የሟሟያው ምርጫ በሀሰተኛ ሪፖርቶች ደምቆ ተጠናቀቀ

ከ10ሺህ በላይ የኢህአዴግ እጩዎችና 2 የተቃዋሚ እጩዎች የተወዳደሩበትና በትላንትናዉ ዕለት የተካሄደው የማሟያ ምርጫ የመራጮች ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል እንዳልነበረ፣ የነበሩት ውስን መራጮችም የኢህአዴግ አባል በመሆናቸው ምክንያት ተገደው ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የሄዱ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በምርጫ ጣቢያዎቹ ተዘዋውሮ ሁኔታውን ለመመልከት የሞከረው ባልደረባችን ጣቢያዎቹ ጭር ብለው የቆዩ እንደነበርና መራጮች በሚመጡበት ወቅትም በተናጥል ሳይሆን በህብረት ይመጡ እንደነበር ለመታዘብ ችሏል፡፡ ይህ የሆነበትን ምክንያት ለማጣራት ባደረገው ጥረት ኢህአዴግ ባፈው ግንቦት ወር ለተካሄደው ምርጫ እንዳደረገው የአንድ ለአምስት የጠርናፊ ተጠርናፊ የምርጫ ስትራቴጂውን በአሁኑ የማሟያ ምርጫም እንደደገመው አረጋግጧል፡፡ ይህን ስትራቴጂ ተቃዋሚዎች ባልተወዳደሩበት በዚህ ምርጫ ለመተግበር ያስፈለገበትን ምክንያት የገለፁልን ውስጥ አዋቂ ምንጮቻችን እንዳስረዱት ኢህአዴግ የጠርናፊ ተጠርናፊ ስትራቴጂውን ለሚቀጥለው የ2007 ዓ.ም ምርጫም መድገም ይፈልጋል፡፡ ይህንን ለማድረግ እንደ አዲስ ምርጫው ሲደርስ ከመሯሯጥ ይልቅ ባለፈው ምርጫ የተደራጀውን ሀይል ሳይበተን እንዲቆይ ማድረግ የሚሻል መሆኑን በፓርቲው ታምኖበት በአሁኑ የማሟያ ምርጫም ይኸው በስራ ላይ እንደዋለም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የአሁኑ የማሟያ ምርጫ በተጠቀሰው ስትራቴጂ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ጉዳዮች ከባለፈው ሀገር አቀፍ ምርጫ ጋር የሚያመሳስለው በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን እነዚህ ውስጥ አዋቂዎቻችን ይናገራሉ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶው ፈረንሳይ ለጋሲዮን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባለ አንድ የምርጫ ጣቢያ አስፈፃሚ የሆኑ ግለሰብ ስማቸው እንዲሸሸግ ጠይቀው እሳቸው በሚያስተባብሩት የምርጫ ጣቢያ ያለውን እውነተኛ ገጽታ ለዜና አገልግሎት ክፍላችን ገልጸዋል፡፡ አስፈጻሚው እንዳሉት በእሳቸው ምርጫ ጣቢያ የተመዘገቡት መራጮች 113 ብቻ ሲሆኑ 546 ሰዎች እንደተመዘገቡ ተደርጎ ሪፖርት ተልኳል፡፡ በትላንትናው ዕለትም በነበረው የምርጫ ሂደት እስከ ቀኑ 10፡20 ድረስ ተጠርንፈው የመጡ 33 የኢህአዴግ አባላት ብቻ ድምጽ የሰጡ ቢሆንም 540 መራጮች ድምጽ እንደሰጡ የሚያሳይ ሪፖርት አስቀድሞ የተዘጋጀ መሆኑንና ይህ መመሪያም ከበላይ ሀላፊዎች እንደመጣ ጨምረው ገልጸዋል፡፡