የቱኒሲያውን ሕዝባዊ ለውጥ፤ ለኢትዮጵያ ያለው እንድምታ እና የኢሣት ሚና

በቅርቡ በቱኒሲያ የተካሄደው ሕዝባዊ ለውጥ አገሪቷን ለ23 ዓመታት በአምባገነናዊ አገዛዝ ቀንበር ሥር ሲገዙ የነበሩትን ዚኔ ቤን አሊ ከሥልጣን ማስወገዱ በሌሎች የአፍሪካና እና የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ሕዝባቸውን በመርገጥ ለዘመናት በሥልጣን ላይ ተንሰራፍተው ለሚገኙ አምባገነኖች ጭንቀትንና ፍርሃትን እያስከተለባቸው መሆኑ እየታየ ነው፡፡ በተለይም በአፍሪካ ይህ የለውጥ ማዕበል ከቱኒሲያ እስከ ዚምባቡዌ እንዲሁም ከሞሪታኒያ እስከ ኢትዮጵያ እየተዳረሰ የመሄዱ ዕውነታ በርካታዎቹን የአፍሪካ አምባገነኖች ዕረፍት እየነሳቸው መጥቷል፡፡ ከዚህም ሌላ ይህ በምንም ሊገደብ የማይችል ማዕበል ማቆሚያ እያጣ በአፍሪካ አገሮች ግብጽ፣ አልጄሪያ፣ ሞሪታኒያ እንዲሁም ከአፍሪካ ውጪ አልባኒያንን እና የመንን እያዳረሰ መጥቷል፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ወደ ኢትዮጵያ መንፈሱም አይቀሬ ነው፡፡

የዚህ ለውጥ ተላላፊነት ካሸበራቸው አምባገነኖች አንዱ የሆነው የአቶ መለስ አገዛዝ ምንም እንኳን ሕዝባችንን በፍርሃት ሸብቦ ከውጪ ደግሞ ‹‹ወዳጆችን›› አሰባስቦ ሥልጣኑን ለማራዘም የሚቻለውን እያደረገ ቢሆንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን በ1997 ምርጫ በተለይ በመስቀል አደባባይ ያሳየውን ሕዝባዊ ንቅናቄ አማራጩ ከተመቻቸለት በሌላ መልኩ ለመድገም ብቃቱ እንዳለው እኛ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ የምንገኝ ሙሉ እምነታችን ነው፡፡ ከዚህም አልፎ እኛ ኢትዮጵያውያን የወደፊት አቅጣጫችን በአምባገነኖች የሚዘወርና እነርሱ በሚፈልጉት መስመር የሚመሩት ብቻ ሳይሆን ይህ የለውጥ ማዕበል እኛ ወደምንፈልገው አቅጣጫ እንዲነፍስ ማድረግ እንደምንችል ንቅናቄያችን በጽኑ ያምናል፡፡ ይህንን ከምናደርግባቸው መንገዶች አንዱ ምናልባትም ቀዳሚውን ሥፍራ ሊሰጠው የሚገባው የኢትዮጵያ ሣተላይት ቴሌቪዥንን – ኢሣትን በመደገፍ ነው፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያንም ምዝበራ፣ ጭከና፣ ሙስና፣ አፈና፣ ግድያ፣ ወዘተ በሰፈነበት በአምባገነናዊ አገዛዝ ለሁለት ዓሥርተ ዓመታት መገዛታችን ከቱኒሲያውያን ጋር ከሚያመሳስሉን በርካታ እውነታዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በተለይ ባሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚታየው የምግብ ዋጋ እስከ 60% መናርና ይህንንም ተከትሎ የዋጋ ግሽበት መከሰቱ ሊያስከትል የሚችለውን ሕዝባዊ ዓመጽ ያስፈራው የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ የአቅርቦትን መጠን በመጨመር ችግሩን በፖሊሲ ደረጃ ከመዋጋት ይልቅ በሕዝቡና በነጋዴው ኅብረተሰብ መካከል መከፋፈል እንዲፈጠር የችርቻሮ ሸቀጦች የዋጋ ተመን በማውጣት ለሕዝብ ተቆርቋሪ መስሎ ለመታየት የሚያደርገውን የማስመሰያ ተግባር ማንም የሚዘነጋው አይደለም፡፡ይህንንም የዋጋ ተመን ድንጋጌ አስፈጽማለሁ እያለ በርካታ ሱቆችን በመላው አገሪቷ በማሸግ የሕዝቡን መከራ እያባሰ ይገኛል፡፡ ታዲያ ይህ መከራ ያንገፈገፈው ሕዝብ ገንፍሎ ሲወጣወደከፋ አቅጣጫ እንዳይሄድ መዘጋጀት አይገባንም ወይ?

ምንም እንኳን በእያንዳንዱ አገር የሚከሰተው ለውጥ ራሱን የቻለ ልዩ ይዘት ቢኖረውም ከቱኒሲያው ለውጥ ከምንማራቸው በርካታ ነገሮች መካከል ቁልፍ የሆኑትና እያንዳንዱን ዜጋ የለውጥ ሐዋሪያ አድርገን ልናሰልፍበት የምንችልባቸው ሦስት መሠረታዊ መመሪያዎች መገናኘት፣ መደራጀት እና መተባበር እንደሆኑ የንቅናቄያችን ዕምነት ነው፡፡

1. መገናኘት

በቱኒሲያ ለተከሰተው ለውጥ እንደምክንያት ከሚጠቀሱት አንዱ የሥራአጥነት ቁጥር እጅግ መጨመርና ይህንንም ተከትሎ በሕዝቡ ዘንድ የተፈጠረው የኑሮ ውድነት ያስከተለው ምሬት ቢሆንም አገዛዙ እጅግ ከፍተኛ ጫና በማድረግ የሕዝቡን ግንኙነት ለማፈን ቢሞክርም ሕዝቡ ግን እንደ ፌስቡክና ትዊተር በመሳሰሉት ዘመናዊ የመገናኛ መንገዶች በመገናኘቱ የለውጡን ሂደት ሊያፋጥን ችሏል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የአቶ መለስ አገዛዝ ሕዝባችን መረጃን ሊያገኝ የሚችልበትን ቀዳዳ ሁሉ በመድፈን የራሱን ፕሮፓጋንዳ ብቻ እየነፋ ይገኛል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የአፈና ተግባር ኢትዮጵያውያንን ከምንግዜውም በበለጠ ሌሎች የመገናኛ መንገዶችን እንዲጠቀሙ የሚያስችላቸውን ዕድል እየፈጠረ ይገኛል፡፡ በዚህም ዋነኛ ተጠቃሾቹ፡-

o የኢትዮጵያ ሣተላይት ቴሌቪዥን (ኢሣት) በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ እያቀጣጠለ ያለው እሳት በመላው አገራችን እንዲቀጥል ማድረግ አንዱ ኃላፊነታችን ነው፡፡ ከዚህም አኳያ ኢሣት ሰሞኑን ያወጣውን የገንዘብ ማሰባሰብ ተማጽንዖ ንቅናቄያችን የሚደግፈው ተግባር ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በቸርነት በመለገስ ከቃል ያለፈ ዕርዳታውን በገንዘብ በመርዳት የኢሣት ፕሮግራም ያለማቋረጥ እንዲተላለፍ ማድረግ አለበት፡፡ የቱኒሲያውን ለውጥ በተግባር ለመፈጸም የተጀመረው የለውጥ ማዕበል ኢትዮጵያንም በድጋሚ እንዲያጥለቀልቃት እንደ ኢሣት ያለ የሚዲያ ውጤት ነው ግንኙነት ሊፈጥር፣ የተፈጠረውም ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ የሚችለው፡፡ ‹‹ኢሣትን በመደገፍ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ለመታደግ›› እንዲሁም የማያቋርጥ የመገናኛ መስመር ማድረግ አሁኑኑ እንችላለን፡፡http://www.ethsat.com/
o ሬዲዮ፣ ጋዜጣ፣ ፌስቡክ፣ ስካይፕ፣ ትዊተር፣ ፓልቶክና ድረገጾች በፍጥነት መልዕክቶችን በማስተላለፍ በኩል ያላቸውን አገልግሎት መዘንጋት እንደሌለብን ድርጅታችን ያምናል፡፡ በአንዱ በኩል ያልተቻለውን በሌላው የቴክኖሎጂ እሴት በመጠቀም የመገናኛ መስመሩን በማዳበር መረጃ የተጠማው ሕዝባችንን ልንደርስለት እንችላለን፤ በዚህም የመረጃ ፍሰቱ ወቅታዊ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል፡፡
o የስልክ ጥሪዎችና የኢሜይል መልዕክቶች ያላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽዖ መዘንጋት የለብንም፡፡ ከቤተሰቦቻችን እንዲሁም አገር ቤት ካሉ ወዳጆቻችን ጋር በስልክ በመገናኘትና አጫጭር ኢሜይል በመላክ የመገናኛ መስመሩ ፈጽሞ እንዳይቋረጥ በማድረግ ሕዝባችንን ማበረታታት እንችላለን፡፡

2. መደራጀት

እንደዚህ ዓይነት ለውጥ ለማምጣት እንዲቻል ከሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮች ሌላው ወሳኝ ተግባር መደራጀት ነው፡፡ መደራጀት ሲባል ሕዝብን በየመንገዱ የተቃውሞ ሰልፍ እንዲያደርግ ከማስተባበር በጣም ለላቀ ተግባር ማዘጋጀት ማለት ነው፡፡ በቱኒሲያ ለጥቂት ቀናት የተደረገው ሕዝባዊ ዓመጽ ቤን አሊን ከሥልጣን ለማስወገድ ቢችልም ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ የተከሰተው የሥልጣን ክፍተት አገሪቷን አለመረጋጋት ውስጥ እንትወድቅ ሊያደርግ እንደሚችል የብዙዎች ፍራቻ ነው፡፡ ለውጥ ቢመጣም አለመደራጀት የሚፈጥረው ችግር ምን እንደሚሆን ትልቅ ትምህርት ሊሰጠን የሚገባ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ለዓመታት ተንሰራፍቶ ያለውን የአንድ ፓርቲ፣ የአንድ ጎሣ አምባገነናዊ አገዛዝ በሕዝባዊና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ለመተካት ከሁሉም ወገን የተውጣጡ ኢትዮጵያውያንን ያቀፈ የሽግግር አመራር መመሥረት አንዱና ዋነኛ የመደራጃ መንገድ ነው፡፡ ይህንንም በጥንቃቄ ዕቅድ በማውጣትና በቂ ዝግጅት በማድረግ መመሥረት የሚቻል ሲሆን ለተግባራዊነቱም የምንጠቀምባቸው ስልታዊ ምንጮች ከውጪ ብቻ ሳይሆን ከአገር ውስጥ እንዲያውም ከራሱ ከህወሃት/ኢህአዴግ ውስጥም እንዳሉ ልንገነዘብ ይገባናል፡፡ ከአገዛዙ ከፍተኛ አመራር እስከ ደኅንነት፣ ወታደራዊና ፍትህ አካላት ውስጥ ያሉ በልባቸው ፈጽሞ የህወሃት/ኢህአዴግን አገዛዝ የሚቃወሙ ሆኖም ግን ሁኔታዎች ተመቻችተው የተደራጀ ሕዝባዊ ለውጥ ሲመጣ ለመቀላቀል የተዘጋጁ የነጻነትና ፍትሕ ፈላጊዎች ቁጥር ጥቂት አይደለም፡፡ በቱኒሲያ ሕዝባዊው ለውጥ ንቅናቄ ሲያደርግ ወታደራዊው አካል ቀጥሎች የደኅንነት አመራሩ የለውጡ አካል እየሆኑ እንደመጡ በግልጽ የታየ ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ ልናስተባበር የምንችለው መደራጀት ስንችል ብቻ ነው፡፡

3. መተባበር

በአሁኑ ጊዜ ነጻነታቸውን እየተጎናጸፉ ያሉ አገሮች ይህንን ተግባር ለመፈጸም የቻሉት ብቻቸውን ሳይሆን ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው የተለያዩ ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ ወዘተ ጋር በመተባበር እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ እኛ በውጪ የምንኖር ኢትዮጵያውያን በምንገኝባቸው አገራት የነጻነትን ምንነት እና ጣፋጭነት ቀምሰናል፡፡ በአገር ቤት ያሉት ወገኖቻችን ግን ነጻነትን በነጻ ሳይሆን ዋጋ በመክፈል የራሳቸው ለማድረግ ቁርጠኝነታቸውን በተደጋጋሚ አረጋግጠዋል፡፡ እኛ በውጪ ያለነው እርስበርስ በመተባበር እንዲሁም ይህንን ትብብራችንን ወደ ኢትዮጵያ በማዝመትና እዚያ ካሉት ጋር በመቀናጀት ነጻነትን የራሳችን ማድረግ ካልቻልን ለእኛ ነጻነት ዋጋ የሚከፍልልን ሌላ ማንም ሊኖር እንደማይችል ልንገነዘብ ይገባናል፡፡ ሁላችንም ተገቢውን መስዋዕትነት ለመክፈል ሳንዘጋጅ ሌላው የበለጠውን እንዲከፍል ስንጠበቅና ስንመከኛኝ ዘመናትን አሳልፈናል፡፡ ነጻነትን ለማግኘት አንዱ ለብቻው ከብዙሃኑ ተነጥሎ በግሉ የሚሠራው አይደለም፡፡ ወይም ሥራውን ሁሉ ለሌሎች ትቶ የነጻነትን ፍሬ ለመረከብ በተስፋ የሚጠብቅብም አይደለም፡፡ መተባበር ማለት የእያንዳንዱ ተግባር ለሁሉም የሚሆንበት፤ የሁሉም ተግባር ለእያንዳንዱ የሚከፋፈልበት ነው፡፡ በዚህ መንፈስ ካልተንቀሳቀስን ከመተባበር ይልቅ ጣት በመጠቋቆምና እርስ በርስ መካሰስ እንኳንስ ሌላውን ነጻ ልናወጣ ይቅርና ለራሳችንም የነጻነት ትርጉሙ እየጠፋብን ይሄዳል፡፡

በመተባበር የሚደረገው ንቅናቄ ለአንድ ጎሣ ወይም ነገድ ነጻነት ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ኢትዮጵያውያኖች እንድንቆም የሚያስተሳስረንን የዓላማ አንድነት ይፈጥራል፡፡ ይህ ሲሆን እያንዳንዱ ግለሰብ የኢትዮጵያን ካርታ ሲመለከት የሚያየው የራሱን ጎሣ ወይም ብሔር ሳይሆን መላውን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ስለሚሆን ከሌሎች ጋር ተባብሮ እንዳይሠራ ያደረገውን አስተሳሰብ ወደጎን በመተው ‹‹አንበሳ ሊያስር የሚችለው ድር እንዲያብር›› የራሱን አስተዋጽዖ በማድረግ መተባበር ይጀምራል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በርካታ ኢትዮጵያውያን ንቅናቄያችን እያደረገ ያለውን ሥራ በመደገፍ የተለያዩ መልዕክቶችን ይልኩልናል፡፡ ከመልዕክቶቹም ጋር ‹‹ለማድረግ የሚጠበቅብኝን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ›› የሚል መልዕክትም ታክሎበት ይደርሰናል፡፡ እንዲህ ያለው ማበረታቻ እጅግ ጠቃሚ የመሆኑን ያህል ተግባራዊ ደግሞ እንዲሆንም እንፈልጋለን፡፡ ስለዚህ የሚቻላቸውን ትብብር ለማድረግ ለሚፈልጉት እነዚህ ደጋፊዎቻችን የምናቀርብላቸው ተማጽንዖ ‹‹ኢሣትን ደግፉ›› የሚል ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ከመተባበሪያ መንገዶቹ አንዱ በመሆኑ ውጤታማ ሥራ እንዲሠራና ለውጥ እንዲመጣ አሁኑኑ እንተባበር፡፡

እስካሁን አንድን ብሔር ለመታደግ ‹‹የነጻ አውጪ›› ትግል በኢትዮጵያ ሲካሄድ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አሁን ግን ይህ ትግል ሰብዓዊነትን ነጻ ለማውጣት ወደሚደረግ ‹‹ሕዝባዊ ለውጥ›› እንደሚለወጥ በገሃድ እየታየ ያለ ተግባር ነው፡፡ ፈጣሪያችንን በእውነትና በመከባበር ቅን የሆነውን መንገድ ለመከተል ስንሻው አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመመሥረት የሚያስችለንን የዓላማ አንድነትና ትብብር ይቸረናል፡፡ ይህም ከጠበብንበት የዘር ሳጥን እንድንወጣ ከማድረግ አልፎ ያለ ሁላችንም ነጻነት የነጠላ ነጻነት ዋጋቢስነትን እንድንረዳ ያደርገናል፡፡

የለውጥ ንፋስ በየአካባቢው እየነፈሰ ነው፡፡ ለተግባራዊነቱ ምን ያህል ዝግጁ ነን?

(ለዚህ ደብዳቤ ምላሽም ሆነ ለተጨማሪ መረጃ ዋና ዳይሬክተሩን ለአቶ ኦባንግ ሜቶ ([email protected]) በመጻፍ ወይም ድረገጻችንን (www.solidaritymovement.org) በመጎብኘት ለመረዳት ይችላሉ፡፡)