የሴቶች የትግል ተሣትፎ ከትናት እስከዛሬ

ከሎሚ ተራተራ

አትነሺም ወይ አትነሺም ወይ፤ እህት አትነሺም ውይ፤
በግፍ የተገደለው፤ የተሰደደው ያንቺ አይደለም ወይ?
እሺ እነሣለሁ፤ እሺ እነሣለሁ፤ የሕዝቤን ጩኽት ስምቼዋለሁ፤
ሌትና ቀንም እታገላለሁ፤ ነፃነቴንም አስመልሣለሁ።

መቼም ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ እንዴት ነበር ያ ዘመን ? አሁነስ እንዴት ነው? ብሎ መጠየቅ ግድ ይላል። ትውልድ የት እንዳለና ምን እንደጎደለው አጥርቶ መመርመር በጣም አስፈላጊ ነው። ከውድቀትም ሆነ ከክስረት ያድናል እና።!

ሰሞኑን ቁጭ ብዬ በሀገራችን ኢትዮጵያና በህዝብ ላይ የደረስውን አበሳ እያወጣሁ እያወረድኩ አይ ፍርዳችን መቼ ይሆን ማብቂያው፤ ? ምንስ ብናደርግ ነው ከዚህ አስከፊ ጨካኝ አውሬ የምንገላገለውና ምድሪቷ ሰላም የምታገኝው? ብዬ እርሴን ስጠይቅ ድንገት የኮሎኔል መንገስቱ ሐይለማሪያም መፈክር ፦

“ያለሴቶቸ ተሳትፎ አብዮት ግቡን አይመታም ! “ ያሉት ትዝ ቢለኝ ተገረሜ ..ሣቅ አልኩና..

ሌላኛው ስውም በዘመኑ አባባል ተገርመው፦ (“ምን አብዮት ብቻ ያለሴቶቸ ትሳትፎ ለሊቱም አይነጋ”)

ያሉት ቢያስደነቀኝ። ክት…. ብዬ… ስቄ .. እውነት ብለው ነበር፤ አብዮቱ ግቡን መታም አልመታ፤ የሴቶቸ ተሳትፎው ግን አስፈላጊ ነበር። በማለት ይህቺን ለመጫር በቃሁ እላችኋላሁ።

አዎ የ ኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ ነው። ስለስፊው ታሪካቸን ብዙ እንናገር ብንል ጌዜም አይበቃንም። ዋና ቁም ነገሩ ታሪክ ከሚያወሩት ሳይሆን ታሪክ ለመስራት ከቆረጡት ጋር መስለፉ ላይ ነው ።

ይህን ሁል ያነሳሁት ሴቶቻችንን ወደ ትግሉ ተሳትፎ እንዲመጡ ለማበረታታትና በትግል ላይ ያሉትንም በርቱ ተበራቱ ለማለት ነው። ለመንደርደሪያ ያክልም የኛዎቹን ባለታሪክ ዮዲት ጉዲትን ብናነሳ በዘመኑ በተከናወነው የውትድረና መስክ በቆራጥ የጦር መሪነት ችሎታቸው በዘመኑ ለነበሩት ለ እነ ስብለ ውንጌልና ንግስት እሌኒ በመልካም አራአያነታቸው በታሪክ ተጠቃሸ ለመሆን አብቅቷቸዋል።

በተለይም እቴጌ ጣይቱ ከ 1851 – 918 እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ያደርጉት አስደናቂ ስራቸው ለዛሬው እህቶቻችን ልዩ ብርታት ይሆናል ብዬ አምናላሁ። ያንንም ታሪክ እንዲያነቡ አበረታታለሁ። ምንም እንኳን ብዙዎቸ እንደሚሉት አንዳንዱ ታሪክ የዘመናቱ ጉዳይ ባንዳንድ ጥቃቅን ምክነያቶቸ ጥያቄውስጥ ቢወድቅም ቅሉ እውነታውን ግን ለጥያቄ የሚያቀርብ ማንም የለም።

የኛዋ ጀግና ባለታሪክ እቴጌ ጣይቱ ቡጥል ለአራት ግዜ ትዳራቸውን ፈተው ቢኖሩም በፍቺ ምክነያት ሞራላቸው ወድቆ ገለል አላሉም። በጠንካራው ሞራላቸውና በሰፊው እይታቸው ጀግናውን ባለታሪክ ሚኒሊክን አግበተው የጀግነነት ተግባራቸውን ቀጠሉ እንጂ። በቆዩበት ዘመናትም ህይወታቸው እስካለፈበት እስከ ጥቅምት 11 1918 እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ድረስ አስተዋይነታቸውንና የጠላትን ሴራ መርመሮ የማወቅ ቸሎታቸውን አስመስከረዋል። ተመሳስሎና አስመስሎ ባድርባይነት የሚስማራውን ሳይቀር በመመንጠር በሚስጡት ምክርና የጀግነነት አቆማቸው በታሪክ ሲዘከሩ ይኗራሉ።

ዛሬም በትግሉ ውስጥ ተሰማርተው የበኩላቸውን ድርሻ በታማኝነትና በጀግንነት እያበረከቱ ለሚገኙት እህቶቼ የነዚሀ ባለታሪክ ጀግኖች እህቶች ታሪክ የናንተም ታሪክ ነውና በርቱ እላለሁ። እናንተም ለሌሎቸ መልካም ምሳሌ በመሆን በቆራጥነት ለዛሬው የነፃነት ትግላችን እንደሻማ እየበራችሁና እግዚአብሄር በሰጣችሁ ማስተዋል በመደገፍ በምንም በማንም አይነት ምክነያት ሞራላችሁ ሳይነካ በቆራጥነት ግፉበት እላለሁ።

ለመሆኑ የሴቶች እህቶቻችን የትግል ተሣትፎ እንዴት ይበረታታል ?

* አዎ በታሪካችን ሴቶቸ እህቶቻችን በጓዲያም ባደባባይም የሄነው የማይባል ተጽዕኖ እንደሚደርስባቸው ይታወቃል። በዚሀም ምክነያት የበርካታ እህቶቻችን እውቀትና ችሎታ ወደትግሉ መስክ ሊወጣ ቀርቶ፤ ወደማህበረስቡ እንዳይቀርቡም አድርጓል። በትግሉም መስክ ጎልቶ እንዳይታይ ሆኗል። ዛሬ ግን ተግባራዊ እንዲሆነ የማድረግ ሃላፊነት በውንዶች ታጋይ ወንድሞቻችንም ላይ የወደቀ ነው እላለሁ።
* እንዴት በትሉኝ ከጓዲያ ወደ አደባባይ እንዲወጡ በማደርግ። ሞራላቸውን በመጠበቅም ሆነ ሞራል በመስጠት ከፍተኛ ድጋፍ እያደርገን እውቀታቸውንም ሆነ እይታቸውን በተለይም ምክራቸውንም ተቋዳሽ በመሆን ተሳትፎአቸውን ማጎልበት አንዱና ከበርካታው በጥቂቱ ነው።

* በታሪክ እንደምናውቀው “ሁልጊዜ ከመልካምና ውጤታማ ከሆኑ ወንዶች ጀርባ ጠንካራና አስተዋይ ሴቶች አሉ”። እየተባለ እንደሚነገር ፤ ወንዶች እነሱ ብቻ ወጤታማ ለመሆን ከመሸቀዳደም በመታቀብ ሴቶቻቸውም ውጤታም አንዲሆኑ በማድረግ ሃላፊነትን በመውሰድ ማበረታታት ተገቢ እርምጃ ነው። ለዚህ ታላቅ ምሳሌ የሚሆነን ለሃያ እረጅም አመት ባደርገነው የነፃነት ትገል አሉ የሚባሉት የፖሎቲካ ድርጅቶቸም ሆነ ሲቬክ ማህበራት ዋናዎቹ ናቸው።

* አሁንም እንደምናየው ባለመቻቻሉም፤ በመጎነታተሉም የሚታየው የወንዶች ግንባር ቀደም የመሪነት ሚና በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል ። ለሴቶች ጀግኖች እህቷቻችን የመሪነትን ሚና እንዲጫወቱ ብናበርታታና እድሉን ብንሰጣቸው መልካም አይሆንም ትላላችሁ ? – መልካም አስተዳደራቸውንም ሆነ እይታቸውንና የማስተዋል ብቃታቸውን በጥቂቱም ቢሆን አይተናል። በመሆኑም እድሉን እንዲቀዳጁ ሞራል በመስጠት በበር ላይ የቆምን ወንዶቸ በሩን በመክፈት ግቡ ማለትም አንዱ ማበረታቻ መንገድ ነው።

* ቅዱሳን መጸሃፍትም (በምሳሌ 3፡ 19) እንዲህ ይላል“እግዚ አብሔር በጥበብ ምድረን ፈጠረ በማስተዋልም ስማይን በ አንድ ቦታ አጸና”። በተለያየ ክፍልም ሴቶች ማስተዋል እንዳላቸውም አስረግጦ ይናገራል። ለጸናና ውጤታም ሊሆን ለሚገባው የነፃነት ትግላችን፤ የ እህቶቻችን አስተዋይና ቆራጥ አመራርን በማበረታታትና ወደ መሪነት እንዲመጡ የማድረገን ሃላፊነት ወንዶች እንውሰድ። ኢትዮጵያዊያን እጅ ለእጅ እንድንያያዝና ትግላችንን በጽናት እንድንታገል አበርታተን ወደፊት እናውጣቸው እንጂ አንግፋቸው ።

* በመጨረሻም በውስጥም በውጭም እስካሁንም ቆራጥነታቸውንና የአስተዋይ አመራር ብቃታቸውን ላሳዩን እህቶቼ ያለኝ ክብር እጅግ የላቀ እንደሆነ ሳላወሳ አላልፍም። ታሪከም ይዘክራቸዋል እላለሁ። እሁንም ደረጃው ከፍ ይበለም ዝቅ፤ በተለያየ ሁኔታ ለሚያደርጉት የትገል ተሳትፎ ክበር ልነሰጣቸውና ልናበረታታቸው ይገባል ። ወደፊትም ወጥተው የመሪነቱን ስፍራ እንዲይዙ አይዞአችሁ በማለት በርቱ ተበራቱ እላለሁ። ወንዶችም አይዞአችሁ፤ አንዳንዴ ሴቶቻችንን ማስቀደም ለመልካም ውጤት ያበቃናልና ልባቸንንም የዘጋነውን በራችንንም በመከፈት እናበረታታ እላለሁ።

እግዚአብሔር ሁላችንንም ልቦና እን ማስተዋል ይስጠን የነፃነት ጮራም ከፊታችን ነው። !