የአረና ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ አስራተ ብርሀን ታሰሩ

የአረና ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ አስራተ ብርሀን ዛሬ ጥር 21 2003 ዓ.ም በመቀሌ ከተማ የመንግስት ጸጥታ ሀይሎች በቁጥጥር ስር እንዳዋሏቸው ተገለጸ፡፡

የወቅቱ የመድረክ ሊቀመንበርና የአረና ትግራይ ለሉአላዊነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ገብሩ አስራት እንዳስታወቁት አቶ አስራተ ሊታሰሩ የቻሉት መንግስት የአረና ፓርቲን ለማፍረስ ሲያካሂድ የነበረውን ህገ ወጥ ድርጊት ለማክሸፍ ባደረጉት ጥረት ምክኒያት ነው፡፡

እንደ አቶ ገብሩ ገለጻ ገዢው ፓርቲ ያደራጃቸውና በተለያዩ ጊዜያት ከፓርቲው የተባረሩ ግለሰቦች ህዝቡን ለማደናገር በአረና ስም ስብሰባ መጥራታቸውን የተረዱት አቶ አስራተ የስብሰባውን ህገወጥነት የሚገልጽ ማስታወቂያ በመለጠፋቸውና ገዢው ፓርቲ የሸረበውን ሴራ በማክሸፋቸው ለእስር ተዳርገዋል፡፡

የአካባቢው ፖሊስ ሀላፊዎች በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን ለማድረግ ያደረግነው ጥረት ስልካቸው ሊነሳ ባለመቻሉ አልተሳካም፡፡