ለፖርትላንድ ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክን ማኅበረ ምዕመናን

ቤተክርስቲያናችን እሁንም በድጋሚ የመበተን አደጋ የገጠማት መሆኑ ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው። አሁን የእኛ የውስጥ ጉዳይ ከመሆን አልፎ አማርኛ ማንበብና የእንተርነት አገልግሎት ላለው በዓለም ዙሪያ ለሚኖረው ፡ አንድነታችንን ለሚጠላውም ሆነ ለሚወደው ኢትዮጵያዊ ሁሉ በድረ ገጽ ይፋ ሁኗል። ይህም በመሆኑ እንድንበታተን ለሚፈልጉ ሁሉ የትብብር ጥሪ በመተላለፉ ፥ በእኛ ውስጥ በተከሰተው የውስጥ ችግር ደስ ለሚላቸው የደስታ መግለጫ ሲሆንና እረ እሰይ ስዕለቴ ሰመረ የማያስብላቸው የምስራች ሲሆን ፥ አንድነታችንን እንጂ መከፋፈላችንን ለማይመኙልን ወገኖቻችን ግን በመራራ ሀዘን ውስጥ ሁነው የሀዘን እንጉርጉሮ ያሰሙበት እለት እንደሆነ አልጠራጠርም። ለምሳሌ ለኔ በድረ ገጽ መውጣቱን አይተው ስልክ ደውለው የነገሩኝ ከሎስ እንጀለስ በነገሩ ጥልቅ ሀዘን የተሰማቸው አንድ አዛውንት ናቸው። እኔም በጣም በመደናገጥ ከዚያም አልፎ ነገሩን ለማመን አቅቶኝ ኮምፕተሬን ከፍቸ ወደተባለው ድረ ገጽ ስገባ የተባለውን ጽሑፍ ለማንበብ በቃሁና በቡድንም ሆነ በግል ያለመግባባቱን በይቅር ስለእግዚአብሔር ለመፍታት ሳደርገው የነበረውን ጥረት ተስፋ ቆርጨ ሁኔታው ከዚህ ደረጃ ከደረሰ በሁዋላ ምንም ማድረግ እንደማልችል /እንደማይቻል ወሰንኩ።

እንድንበታተን ለሚፈልጉ ሁሉ ተባበሩን የሚል ጥሪ ባይሆን ኑሮ ክሱን ለሕጋዊው ሲኖዶስ ጽ/ቤት በቀጥታ መላክ ይቻል ነበር። ነገር ግን ያ አይደለም የሆነው። የውስጥ ችግራችንን ዓለም በመገናኛ ብዙኀን እንዲያውቀው ተደረገ እንጂ። መፍትሔ የሌለው ችግርም አልነበረም የገጠመን። ቄስም ሆን ምዕመን ሁላችንም ሰዎች እንጅ ፍፁማን መላእክት እንዳለመሆናችን ያለመግባባት በመካከላቸን መፈጠራቸው ሊያስደንቅ የሚገባው ነገርም አልነበረም። ጥያቄው ግን በእውነት የተፈጠሩት ያለመግባባቶች እንደ ክርስቲያን በደጀ ሰላማችን በይቅር ስለእግዚአብሔር የማይፈቱ ኑረው ነው? በፍፁም። ይህን ማድረግ ብቻ ችግሩን ሊፈታው እንደሚችልስ በቅርባችን የሚገኙት ታላቁ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ ምሑር ምክራቸውን አለገሡንም ነበር ? አዎ አድርገዋል እንጂ ። ግን ማን ሰምቶ ? እኛ ያልነው ካልሆነ ማን ለሽማግሌ ምሑር ይምበረከካል ተባለ እንጅ ! ሁሉም ነገር እኛ ባልነው ካልሆነ ሊቀጳጳስም ሆነ የወንጌል መምሕር ሰብኮ እንዴት ፈርዖናዊ ከሆነው ልበ ደንዳናነታችን ሊያለዝበን ይችላል ተብሎ አመጽና እምቢተኝነት ተመረጠ እንጂ ! “የተነሳነበተን ዓላማ ግቡ ላይ ሳናደርስ የምን እርቅ ? የመን ሰላም ?” ተባለ እንጂ !

እነዚህ ወገኖቻችን የችግራችንን ቀዳሚ መንስኤ በ2008 ዓ.እ ስያትል ባሉት አባቶቻችን እና በእኛ “ጥቂት ግለሰቦች” መካከል ተፈጥሮ በነበረው የሀሳብ ልዩነት እንደሆነ ነው። እውነት ነው ያለመግባባቶች ተፈጥረው ነበር። ያለመግባባቱ ጉዳይ ግን በግል ጥቅም ላይ የተመሰረተ አልነበረም ፣ ባንድ ከኢትዮጵያ በመጡ ካህንና በብፁአን አባቶቻችን መካከል የነበረውን ያለመግባባት ለመፍታት ባደረግነው ሙከራ ነበር እንጅ። ያም ቢሆን ዛሬ እነዚህ ወገኖቻችን ዓለም እንዲያውቀው በመገናኛ ብዙኃን ሁኔታውን በማጋለጥ ሳይሆን ነገሩን የያዝነው ፥ ጥበብ በተመላበት ሁኔታ ማንም ሳይሰማው እኛ አኩርፈን የነበርን ልጆቻቸው በይቅርታ ከአባቶቻችን ጋር የነበረንን ጊዜያዊ ኩርፊያ ፈትተነዋል። ቅሬታዎቹ ተፈጥረው በነበረበት ጊዜም ነበር የቤተክርስቲያናችን መንፈሳዊ አመራር በስደት የሚገኙት አባቶቻችን መሆናቸውን በቤተክርስቲያናችን ሕገ ደንብ አርቅቀን በምልአተ ጉባዔው እንዲጸድቅ በማድረግ በግንባር ቀደምትነት ወሳኙን ሚና የተጫወትነው እኛ ለጊዜው አኩርፈን የነበርነው ልጆቻቸው መሆናችንን አባቶቻችን እራሳቸው የሚያቁት ጉዳይ ነው። ትላንት፥ ዛሬም ሆነ ነገ ከአባቶቻችን ጋር እንደምንቆም አባቶቻችን ጠንቅቀው እንደሚያውቁ አንጠራጠርም። አዎ ይህ ጸሓፊ ከሁሉም በላይ እውነትን መከላከያ ጋሻውና ማጥቂያ መሳርያው በማድረግ ሰዎችን ከእውነት በላይ አድርጎ የማያይ ደቀ መዝሙራቸው መሆኑን ያውቁታል። አዎ ይህ ልጃቸው ለግል ጥቅምም ሆነ ለውዳሴ ከንቱ ብሎ እውነት ላልሆነ ነገር የሚምበረከክ እንዳልሆነ ያውቁታል። እርግጥ ነው አንድ ነገር እውነትነቱን ለማረጋገጥ ዳተኛ ነው። እውነት እውነትነትዋ በመረጃ ከተረጋገጠ ግን ከእውነት ጋር እስከመጨረሻው ይቆማል። ከሁሉም በላይ የቂምና የበቀል ሰው እንዳልሆነ የሚያውቁት ሁሉ ይመሰክሩለታል። ለሥልጣን ወይም ለቁሳቁስ የሚስገበገብና እኔ አውቃለሁ ብሎ የሚመጻደቅ ሰውም ያለመሆኑን የእውነት ሰዎች ሁሉ ያውቁለታል። ሆኖም ግን አባታዊ ምክርንና ተግሳጽን ግን በፀጋ እንደሚቀበል እንዲሁ አባቶቻችን ያውቁታል። ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ከጌታው ከመዳኅኔዓለም ክርስቶስ ጋር እስከመጨረሻው ድረስ በመስቀሉ ስር ሁኖ እንደቆመ ሁሉ ፥ አሁንም አባቶቻችን እስከመጨረሻው ድርስ አብሮአቸው የሚቆም ማን እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቃሉ። አስመሳዩን ከእውነተኛው ለይቶ የማወቅ ከሁላችንም በላይ ብቃቱ አላቸው እና ።

እኛን ምዕመናንን ብቻም ሳይሆን ከአባቶቻችን ጋር ለማጋጨት የፈልጉት እኒህ “የአባቶቻቸን ተቆርቋሪዎች” አሁን በጠላትነት የተነሱባቸውን ቀሲስ ኤፍሬምንም ለማጋጨት ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። ያም ብቻ አይደለም ፣ ስያትል ያሉትን አባቶቻችንም ለመከፋፈል ሞክረዋል። ብፁዕ አቡነ ሉቃስና አባ ገ/ሥላሴ የኋላሸት ከነሱ ጋር እንደቆሙ ፤ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስና መምሕረ ወንጌል አባ ገ/ሥላሴ ጥበቡ ደግሞ ችግሩን ለመፍታት ያደረጉትን አባታዊ ምክርና ተግሳጽ ‘’ችግር ፈችዎች ሳይሆኑ ችግር አባባሾች እንደሆኑ” አድርገው ፈርጀዋቸዋል። ለምን ? በካህኑ ላይ ያቀረቡትን ፍሬቢስ ክስ ‘’ይደልዎ’’ ብለው ተቀብለው ካህኑን አባረው ቤተክርስቲያኒቱን እንድትዘጋ ወይም ለሌላ ኃይል እንድትሰጥ ባለለመፍቀዳቸው። ‘’የቤተክርስቲያን መመሪያ ወንጌል እንጂ ሰው ሰራሽ ሕግ አይደለም’’ በማለታቸው ተሾፈባቸው። ቃላቸውን አስተሐቀሩት ! አሁን እስቲ አንድ ሊቀጳጳስ የቤተክርስቲያን መመሪያ ከወንጌል የተለየ ነው እንዲል ይጠበቃል ? ምን አለ በማናውቀው ሙያ ውስጥ ጣልቃ ገብተን ባንፈተፍት። አዎ ‘’ድንቁርና ለድፍረት ፥ አፍቅሮ ንዋይ ለክህደት ይመቻል’’ ይላሉ አበው። ታድያ አባቶችን ከአባቶች ፥ ቀሳውስትን ከአባቶቻቸው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ፥ ምዕመናንን ከቤተክርስቲያን አባቶች ጋር፥ የሰበካ ጉባዔ አባላትን ከሁለት ከፍሎ ማጋጨት የማን ሥራ ነው ? አብረው ክፉና መልካሙን ለ19 ዓመታት ያሳለፉ አባላትን/የሥጋ ዝምድና ያላቸውን ሳይቀር የእግዚአብሔርን ሰላምታ መለዋዎጥ እስከሚያቆሙ ድረስ የጥል መርዝ የረጨባቸው የማን ተወካይ ነው? መንጋውን ከጠባቂው ነጥሎ ለነጣቂ ተኩላ አሳልፎ ለመስጠት የሚደረገው ጥረት የማን ተግባር ነው? አሁን በዘመናችን ኢትዮጵያውያንን በውጭም ሆነ በውስጥ እየከፋፈለና እርስበርስ እያጋጨ ያለው ኃይል ማን ነው ? ይህስ ታዲያ የማን ተልእኮ ነው ? መልሱ አጭርና ግልጽ ነው፣ እነዚህን የዋሀን እየመራ ያለው ግለሰብ ነው። የግለሰቡ ተልእኮ የማን እንደሆነ መልሱን ለአንባብያንና ገለሰቡን ለሚያውቁት ሰዎች እተወዋለሁ።

እነዚህ ወገኖችና መሪያቸው ቄሱን የሚከሱባቸው ነገሮች እንዲህ የሚሉ ናቸው ፣

1. ‘’ቀሲስ ኤፍሬም የቤተክርስቲያናችን ተቀጣሪ መሆናቸውን ዘንግተው “ በቦርዱ ሥራ ጣልቃ እየገቡ ‘’ቦርዱ የማያውቀውን ጉዳይ ለምዕመናን ያቀርባሉ’’ ‘’እስቲ እውነተኛ አማኞች የሆናችሁ አንባብያን አስተውሉት ይህን ‘’ተቀጣሪ’’ የሚለዉን ቃል። ታድያ እነዚህ ወገኖች ስለሚናገሩት ነገር የሚያውቁ ናቸው ማለት ይቻላል ? ቤተክርስቲያንን ከግል ኩባንያ ለይተው ማወቅ ስላልቻሉ ለቤተክርስቲያን አገልጋይ ካህን “ተቀጣሪ” የሚል ቃል እንዲጠቀሙ ተገደዋል። ታዲያ ለቤተክርስቲያን ሥርአት እነዚህ ወገኖች ከካህኑ በላይ ሁነው መናገር መንፈሳዊም ሆነ ሞራላዊ ብቃት አላቸው ብለው አባቶች ካህኑን እንዲያባርሩ እንዴት ይጠበቃል? “ቤተመቅደሱ እያፈሰሰ ስለሆነ እባካችሁ አስቡበት “ ማለታቸው ነው “በቦርዱ ሥራ ጣልቃ እንደገቡ “ ሁኖ እንደ ወንጀል የተቆጠረባቸው። ማን ነው ለመሆኑ ለቤተመቅደሱ ቅርበት ያለው ? ካህኑ ወይስ ምዕመናን የቦርዱ አባላት? ከቦርዱ አባላት አንዱ ምዕመን አውቀው በድፍረት ሳይሆን ሳያውቁ በስህተት ድምጽ ማጉያ ፍለጋ ወደቤተ መቅደስ ሲገቡ መግባት እንደማይፈቀድላቸው ካህኑ መከልከላቸው ጥፋት ነው? ይህም በቦርዱ ሥራ ጣልቃ መግባት ነው ? እኒህ የቦርዱ ሊቀመንበር በጣም የምናከብራቸው ታላቅ ሰው ናቸው። ክፉ ተናግረው ሰውን ማስቀየም የማይወዱ እጅግ ትሁትና ደግ ሰው ናቸው። ግን አሁን ይህ ግለሰብ የጥፋት ተልእኮው ማስፈጸሚያ አድርጎ እየተጠቀመባቸው ስናይ ልባችን ይደማል።
2. ‘’ቦርዱ ሳያውቀው መስቀል እንዲገዛ ገንዘብ አሰባስበዋል ‘’ መስቀል ይገዛ ማለት የካህኑ ሥራ መሆኑ እንዴት እንደጥፋት ይቆጠርባቸዋል? ይህም ቢሆን አሁን ባለን የበጀት አቅም ባሉን መስቀሎች መጠቀም እንጂ ሌላ ተጨማሪ መስቀል አያስፈልገንም የሚለው ሃሳብ አሳምኖአቸው ለመስቀል መግዣ ከምዕመናን የሰበሰቡትን ገንዘብ ለቦርዱ አስረክበዋል።
3. የቤተክርስቲያን አባላትን በእኩልነት እንደማይመለከቱ ስለቀረበው ክስ ፤ ሃቁ ግን የክሱ አቀነባብሪና ነገረ ፈጁ እንዲሁም ከተከታዮቹ 70% የሚሆኑት ካህኑ ከተወለዱበት ክ/ሀገር ከመወለዳቸውም በላይ የሥጋ ዝምድናም ያላቸው ከመካከላቸው አሉ። ተው ልክ አይደላችሁም ከምንለውም መካከል እንዲሁ ነው። እንዲያው ዘመን አመጣሹን የጎጥና የጎሳ ቋንቋ ለጥፋት መከላከያቸን አድርገን ብንጠቀም ክሳችን አዳማጭ ያገኝልናል ተብሎ የቀረበ ቅብዓተ ገጽ (makeup or diatribe)ነገር ነው። የነዚህ ሰዎች ኢላማዎች ቄሱ ብቻም አይደሉም። ይህ ጸሓፊና አንድ ወንድምም ጭምር ነን ። ሁለታችን በውጭ ሁነን ተሰጥዖ በመቀበል የምናገለግል ነን። በተለይ ይህ ወንድማችን ህጻናት ልጆቹን ከእንቅልፋቸው ከጧቱ በ 6 ሰዓት እየቀሰቀሰ ወደ ቤተክርስቲያን ከሁላችንም በፊት ቀድሞ በመገኝት ካህኑንና ዲያቆኑን በመርዳት የሚያገለግል ትሁትና ትጉ ወንድም ነው። በቅዳሴ ጊዜም ተሰጥኦ ከመቀበሉም በላይ እንደ ልጅ ለማእጠንት ፍሕም የሚያቀርብ ፥ በግጻዌው መሠረት የእለቱን ምንባቦችና ስብከቱን እያወጣ የሚያቀርብ በውጭ ሁኖ እንደ አስመልካች ካህን ሁኖ የሚያገለግል ወንድም ነው። ሁላችንም እንደማንኛውም ምዕመን ወርሀዊ መዋጮአችንን እንከፍላለን። ታዲያ እኛ ከካህኑ ጋር ተወግደን ምን አይነት አገልግሎት የሚካሄድበት ቤተክርስቲያን ለማድረግ ነው ? ለማዘጋት ወይም ለሌላ ኃይል አሳልፎ ለመስጠት ካልሆነ በስተቀር ? አባቶችህ ይህን ካህን አባረው ሌላ ምትክ እንደማያገኙልን ግልጽ ማድረጋቸውን መገንዘብ አለብን እኮ።

ከከሳሾቹ መካከል አንዳንዶቹ ፥ በተለይ መሪያቸው ወደ ቤተክርስቲያን የሚመጡት ግን አገልግሎቱ ካለቀ በሁዋላ ነው። የሚመጡትም ለጥፋት ሥራቸው ተባባሪ ለመመልመል ነው። መሪያቸው በደጀሰላሙ ፥ በምግብ ማብሰያው ሴቶችን ፤ እንዲሁም በመኪና ማቆሚያው ወንዶችን እየዞረ ለአድማውና አመፁ እንዲተባበሩት ‘’ቄሱ እንዲህ አላችሁ” እያለ አእምሮእቸውን ለመመረዝ ነው የሚመጣው። ቤተክርስትያን ወስጥ ቄሱ ሲያስተምር ድምጽ መቅጃ ይዞ ነው የሚቀመጠው። ከዚያ ውስጥ ቃላቶችን እየመረጠ እያጣመመ በመተርጎም ምዕመናንን እንዲሰናከሉ ያደርጋል። በዚህ ስልቱ ብዙ የዋሓን ምዕመናንን ከጎኑ ለማሰለፍ ቻለ። በዚህ ሁኔታ ለ 2 ዓመት ስራውን ከሰራ በሁዋላ አሁን ከደረሰበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በቃና የሥራውን ውጤት በመገናኛ ብዙኃን ዓለም እንዲያውቅለት አደረገ ።

ሰለዚህ አሁን ከላይ በተጠቀሱት ክሶች ካህኑን አባረን ቤተክርስቲያናችንን እንድንዘጋ አድራሻው ለሕጋዊው ሲኖዶስ ተደርጎ ዓለም እንዲያውቀው በስማቸን በድረ ገጽ እንዲወጣ የተደረገው። ይህን ተልዕኮው ጥፋት ብቻ የሆነውን ተግባር በሥራ ላይ ለማዋል ለJanuary 30, 2011 የብተና ቀን እንዲሆን መርጠውታል። ይህም የሚሆነው በነሱ ጽሑፍ ላይም ሆነ እኔ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና መምሕረ ወንጌሉ የሰጡትን ምክር ውድቅ በማድረግ ነው።

ስለዚህ በፖርትላንድ የምትገኙ የዚች ቤተክርስቲያን አባላት የሆናችሁ ሁሉ ቤተክርስቲያኒቱን ቀዳሽ ካህን አልባ አስቀርቶ ጣራና ግድግዳውን ብቻ አቅፈን እንድንቀር ለማድረግ እየተደረገ ያለውን አፍራሺ ሥራ እንድታከሽፉ በወላዲት አምላክ በቅድስት ድንግል ማርያም ስም ተማጽኛችሁ አለሁ። በግለም ሆነ በጋራ ለምታውቁዋቸው ሳይገባቸው ለዚህ ጥፋት ተባብሪ የሆኑትን ወገኖች ለመምከርም ብትሞክሩ መልካም ነው። ከመካከላቸው በይቅር ሰለ እግዚአብሔር የሚያምንም ካለ ምከሩ። በበኩሌ በይቀርታ አምናለሁ። አስቀይመኸናል የሚልም ካለ ተንበርክኬ ይቅርታ ለመጠየቅ ምንጊዜም ዝግጁ ነኝ። ከዚህ ሁሉ ከመድረሳቸን በፊትም ከካህኑ ጋር ቅሬታ አለን ያሉት ለማስታረቅ ሞክሬ ካህኑ ፈቃደኛ ሲሆኑ የዚህ ከፍፍል መሪ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሙከራየ ውጤት አልባ ቀርቶአል።

በግሌ ችግሩን ለመፍታት ለቦርዱ አቅርቤው የነበረውንም የመፍትሄ ጥሪ እንደመረጃ ይሆናችሁ ዘንድ እንድትመለከቱት ከዚህ በታች በአባሪ መልክ አቅርቤው አልሁ። ለጥፋት ሳይሆን እንደ ክርስቲያን ለመልካም ሥራ እንተባበር። አምላከ ብርሃናት ዐይነ ህሊናችንና እዝነ ልቦናችንን ያብራልን ፥ ዓሜን።

ለቤተክርስቲያኗ ከሚቆረሮሩ ምዕመናን አንዱ ሰማዕተ ጽድቅ ነኝ።

ለፖርትላንድ ደብረጽዮን ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት፡

ፖርትላንድ ኦሬጎን።

ከሁሉ አስቀድሜ ወንድማዊ ሰላምታየን በእግዜብሔር ስም አቀርባለሁ። መልካም የአውሮፓውያን አዲስ ዓምትም እንዲሆንላችሁ እመኝላችሁእለሁ።

ሁላችንም እንደምናውቀው ቤተክርስቲያናችን በየጊዜው ብዙ ፈተናዎች ሲገጥሟትና የገጠሟትን ፈተናዎችም በእግዚአብሔር እረዳትነትና በምዕመናኖቹዋ አርቆ ኣስተዋይነት ስትወጣቸው መቆየቷ የሚታወስ ነው። አሁን ያ የለመድነው ፈተና በናንተ ያገልግሎት ዘመንም ክርስቲያናዊ የሆነውን ማኅበራዊ አንድነታችንን ለመበተን በድጋሚ እየተፈታተነን እንደሆነ ለሁላችንም ግልጽ ነው። ምንም እንኳ ከካህኑ ጋር ያለመግባባት የፈጠሩት ምዕመናን ጉዳዩን በእርቀ ሰላም ለመፍታት ያደረግነውን ሙከራ ሳይቀበሉት ቢቀሩም ፣ ይህን አሁን የገጠመንን ችግር ወደናንተ ከመድረሱ በፊት በግል ለመፍታት ጥረት ያደረግን ሽማግሌዎችም ነበርን ።

የተፈጠረውን ያለመግባባት ለመፍታት እናንተ የተጠቀማችሁበት የቅራኔ አያያዝና አፈታት ዘዴ ግን የተፈጠረውን ያለመግባባት እንዲታረቅ በማድረግ ፋንታ ጭራሽ እንዲባባስ አድርጎታል ብል ማጋነን ሳይሆን እውነታውን ያለመቀነስና ያለመጨመር እንዳለ ያሳያል ብየ ኣምናለሁ።

ለምን ?

፩ኛ በመተዳደሪያ ደንባችን በአንቀጽ ፰ ውስጥ የተዘረዘሩትን የካህኑን የሥራ ድርሻዎች ባለመወጣት የቀረበ ክስ ሳይሆን ‘አሉሽ አሉህ’ በሚል ባለቤት የለሽ የሆነውን የግለሰቦችን ውዝግብ እኛ እንደሞከርነው በግል ጉዳይ የተፈጠረውን ያለመግባባት በእርቅ በመፍታት ፋንታ እንደ ቤተክርስቲያን ጉዳይ አድርጋችሁ መቀበላችሁ።

፪ኛ በዚህ ሁኔታ በካህኑና ያለመግባባት በፈጠሩት ምዕመናን መካከል የተፈጠረውን ያለመግባባት ከላይ እንደገለጽኩት የክርስትና እምነታችን መሠረት በሆነው ‘ይቅር ስለ እግዚአብሔር’ እንዲባባሉ በማድረግ ፋንታ የቤተክርስቲያኒቱን መተዳደሪያ ደንብ በሚፃረር መልኩ፡ ሙሉ በሙሉ ከግጭቱ ገለልተኛ ያልሆኖትን ወገኖች ያካተተ አጣሪ ወይም መርማሪ ኮሚሺን አቋቁማችሁ ካህኑ ‘ጥፋተኛ ናቸው’ የሚል ብያኔ ማስበየናችሁ።

፫ኛ ለእርቀ ሰላም ዋና መሠረት የሆነውን ቃለ ወንጌልና ተግሣፀ አበውን ለመስጠት ከስያትል የመጡትን የሀገረ ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ በፁዕ አቡነ ዮሐንስንና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ኣሉ ከሚባሉት አንደበተ ርቱዕ ከሆኑት ሰባኬ ወንጌል መምሕር ገብረ ሥላሴ የተሰጠው ምክር ከካህኑ ጋር ቅሬታ አለን በሚሉት ወገኖቻችን እንዲስተሐቀር(ዋጋ እንዲያጣ) ሲደረግ በዝምታ መመልከታችሁ ነው ብየ አምናለሁ።

ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላስ ለችግሩ መፍትሔ አለው ?

እኔ አወ አለው እላለሁ። እንዴት አድርጎ ከተባለ? የተፈጠረው ያለመግባባት ካሁን በፊት እንደነበሩት ሥራተ ቤተክርስቲያንን በመቀበልና ባለመቀበል የተፈጠሩ አይደሉም። ካህኑም ሆኑ ከካህኑ ጋር ያለመግባባት የፈጠሩት ወገኖቻችን እስካሁን በስደት ያሉትን የቤተክርስቲያን አባቶች እንደ መንፈሳዊ አባቶቻቸው ይቀበላሉ። ታዲያ በዚህ ቁልፍ ጥያቄ ላይ ልዩነት በሁለቱም ወገኖች በኩል እስከሌለለ ድረስ እንደ ክርስቲያን ‘’ይቅር ስለ እግዚአብሄር” በመባባል ብቻ ሊፈታ ይችላል። ካህኑ ሰው እንደመሆናቸው በሁሉም ነገር ፍፁም መሆን አለባቸው ብለንም መጠበቅ የለብንም። አልፎ አልፎ በማኅበራዊ ሕይዎታቸው ድክመቶች ሊያሳዩ ይችላሉ። እንደኔ ግንዛቤ ካህኑ በክህነት አገልግሎታቸው ግን ምንም ሕፀጽ አይታይባቸውም። የዶግማ እምነቶችን ፡ የቀኖና ሥራቶችን ፡ እንዲሁም ሌሎች የቤተክርስቲያናችንን ትውፊቶች ጠንቅቀው የሚያውቁና የሚሠሩም ካህን ናቸው። ያስተምራሉ፤ ያጠምቃሉ፤ ያቆርባሉ፤ ለሞቱት ጸሎተ ፍትሐት ያደርጋሉ። በነዚህ መንፈሳዊ አገልግሎቶች ማንንም አላገለሉም። በስደት ያሉትን የቤተክርስቲያን አባቶች መንፈሳዊ አመራርና ትእዛዝ ያለምንም ማስተሐቀር በማክበር ይቀበላሉ። ይህን አያደርጉም ብሎ የሚከሳቸው ማን ነው ?

ለዚህ ሁሉ የሚከፈላቸው የአገልግሎት አበልም በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙት ካህናት ዝቅተኛ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። አሁን የሚያገኙት አበል በሌላ አካባቢ ለዲያቆን ከሚከፈለው ያነሰ መሆኑ መታወቅ አለበት። ነገር ግን ካህኑም ሆኑ ወንድማችን ሊቀ ዲያቆናት መንበሩ ክህነታቸውን በገንዘብ ሊመዝኑት ስላልፈለጉ ለአገልግሎታቸው የንዋይ ቅድመ ሁኔታን አላስቀመጡበትም። በኔ እምነት ካህኑም ሆኑ ደጉና ትሁቱ ሊቀ ዲያቆናት መንበሩ እያገለገሉን ያሉት በፈቃደ እግዚእብሔርና በወላዲት አምላክ በቅድስት ድንግል ማርያም ምርጫ ነው እላለሁ። ይህን ተጋፍቶ ካህኑን ለማባረርና ቤተከርስቲያንን ለመዝጋት የሚደረገውን ጥረት ተባብረን ችግሩን በመፍታት እንድናከሽፈው ክርስቲያናዊ ግዴታ ኣለብን እላለሁ። ቤተክርስቲያንን ለማፍረስ ወይም ለሌላ ኃይል አሳልፎ ለመስጠት የታቀደ ሌላ ድብቅ አጀንዳ በስተጀርባ እስከሌለ ድረስ ሊታረቅ የማይችል ችግር አልገጠመንምና።

<<ነጽሩ ነፍሰክሙ ፡ ወአንጽሑ ነፍስተክሙ ፣ ወለቢጸክሙሂ ኢትዝክሩ አበሳሁ፡ ርእዩ ከመ መኑሂ ኢሀሎ በመዓት ምስለ ካልኡ። >> ትርጉም =<< ነፍሳችሁን ተመልከቱ ፡ ሰውነታችሁንም ንጹሕ አድርጉ፣ የባልንጀራችሁንም በደል አታስቡ፣ ማንም ከወንድሙ ጋር በቁጣ እንዳይኖር አስተውሉ። >> ይላል የጌታ ቅዳሴ።

ስለዚህ አሁን ለመጥራት ያሰባቸሁት ጠቅላላ ጉባዔ ያለመግባባቶችን በዚህ መልክ ያለምንም ንትርክና ውዝግብ እንደ ክርስቲያን ማንም በማንም ላይ ቅሬታ ያለው የቤተክርስቲያናችን አባል ይቅር ስለ እግዚአብሔር ተባብለን አብረን ለመኖር የምንወስንበት ጉባዔ እንድታደርጉት በቤተ ክርስቲያን ስም ተማጽኛችኋለሁ። ከዚህ ውጭ ደጀ ሰላሙን (የሰላሙን መድረክ) ካህኑን የግል ቂም ላለባቸው ወገኖች የበቀል መወጫ እንዳታደርጉት አደራ እላለሁ። ከስያትል መጥተው ያስተማሩን አባቶች መልክትም የተፈጠሩት ያለመግባባቶች በይቅር ስለ እግዚአብሔር ብቻ እንዲፈቱ ነው። በዚህ ምክንያት ማንም ምዕመን ከቤተክርስቲያናችን መለየት የለበትም። ስንመርጣችሁም ምዕመናን የጣልንባችሁ አደራ ዋናው ተግባር አንድነታችንን እንድትጠብቁልን መሆኑን መዘንጋት የለባችሁም። ቤቱ ቤተክርስቲያን እንጅ የአክስዮን ማኅበር እንዳይደለ ሁላችንም ማወቅ አለብን። ቤተክርስቲያን የምንለው በሥራትና በእምነት የሚመራ የምዕመናን ማኅበረ አንድነት ማለት ነው እንጅ ጣራውና ግድግዳው አይደለም። በቤተ እግዚአብሔር ውስጥ የምናገኘው ጥቅም መንፈሳዊ እንጅ ሥጋዊ ስላልሆነ ፡ ከዚህ አንጻር ነው የሚገጥሙንን ፈተናዎች ሁሉ ልንወጣቸው የሚገባን። አማካሪዎቻችሁም ስለቤተክርስቲያን ሥራት በቂ ግንዛቤ ያላቸው ቢሆኑ ይመረጣል። ይህን ብታደርጉ ኑሮ አሁን የገጠመንን ችግር ማስወገድ ይቻል ነበር። ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ተቅዋም እንደመሆኗ ችግሯ ሁሉ ሊፈታ የሚችለው በመንፈሳዊ ጥበብ እንጂ በሥጋዊ መንገድ አይደለም። ለዚህም ነው ከሲያትል መንፈሳዊ አባቶችን ለመጥራት የተገደድነው።

እስቲ ቅዳሴአችን የሚለውን እንመልከት << ….ንሕነሰ ሥጋውያን ንሔሊ ሕገ ሥጋ ወንገብር ግብረ ሥጋ ፡ ወነሐውር በፍኖተ ሥጋ ። አንተ ባሕቱ መሀረነ ምግባረ መንፈስ ወአለብወነ ሕገ መንፈስ ወምርሐነ ለነ አንተ ፍኖተ መንፈስ >> ትርጉም ፣ << ….ሥጋውያን የምንሆን እኛ ግን የሥጋን ሕግ እናስባለን ፡ የሥጋንም ሥራ እንሠራለን ፣ በሥጋ መንገድም እንሄዳለን። አንተ ግን የመንፈስን ሥራ አስተምረን ፡ የመንፈስንም ሕግ አስረዳን፡ የመንፍስንም መንገድ ምራን።>> ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ።

አጭር ማስተዋሻ ስለቀዱስ ዲዮስቆሮስ ፤ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በ444 ዓ.ም መምሕሩ የተዋሕዶ ኃይማኖት አባት ቅዱስ ቄርሎስ እንዳረፈ በእስክንድርያ መንበረ ፓትርያርክ ተቀምጦ በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ የደረሰው ጸሎተ ቅዳሴ ነው። የእኛም ፓትርያርክ ነበር። ዛሬ ቅዳሴው ከልደት እስከ ዐቢይ ጾም መግብያ እና ከትንሣኤ እስከ ጾመ ሐዋርያት መግቢያ በቤተክርስቲያናችን ይቀደሳል። ይህ ቅዱስ የተዋሕዶ አባት በተዋሕዶ እምነቱ ምክንያት በትንሿ እስያ በኤጅያን ባሕር በምትገኝው ጋንግራ ደሴት ውስጥ በግዞት ተሰቃይቶ በ454 ዓ.ም አርፎአል።

የሰላምና የቅዱሳን አምላክ አይለየን ፡ አዲሱ የምንኖርበት አገር ዓመት የሰላም የፍቅርና የእንድነት ዓመት ይሁንልን ዓሜን።

ነገሩ ካሳሰባቸውና ስለቤተክርስቲያን ሥራትና አንድነት ከሚቆረቆሩት ምዕመናን አንዱ ነኝ።

(ኢሜይል [email protected])