ ክርስቲያኑ የሙዚየም የመሰረት ድንጋይ እስከ ዛሬ ድረስ ምንም የግንባታ እንቅስቃሴ ሳይደረግበት እንዳለ አለ።
በመሰረቱ በወቅቱ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ያሉት ቅርሶች ለሙዚየም እይታ የሚበቃ ቁጥር ያላቸው አልነበሩም፤ በወቅቱ ስለ ቤተ ክርስቲያኑ ታሪክና ቅርስ በግሌ ጥናት ባደረኩበት ጊዜ በተለይ ለዚህ ጥናቴ በቂና አስተማማኝ የሆነ መረጃ ያገኘሁበት በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክና የቅርስ አስተዳደር የትምህርት ክፍል ሊቀመንበር የሆኑት (Chairman of the Department of History and Heritage Management) ዶ/ር ውዱ ጣፈጠ ለመጀመሪያ ዲግሪ ማሟያ መመረቂያ የሆናቸውን የምርምር የጥናት ጹሁፍ ያዘጋጁት በዚሁ ቤተ ክርስቲያንና በእንጦጦ ርእስ አድባራት ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን አመሰራረት ታሪክ ላይ ነበር፤ በዚህ የመመረቂያ ጹሁፋቸው በእንጦጦ ደብረ ኃይል ራጉኤል ወኤልያስ የነበሩትን ቅርሶች በመመረቂያ ጹሁፋቸው መጨረሻ ገጽ ላይ አባሪ ያደረጉትን የቅርሶች ዝርዝር ከተመለከትኩ በኃላ የተዘረዘሩት ቅርሶች በሙሉ ማለት ይቻላል በቤተ ክርስቲያኑ እንደሌሉ ለመታዘብ ችያለሁ፤ በቤተ ክርስቲያኑ ለረዥም ዓመታት የቆዩ ሰዎች እንደነገሩኝ ጣሊያን ከሀገራችን ከወጣ በኃላ ታቦቱ ወደ መርካቶ ሲዛወር ቅርሶቹም አብረው መዛወራቸውን በሀዘኔታ አጫወተውኛል፤ በትክክል የተባሉት ቅርሶች እዛ ስለመኖራቸው ግን ጥርጥር አለኝ። ዛሬም ቢሆን በቤተ ክርስቲያኗ በነገሰው ሥረዓት አልበኝነትና ዘረፋ የብዙ ትውልድ ታሪክና ቅርስ እየተዘረፈ እየተበላሽና ወደ ውጭ ሀገራት እየተሻገሩ ናቸው። ይኽም ሌላ በትውልዱ ላይ የተንጣጠረ ትውልድን ታሪክና ቅርስ አልባ የማድረግ ዘመቻ ነው።
ወደ ዋናው የጹሁፌ ጭብጥ ስመለስ ለዘመናት የሃይማኖት ካባን በደረቡ ፖለቲከኞችና ገንዘብ አምላኪ ይሁዳዎች፣ ሆዳቸው አምላካቸው ክብራቸው በነውራቸው በሆኑ ሰዎች ሲታመስና የኖረውና በሰይጣን ክፉ አሰራር የተተበተበው የቤተ ክህነቱ ተቋምና ቤተ ክርስቲያናችን፣ ለመታጠቅና ለማስታጠቅ፣ ለመግደልና ለማስገደል፣ ለዝርፊያና ምግባረ ብልሹነት፣ ለሴራና ለተንኮል ታሪክ አዲስ አይደሉም፤ አጼ ቴዎድሮስ ያራመዱ በነበረው ኢትዮጵያን የማዘመን ሂደት ውስጥ በዘመኑ የሀገሪቷ ኢኮኖሚ ወሳኝ የነበረውን የመሬት ሀብት ያለአግባብ የያዙት የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና የቤተ ክህነቱ ተቋም በአጼ ቴዎድሮስ የመሬት ፖሊሳቸው ምክንያት በብዙ ሥራ ፈት ካህናትና ደብተሮች ጥርስ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸው ነበር፤ እንዚህ ጥርሳቸውን የነከሱባቸው ቀሳውስትና ደብተሮች አጼ ቴዎድሮስን ለመግደል አሸምቀው ይጠባበቁ ነበር። እናም በአንድ ወቅት አጼ ቴዎድሮስ በሚገኙበት ታላቅ የቤተ ክርስቲያኗ መንፈሳዊ በዓል ላይ እነዚሁ ደብተሮች የአጼ ቴዎድሮስን አንገት ለመቅላት በእጀ ጠባባቸውና በቀሚሳቸው ውስጥ የታጠቁትን ጎራዴ ለንጉሱ አንድ ታማኝ ሹክ ብሏቸው ህይወታችው ሊተርፍ የቻለበትን አጋጣሚ ታሪክ ዘግቦ አቆይቶልናል። በመድሃኒት በድግምትና በአጋንት አሰራር የተካኑ የቤተ ክህነቱ ሊቃውንት ነን ባዮች በቤተ መንግስትና በየመኳንቱ ቤት እየዞሩ ሥራቸው ይሄ እንደነበረ ብዙ የታሪክ ማስረጃዎችና ማጣቀስ ይቻላል። ይሄ በምንም መልኩ ንጹሃን የሆኑትን የቅዱስ ወንጌል ባለ አድራዎቹን ታላላቅ የቤተ ክርስቲያናችንን ካህናት አባቶቻችንና ሊቃውንቶች አይመለከትም።
ቤተ ክርስቲያኒቷ በሰለሞናዊው ስርወ መንግስት ውስጥ ከነበራት ረጅም እጅ የተነሳ የነበረውን ሹም ሽረትና ፖለቲካዊ ሚና ወደ ኃላ ተመልሰን የታሪክ መዛግብት ብናገላብጥ ጉድ የሚያሰኙ ብዙ ታሪኮች አሉ፤ ከላይ በአጭሩ ለመጠቆም እንደሞከርኩት በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ የድግምቱ የምትሃቱና የአጋንታዊ አሰራሩ በዋንኝነት ተጠቃሽ ነው። በቤተ ክርስቲያን ጉያ ተሸሽገው ባህታዊና መነኩሴ ነን በሚሉ በሐሰተኛ ህልም ኣላሚዎችና ባለ ራእይዎች በሚነገር የሐሰት ትንቢት የተነሳ ለዙፋን ሲሉ ወንድማማቾች ሳይቀሩ የተራረዱበትና ብዙ ነገሥታት ሕይወታቸውን ያጡበት ታሪክ በሀገራችን በሽ በሽ ነው፤ እስከ አሁንም ድረስ በጣም በእጅጉ የሚገርመኝ ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ለጌታችንና ለአምላካችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የተገባውን፤ የይሁዳ አንበሳ የሚለውን ስያሜ ኃይለ ሥላሴ በፖለቲካዊ ስልጠትና ብልጠት ዘውዱ ከእሳቸውና ከቤተሰቦቻቸው ውጪ እንዳይወጣ ለመከላከል ሲሉ ይሄን በቅዱስ ዮሐንስ ራእይ መጽሀፍ ምእራፍ 5፤5 ለኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠውን ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ/የይሁዳ አንበሳ ስያሜ ለራሳቸው በማድረግ “ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ስዩመ እግዚአብሔር” ተብለው የተቀቡበትን በዓለ ንግስናቸውን ይደልዎ በማለት የቤተ ክህነቱ ተቋም ማረጋገጫ የሰጠበትን መንፈሳዊ ወይም መጽሀፍ ቅዱሳዊ አመክንዮ ካለ ሊያስረዱን ይገባል።
ዛሬ በካረቢያንና በጀማይካ አሁን አሁን ደግሞ በአፍሪካ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ በነጮቹ ጭምር እየተስፋፋ ያለው ኃይለ ሥላሴን ጥቁር መሲህ የማድረግ ባእድ አምልኮ በከፊልም ቢሆን ውሉ የሚመዘዘው ከዚህ ኃይለ ሥላሴ በማን አለብኝነት ሥልጣናቸውን ፍጹማዊና ተቀናቃኝ አልባ ለማድረግ ለንግሥናቸው ከደረቡት መለኮታዊ ማእረግ ነው። ይሄን በተመለከተ በወቅቱም ቢሆን አሁን ከቤተ ክህነትም ሆነ ከቤተ ክርስቲያን አባቶች የተሰጠ ምላሽ አላደመጥኩም፤ ስለዚህ ስያሜ ታሪካዊ ሂደት የምታውቁ አባቶችና በወቅቱ የነበራችሁ ሰዎች ከዚህ ስያሜ ጀርባ ስላለው እውነት እናውቅ ዘንድ እርዱን። በግሌ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለሀገራቸው እድገት ለቤተ ክርስቲያኗ መስፋፋት ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለዓለም ሰላምና ለአፍሪካ አንድነት መቋቋም ላደረጉት ጥረት አድናቂያቸው ብቻ ሳይሆን አፍቃሪያቸው ጭምር ነኝ፤ ግና ዙፋናቸውን በተመለከተ የነበራቸውን አቋምና ብልጠት ግን እስከ ዛሬ ከተባለውም በላይ ብዙ ሊባልለት የሚችል ነገር አለ፤ ይህን ግዙፍ ጉዳይ በዚህ ጹሁፍ ልነካው አልወድም።
ወደ ተነሳሁበት ርእሰ ጉዳይ ስመለስ በጠባብ ብሔርተኞችና በታጣቂዎች፣ በጣት ከሚቆጠሩት በስተቀር በቃል ከሚያነበንቡት ጥራዝ ነጠቅ እውቀታቸው ውጪ የመጽሀፍ እውቀትና ምንም መንፈሳዊ ፍሬ የሌላችው ሰዎች በሞሉበት ቤተ ክህነት ስላለው አጋንታዊ አሰራርና ዘረኝነት እንዲሁም አቡነ ጳውሎስን ጋሻ አጃግሬ ሆነው ለከበቧቸው ሰዎች በወንጌል ቅዱስ ቃል የተቃኘ አብዮት እንድሚያስፈልጋቸው ጥያቄ የለውም፤ ዛሬም ሁሌም ደጋግሜ እንደምለው በወንጌል ቃል ወልዳ ካሳደገችኝ ቤተ ክርስቲያኔና እውነተኛ አባቶቼ ዘንድ ጠብ የለኝም፤ ግና ቤተ ክርስቲያንን ተጠልለው በውጭ መሰቀል በውስጥ ገዳይ መሳሪያ በመታጠቅ በግልጽና በሥውር አጋንታዊ የጨለማ ሥራ በሚያካሂዱ የአመጻ ልጆች ላይ በወንጌል ቃል የሆነ አብዮት ይታወጅባቸው ዘንድ ድርሻችንን ለማበርከት መነሳት የሁላችንም የቤተ ክርስቲያን ልጆች ኃላፊነትና ግዴታ ነው። ይሄ ጹሁፍም ማንንም በግል ለማጥቃት የጻፍኩት ሳይሆን እንደማንኛውም የቤተ ክርስቲያኒቷ ልጅ እንዲህ ዓይነቱ የርኩሰት አሰራር በቅድስናው መቅደስ ሲነግስ ዝም ብሎ ማየት የሚያስችል ወኔ ባጣ ነው ይህችን ትዝብቴን ከወገኖቼ ጋር ለመካፈል ብእሬን ያነሳሁት።
ዛሬ ዛሬ ቤተ ክርስቲያኗን ተግን አድርገው ያሉ አንዳንድ ገንዘብን ብቻ ማእከል ያደረጉ አገልጋዮችም ሆኑ በቡድን የተደራጁ ማኅበራት ጭምር የቆሙበት መሰረት አሸዋ ከሆነ ከማይቀረው የወንጌል ቃል አብዮት ማእበልና የክርስቶስ ኢየሱስ ጅራፍ ለማምለጥ መሸሻ ጥግ አይኖራቸውም፤ ለነቢየ እግዚአብሔር ለኤርምያስ እንደተነገረው የእግዘብሔር ቃል ከአንደበታቸው የሚፈስ ቅዱሳን የእግዚአብሔር ሰዎች እንዚህን ምንደኞችና የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች በቤተ ክርስቲያናችን የቅድስና አደባባይ ላይ ያቆሙትን የዘርኝነት፣ የዝርፊያ፣ የሞራል አልባ መንፈሳዊ አልባ የማንነታቸውን ጣኦት ይነቅሉና ያፈርሱ ዘንድ ሥልጣን አላቸው፣ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፦
እግዚአብሔርም አጁን ዘርግቶ አፌን ዳሰሰ፦ እነሆ ቃሌን በአፍህ ውስጥ አኑሬያለሁ፤ እነሆ ትነቅልና ታፈርስ ዘንድ ትገለብጥ ዘንድ፣ ትሰራና ትተክል ዘንድ በአህዛብና በመንግስታት ላይ ዛሬ አድርጌሃለሁ አለኝ። ኤርምያስ 1፤9_10 እንዲሁም መዝሙረኛው ንጉሥ ዳዊት እንደተናገረው፦
“ቅዱሳን በክብር ይመካሉ በምንጣፋቸውም ላይ ሐሴትን ያደርጋሉ፤ የእግዚአብሔር ምስጋና በጉሮሮአቸው ነው። ሁለት አፍ ያለው ሰይፍ በእጃቸው ነው በአህዛብ ላይ በቀልን በሰዎችም መካከል ቅጣትን ያደርጉ ዘንድ ንጉሶቻቸውን በሰንሰለት አለቆቻቸውን በእግር ብረት ያስሩ ዘንድ የተጻፈባቸውን ፍርድ ሁሉ ያደርጉባቸው ዘንድ ለቅዱሳን ሁሉ ይህች ክብር ናት።” መ/ዳዊት 149፤5_9። በዚህ ሰይፍ በሆነ በወንጌል ቃል የታጠቁ ወንድሞችና አባቶች ጌታችን መድኃኒታችን ቤቱን ከነፍሰ ገዳዮች፣ ከገንዘብ አምላኪ ይሁዳ ነጋዴዎችና ነፍሰ በላዎች ያነጹልን ዘንድ እነዚህን የወንጌል አርበኞች በተስፋ እንጠባበቃለን፣ የቤተ ክህነቱ ተቋምና አገልጋዮቹ ያሉበትን የሞራል ውድቀት፣ ሙስና፣ ዝርፊያና አልጠግብ ባየነት ለመዘርዘር አይቻልም ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች እንደስጠነቀቃቸው “ፍሬ ከሌለው የጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፤ ይልቁንም ግለጡት እንጂ፣” እናም በቤተ ክህነቱ ተቋምና በቤተ ክህነቱ ሰዎች ዙሪያ ስላለው ጭንቅላት አሲይዞ ኡ ኡ ኡ…! ስለሚያሰኘው ጉድ ስንቱን መዘርዘር ይቻላል፤ ቃሉ እንደሚል “እነርሱ በስውር ስለሚያደርጉት ነገር መናገር እንኳ ነውር ነውና፤ ሁሉ ግን በብርሃን ሲገለጥ ይታያልና፤ የሚታየው ሁሉ በብርሃን ነውና።” ይሄን ነውር በብርሃን የሚገልጥ የለውጥ የወንጌል አብዮት የቤተ ክህነቱ ተቋምና ሰዎቹ ያስፈልጋቸዋል፤ ጊዜውን ያቅርብልን እስቲ የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ!!!
ሠላም! ሻሎም!