ሰላማዊ ትግል ወይስ ሰላማዊ እንቅልፍ
ከበልጅግ አሊ
ስለ እንቅልፍ ከተነገሩ የዘመኑ ቀልዶች ሁሉ የሚያስቀኝ ቀልድ አለ ።የፖለቲካ ቀልድ የሚያውቁት መረራ ጉዲና የዛሬውን አያድርገውና “የተከበሩ” ተብለው የወያኔ ፓርላማ ውስጥ ገብተው ነበር ። እንደሚታወቀው የወያኔ ፓርላማ በወያኔ አባሎችና ደጋፊዎች የተሞላ ነበርና የአንድ የወያኔ የፓርላማ ተወካይ ሲናገር ሌሎቹ በማጨብጨብ ጊዜያቸውን ያጠፉ ነበር። በዚህ አሰልቺ በነበረው ፓርላማ ውስጥ የሚገኙ ተቃዋሚ ነን የሚሉትም ጊዜያቸውን በአዳራሹ ውስጥ በማዛጋትና አልፈውም በእንቅልፍ ያሳልፉት ነበር ።የተከበሩ መረራ ጉዲና በዛ ወቅት የፓርላማው ተመራጭ ነበሩና በፓርላማ ውስጥ በእንቅልፍ ጊዜያቸውን ያጠፉ ከነበሩት በዋነኛነት ይታሙ ነበር። አንድ ይህንን የተከታተለ ተንኮለኛ ጋዜጠኛ “እንዴት ነው እንቅልፉ?” ብሎ ይጠይቃቸዋል። ፕሮፌሰሩም በደንብ ስላልተኙ ተናደው “እነዚህ ወያኔዎች ለሆነው ላልሆነው እያጨበጨቡ ምኑን ያስተኛሉ” አሉ ይባላል ።እውነታቸውን ነው የሕዝብ ገንዘብ እየተከፈለን መተኛት እስከቻልን ድረስ ለምን መረበሽ ያስፈልጋል? ለሕዝብ መታገልስ ለምን ያስፈልጋል?
ሕዝብ መርጦት ፣ ለሕዝብ ይሠራል ተብሎ ጥቅሙን ሲያገኝ እያንቀላፋም ደሞዙን መላጥ የተለመደ ነው። የድሮ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፓርላማ አባል አንድ የማይረሳ ግጥም ትተው አልፈዋል። የዛን ዘመን ፓርላማ ተመራጮች ደሞዛቸው ሰባት መቶ ሃምሳ ስለነበር እንዲህ ብለው ገጠሙ፡-
እኛ ምን አገባን ለሕዝቡ ጫጫታ፣
ሰባት መቶ ሃምሳ ይምጣ በልደታ ።
በዛሬው ፓርላማም ከወያኔ አባላት በስተቀር ማንም ሌላ ተቃዋሚ ስለሌለበት ቢተኙም ባይተኙም ልዩነት የለውም። ፓርላማውንም ዘግተውት ቢሄዱም እንኳ ልዩነት የለውም። መለስ በግሉ የሚወስነውን ለማጽደቅ መሰብሰብም አያስፈልግም። የራሳቸውን ድምጽ እራሳቸው እየሰሙ የሚደሰቱበት፣ ጮቤ የሚረግጡት እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ ፓርላማ ምንም አይጠብቅም።
በጣም የሚያሳስበው ግን በእንደዚህ ዓይነት ፓርላማ ውስጥ ተቃዋሚዎች ለመሳተፍ የሚያደርጉት ጥረት ነው። ወያኔ እስካሁን ባቋቋማቸው ፓርላማዎች የፈጠረውን ሁኔታ ሕዝብ ልቅም አድርጎ ያውቀዋል። የወያኔ ምርጫና ዴሞክራሲ ምን ማለት ምን እንደሆነም በደንብ ተረድቶታል። ይህ ለምዕራብያውያን ተብሎ የሚዘጋጅ የቴያትር ፓርላማ ውስጥ ከያኒ ለመሆን የሚደረገው ጥረት በግል ጥቅምና ወያኔንን ዴሞክራት ከማስባል ባሻገር ለሕዝብ የሚፈይደው ምን እንደሆነ መረዳት አያዳግትም። ሕዝብ እየተበደለ ፣ምርጫ እየትጨበበረ እስከመቼ እንደሚቀጥል የሁላችንም ጥያቄ ነው። እንደዛም ሆኖ ግን ተቃዋሚዎች በምርጭው መሳተፋቸው አይቀርም። ይህ በምርጫ መሳተፍ ወያኔን ዴሞክራሲያዊ አስመሰለው እንጂ ተቃዋሚዎቹን እውነተኛ ተቃዋሚ አላደረጋቸውም ፣ ወደፊትም አያደርጋቸውም።
በምርጫ መሳተፍ አንዱ የሰላማዊ ትግል መልኩ ነው ። ግን እሱ ብቻ አይደለም ሌሎችም አሉ። ሰላማዊ ትግል ማለት መሣሪያ ማንሳትን አያካትትም እንጂ በዛ ያሉ ቅርንጫፎች አሉት ። ረሃብ አድማ ፣የሥራ ማቆም አድማ ፣ ሰላማዊ ሰልፍ፣ ወዘተ። በምርጫ አልሳተፍም ብሎ ማመጽም የሰላማዊ ትግል አንዱ ገጽታ ነው ።የኛ ሀገር ሰላማዊ ታጋዮች እነዚህን ከላይ የጠቀስኳቸውንና ሌሎችንም የሰላማዊ ትግል አይነቶች በአሁኑ ጊዜ እያደረጉ ነው? ይህንን ጥያቄ ሁላችንም ልናጤነው ይገባል። ሰላማዊ ትግል እየተካሄደ ነው ወይስ አይደለም?
ፕሮፌሰር መስፍን ብርቱካን ሚደቅሳ የተፈታች ሰሞን በፓልቶክ ክፍል ቀርበው “ሰላማዊ ትግል ገና መች ተጀመረና” ብለው ሲሉ ሰማኋቸው ። ለነገሩ ይህንን ዓይነት ሃሳብ የሚያቀርቡት እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ብዙዎቹ የሰላማዊ ትግል ደጋፊዎች ጭምር ናቸው ። እንዲያውም አንዳንዶቹ የሰላማዊ ትግል ደጋፊዎች የሁለገብ ትግልን በተለይም የመሣሪያን ትግል መቃወም ፣ ማጣጣል የሰላማዊ ትግል ዋነው ዓላማ የሚመስላቸው አይጠፉም። በዚህም ምክንያት በየቀኑ በየፓልቶኩና ፣ድረ ገጹ በመሣሪያ የሚታገሉትን በአገኙት ዘዴ ሁሉ ሲያጣጥሉ እናያለን ። አንዳንዶቹም አልፈው ተርፈው ከወያኔ መዋደጃ ሲያደርጉት የታየበት ሁኔታ ብዙ ነው ። ለመሆኑ ይህ ተሰፋ የተጣለበት ሰላማዊ ትግል መቼ ነው የሚጀመረው ? ሰላማዊ ትግል ወይም በምርጫ መሳተፍ ማክተሙን ላለማመን የሚደረግ ጥረት ነው ወይስ እውነትም ገና አልተጀመረም?
ደብረ ማርቆስ አልተሻሻለችም ለማለት ንጉሥ ተክለ ሀይማኖት ዛሬ ከሞት ቢነሱ ምንም ለውጥ አያዩባትም ይባላል። ማለትም እርሳቸው ከነበሩበት ወቅት ብዙም አልተሻሻለችም ለማለት ነው ። እነ ፕሮፌሰር አሥራትም ፣ እነ ተስፋዬ ታደሰም ፣ እነ አሰፋ ማሩም፣እነ ሽብሬ ደሳለኝና ሌሎቹም ዛሬ ከመስዋዕትነታቸው ቢነሱና ሰላማዊ ትግሉ አልተጀመረም እያሟሟቅን ነው ቢባሉ ከኛ ከሙታን ምን ተሻላችሁ ? ብለው እንደሚጠይቁን አልጠራጠርም። እነርሱ በሰላማዊ ትግል ታግለው( ሌላ እስካልተባለ ድረስ) በወያኔ ግፍ ተገድለዋል ። ለእነርሱ የመጨረሻ የሆነውን ህይወታቸውን ከፍለው አልፈዋል። ይህንን ክደን ሰላማዊ ትግል ገና አልተጀመረም ስንል ምን ይሰማን ይሆን ? ሰላማዊውን ትግል ለመጀመር ምን እየጠበቃችሁ ነው ብንባልስ ? አልተጀመረም ብለን ስንክድ ሁኔታውን ለማካበድ ነው እንጂ እውነቱ ጠፍቶን አይደለም።
እውነት ነው ለብዙዎቹ ሰላማዊ ትግል አልተጀመረም ለሚሉት የተጀመረው ሰላማዊ እንቅልፍ ነው። አንድ ሰሞን ምርጫን አስደግፎ የተሟሟቀው ትግል የበጋውን ሙቀት እንደሚጠብቅ በረዶ ረግቶ ያለበት ሁኔታ እየተመለከትን ነው። ከ2002 ዓ. ም. ምርጫ በኋላ እነዚህ ሰላማዊ ፖለተከኞች መስማት አቁመናል። እንኳን ሰለማዊ ሰልፍ ፣ እንኳን የሥራ ማቆም አድማ ፣ እንኳን አመጽ የነበሩት ድርጅቶችም እየተከፋፈሉ፣ መሪዎቻቸውም እየተደበቁ በሰላማዊ እንቅልፍ ላይ ናቸው ያሉት ። አንዳንዶቹም ከመንግሥት ጋር የሚያቃርናቸውን ወይም የግል ጥቅማችን የሚነካ ምንም ነገር ማንሳት አይፈልጉም ። በሌላ አነጋገር ተኝተዋል ። ሰላማዊ እንቅልፍ ላይ ናቸው ። በምርጫው ዘመን እንሰማቸው የነበሩት ስሞች በሙሉ ዛሬ ጥፍት ብለዋል ። በዚያው የሚቀሩ ግን አይመስለኝም ። እንደገና አምስት ዓመታትን ጠብቀው እንደ ረጋው በረዶ በበጋው ሙቀት ሊቀልጡ ለሌላ ምርጫ ብቅ ይላሉ ። እንደገናም ይሸነፋሉ ። እንደገና ወደ እንቅልፋቸው ያዘግማሉ።
የሰላማዊ ትግል እንደ ቢራቢሮ የሕይወት ዘመን (Metamorphosis) ምርጫ ሲያልፍ መደበቂያ ውስጥ ተገብቶ የሚደበቁበት ፣ ምርጫ ሲደርስ የሚራወጡበት ብቻ መሆን የለበትም ። ትግሉ የቀን ተቀን እንቅስቃሴን ይፈልጋል። የወያኔ መንግሥት ወደደም ጠላም ጥያቄዎችን እያነሱ ማፋጠጥ ፣እንቢኝ ብሎ መታሰርም ፣ መገደልም ይኖራል።
ከእስር ለመሸሽ ሲባል አቋምን እየለዋወጡ ወይም መሪያቸው ሲታሰር እየተከፋፈሉ ለሥልጣን እየተጣሉ የሰላማዊ ትግል አልተጀመረም ወይም ገና መች ተካሄደና ማለት ምንም አይጠቅምም ። ይህ የሰላማዊ ትግል መች ተጀመረና የሚለው መፈክር የሚገርም ነው።ሰላማዊ ትግል ማለት በየምርጫው መሳተፍ ብቻ ይመስል በየማሃሉ ዝምታና ፀጥታ እየሰፈነ የሚደረገው ማዝገም፣ በምርጫ መካከልም ከወያኔ የሚገኘውን ጥቅማ ጥቅም ማግበስበስ በሕዝብ ዘንድ ተአማኒነትን አሳጥቷል ። በዚህ አይነት ዝግሚያ የተኛ ሰላማዊ ታጋይ እንቅልፉን ይጨርስ እንደሆን ነው እንጂ ሰላማዊ ትግሉን እንደሆነ ካለበት አይነቃነቅም ።ምንአልባትም በዚህ የፀጥታ ጊዜ ለአንዳንዶቹ ኪሳቸውን ያሳብጥ እንደሆን እንጂ ትግሉን እያፋፋመ የወያኔን አገዛዝ እያዳከመ አይደለም።
በሃገራችን የሰላማዊ ትግል ገና አልተጀመረም እየተባለ ስንት አመት ልንጠብቅ ነው? ጎበዝ እነዚህ ሰላማዊ ታጋዮች ምርጫ ሲደርስ በየፓልቶክ ክፍሉ እየተጠሩ ቃለ መጠይቅ ማድረግ ብቻ አይበቃም ። ዛሬውኑ እነዚህ የተኙ መሪዎች ተጠርው በየፖልቶክ ክፍሉ ፣ በሬዲዮና በጋዜጣም አቋማቸውን ከወዲሁ ግልጽ እንዲያደርጉ መጣር ይኖርብናል። መጠየቅ ይኖርባቸዋል ። ለታሪክ የሚመዘገብ ሰነድ ሊያዝ ይገባል ። አለበለዚያ ግን ከተኙት ጋር ተኝተን ምርጫው ሲደርስ ብንጫጫ ምንም ውጤት አናመጣም።
እያንዳንዱ የፖለቲካ ድርጅት፣ የፖለቲካ መሪ አሁንኑ አቋሙን ግልጽ ሳያደርግ ተደብቆ ቆይቶ ጥቅሙን ለማስጠበቂያ ብቻ ምርጫ ሲደርስ መንቀሳቀሱ ሃገርን ከመበደል ሊተናነስ አይችልም። ወያኔን ወደ ድል ለሚወስደው ምርጫ መፈራረም የሚፈልግ ካለ ዛሬውኑ አቋሙን ግልጽ እንዲያደርግ ልንጠይቀው ይገባል ። አልያ ግን ወያኔ በዚህ ዓይነት ዝርክርክነት ከሄድን ሁል ጊዜ አድርባይ አያጣም ። አድርባዮችም ሕዝቡን ለመከፋፈል ሰላማዊ ትግል ተብየውን እንደ መሣሪያ መጠቀም ይጀምራሉ።
ምን አልባት የሰላማዊ ትግል ተቃዋሚ አድርጋችሁ የምትወስዱኝ ካላችሁ ተሳስታችኋል። እኔ የምቃወመው ሀገር እየተበተነች፣ መሬታችን ለባዕድ እየተሸነሸነ፣ ክልል አፓርታይድን እያስከበረ በሰላማዊ ትግል ስም ሰላማዊ እንቅልፍ ሊኖር አይገባም ነው የምለው። ሰላማዊ ትግል እናደርጋለን የሚሉ ድርጅቶች መሪዎች ለወደፊት ምንድነው ራዕያቸው? ለሕዝብ ቀድመው ሊነግሩት ይገባል። እንዴት ነው የሚያታግሉን? ይህንን ጥያቄ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሁኑኑ መልሱን ይፈልጋል። እንደ ሰጎን ጭቅላችንን አሸዋ ውስጥ ከተው ተደብቀናል ቢሉ ከታሪክ ተወቃሽ ከመሆን አያመልጡም።
[email protected]
በልጅግ 2011 ጀርመን