ለምን የአቶ መለስ ወያኔ እንደ ቴሌ ለውጪ አይሸጥም

የተበሳጨ ዜጋ

በአንድ ትልቅ ቤተሰብ ወስጥ ያሉ የቤተሰቡ አባላት ህይወት ችግር ውስጥ ከገባና ህይወታቸውንም በትክክል ለመምራት ከተቸገሩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የቤተሰቡ ዋነኛ ሀላፊ የሆኑ አባወራና እማወራ ከችግሩ ጋር በዋነኝነት የተያያዙ ስለሆኑ ለሚፈጠረው ውድቀትና ችግር ተጠያቂ ናቸው ማለት ነው፡፡መንግስትም በተወሰነ መንገድ የአንድ ትልቅ ቤተሰብ ግልባጭ ነው፡፡

መንግስትን መንግስት የሚያስብሉት በመጀመሪያ ደረጃ የተከለለት ቁሳዊ የሆነው ጆኦግራፊያዊ ሀገርና በዚህ ውስጥ የሚኖሩት ህዝቦች ሲሆኑ እነዚህን ሁለት ዋነኛ ነገሮች የሚያስተሳስሩት ድሮችና ሰንሰለቶች ደግሞ ህዝቦች ህግንና ደንብን ተከትለው በመስማማትና በመወያየት በሂደት የሚያዋቅሯቸው የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማቶች ናቸው፡፡ አንድን መንግስትም እውቅና ያለው መንግስት የሚያስብሉትም በዋነኝነት እንዚህን 3 ነገሮች ማለትም 1ኛ-ህዝብ 2ኛ-ጆኦግራፊያዊ ክልልና 3ኛ-ተቋማቶች በስርዓት አቀናጅቶና አስተባበሮ ሲገኝ ነው፡፡ ከእነዚህ አንዱ ከጎደለ መንግስት ሊባል አይችልም፡፡ስለዚሀም ለምሳሌ በአንድ ሀገር ውስጥ ያሉ ዋና-ዋና ተቋማት በስርዓት የሚጠበቅባቸውን ተግባር ማከናውን ካልቻሉ የእነዚህ ባለቤት የሆነ አንድ መንግስት እንደ መንግስት የሚጠበቀውን ተኣማኒነትና ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም ማለት ነው፡፡ እነዚህ የተለያዩ ተቋማትም እራሳቸውን በስርዓት ማስኬድ ካልቻሉና ውድቀትና ችግር ውስጥም ከገቡ በተዘዋዋሪ የእነዚህ ተቋማት የበላይ ጠባቂ የሆኑት ማናቸውም አካላት ተጠያቂ ናቸው ማለት ነው፡፡ ስለዚህም አቶ መለስና ወያኔ እንደ መንግስት በሀይልም ይሁን በብልጣብልጥነት ስልጣን ላይ እስካሉ ድረስ የዚህች ሀገር ከፍተኛው የበላይ ጠባቂና ወሳኝ ናቸውና እንደ ቴሌኮሙኒኬሽን ያሉ ከፍተኛ ግምትና ዋጋ ያላቸው የመንግስትና የህዝብ ተቋማት ውድቀት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የራሳቸው የአቶ መለስና የወያኔ ስርዓት ውድቀትና ጥፋት ውጤት ናቸው ማለት ነው፡፡ ይህ ከላይ የተገለፁት አባባሎችና አስተያየቶች ጤናማ አስተሳሰብና ላለው ቀና ለሆነ መንግስት በገንቢነት የሚሰጥ አስተያየት ቢሆንም በተቃራኒው ግን ሀገርና ህዝብን ለመበተንና ለማጥፋት ወገባቸውን አጥብቀው ሌት ተቀን እንቅልፍ አጥተው በእኩይ ተግባር ለሚንቀሳቀሱት ለአቶ መለስና ለወያኔ የሚሆን አስተያየት እንዳልሆነ ይገባኛል፡፡

በእርግጥ የምናውቀውን ቴሌኮሚኒኬሽንንማ ላለፉት 5 ዓመታት ያህል አቶ መለስና ወያኔ ሆነኝ ብለው ወደ ወድቀት እንዲያመራ የሚችሉትን ያህል የቤት ስራ ሲሰሩ ነው የኖሩት፡፡ልክ እንደ ምርጫው ማለት ነው፡፡በመጀመሪያ ወያኔ ሀገሪቷን ሲቆጣጠርና በመንግስትነት ስልጣን ሲይዝ በቴሌኮሚኒኬሽን ውስጥ ዋና ስራ አድርጎ ሀ ብሎ የጀመረው ለሌሎች ምርጥ ባለሙያዎችና ኤክስፐርቶች እንኳን የማይደረገውን በድርጅቱ ውስጥ የራሴን የደህንነት ስራ ይሰራልኛል ብሎ ላስቀመጠውና ነገር ግን ምንም አይነት ከቴሌኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ጋር የሚያያዝ አንዳችም እውቀት ለሌለው ተራ ተጋዳላይ ግለሰብ ምርጥ መኪና በአደባባይ በመሸለም ነበር፡፡ እንግዲህ በዚህ ድርጅት ውስጥ አንድ ተራ ተጋዳላይ ከአንድ በቴክኖሎጂው ከሰለጠነ ባለሙያ የተሻለ ክብርና ዋጋ እየተሰጠው የመጣው ከዚያ ጀምሮ ነው፡፡ይህም ድርጊት ያው አቶ መለስ አንድ ወቅት መሃይምም ቢሆን የኢህአዲግን ዓላማ እስካስፈፀመ ድረስ ያሉት ዋና መርህና መፈክር አካል መሆኑ ነው፡፡በዚህ አይነት ሁኔታ ሀ ተብሎ የተጀመረ መጥፎ አያያዝና አካሄድ ከዚያ ቀስ በቀስ ሙያና ችሎታ ያለቸውን ሰዎች በመግፋትና ግማሾቹም ከንቱ የውንጀላ ሰበብ እየተፈጠረላቸው እስር ቤት እየተወረወሩ ቀስ በቀስ ድርጅቱ የፖለቲካና ተራ የውንብድና ዝርፊያ የሚካሄድበት ማእከል እየሆነ መጣ፡፡

ውሳኔዎችና አመራሮች እውቀቱ ባላቸው ብቁ ባለሙያዎች መሰጠት ሲገባቸው ብቃቱ በሌላቸው የፖሊተካ ታማኞች መሆን ጀመሩ፡፡ይህም የሆነው አቶ መለስና ወያኔ የራሳቸውን ድብቅ አላማና ፍላጎት እንደፈለጋቸው ለማስፈፀም እንዲመቻቸው ለማመቻቸት ነበር፡፡ስለዚህም ላለፉት 5 ዓመታት ያህል ቴሌን የማፈራረስና የማዳከሙ ተግባር በረቀቀ መንገድ ሲካሄድ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

ከዚያም አቶ መለስና ወያኔ ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ስሟን ዥግራ ይሏታል እንዲሉ አስቀድመው ድርጅቱን በተለያየ መንገድ ሆነኝ ብለው በሂደት እንዲንኮታኮትና አቅመ ቢስ እንዲሆን ለዓመታት ያህል መሰሪ ስራቸውን ሲሰሩ ከኖሩ በኋላና ይኸው ዛሬ ብብቃት ማነስ ሰበብ ማኔጅመንቱን መፈንቅለ-መንግስት አካሂደውበት እጅግ ውድ በሆነ ክፍያ ለውጪ ዜጎች አሳልፈው ሰጡት፡፡በእርግጥ አቶ መለስና ወያኔ ይህንን ያደረጉትና ከዚህ በፊትም ቴሌ ለባለሀብቶች አይሸጥም እያሉ ሲሟገቱ የኖሩት ያን ያህል በተቆርቋሪነት ለሀገርና ለህዝብ አስበው አልነበረም፡፡ይህንን አንድ ወቅት የሚታለብ ላም እየተባለ የሚጠራንና የሀገሪቱ ብዙ አንጡራ ሀብት የፈሰሰበትን ትልቅና አንጋፋ ድርጅት በሂደት እራሳቸው በተዘዋዋሪ በባለሀብት ስም ለመግዛትና እራሳቸው በተራቸው እንደላም ሊያልቡበት ሁኔታዎችን ሲያመቻቹ ነበር፡፡በእርግጥ አዎ ቴሌ የመንገስትና የህዝብ ንብረት ነው ቢባልም ላለፉት 5 ዓመታት ያህል አቶ መለስና ወያኔ ይህንን ድርጅት በተለያየ መንገድ በተዘዋዋሪ በተጠናከረ ሁኔታ እንደ ላም ሲያልቡት ሲቦረቡሩትና ሲያዳክሙት ኖረዋል፡፡

ስለዚህም ያሁኑ ክስተት ለቴሌ የአንዴና የመጨረሻው ውድቀት መጀመሪያ ዋዜማ ነው፡፡ማነህ ባለ ሳምንት እንደሚባለው የሚቀጥለው ተረኛ ደግሞ ማን ይሆን ያስብላል፡፡ በእርግጥ አቶ መለስና ወያኔ ዋነኛ ስራቸው ሀገርን ለዘለቄታው ከትውልድ ትውልድ በሚሸጋገር መንገድ ማቃናትና መገንባት አይደለም፡፡ዋነኛ ስራቸውም በእርዳታና በብድር በሚገኝ ገንዘብ በልማት ስም እንደ አንድ ተራ የቢዝነስ ሰው በዚህች ሀገርና ህዝቦች ኪሳራ የራሳቸውን ጥቅም ማሳደድ ነው፡፡ሀያ አራት ሰዓት አእምሯቸውና ልባቸው የሚባዝነው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ እንዴት አድርገው ከእያንዳንዱ እንቅስቃሴና አጋጣሚ ሁሉ እንዴት አድረገው ባቋራጭና በፍጥነት ጥቅም እንደሚያገኙ ማስላት ነው፡፡ ስለዚህም አቶ መለስና ወያኔ በታሪክ ከሚታወቀው የመንግስትነት መገለጫ ብህሪያት ይልቅ እንደ ዘመኑ አይነት ያለ የአጭበርባሪ የቢዝነስ ሰው አይነት ባህሪያት ነው ያላቸው፡፡ ስለዚህም የቴሌም ውድቀት ከዚህ እንደ ካንሰር በቀላሉ ከማይድንና ጤናማ ካልሆነ መሰረታዊ አስተሳሰብና ፍላጎት ከሚመነጭ ሁኔታ ጋር በጣሙን የተያያዘ ነው፡፡ ስለዚህም መርዶ ነጋሪነት ካልሆነብኝና እድሜና ጤና ከሰጠን የትላንቱን ETC(Ethiopian Telecommunications Corporations) ወይንም የዛሬውን (Ethio-Telecom) እነ አቶ መለስ እንደ ሚሉት የሙከራ ጊዜውን ጨርሶ ከሁለት ዓመት በኋላ በሙሉ የመንግስትና የህዝብ ንብረትነት እናገኘዋለን የሚል እምነት ያን ያህልም የለኝም፡፡ ምክንያቱም ቅድም እንዳልኩት ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ስሟን ዥግራ ይሏታል አይነት ስለሆነ አቶ መለስና ወያኔ ቅድም የገለፅኩትን ድብቅ አላማቸውንና ፍላጎታቸውን ካላሟሉ በስተቀር የተረጋጋ እንቅልፍ የሚወስዳቸው አይመስለኝም፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ ይህንኑ ቴሌን በሂደት የማፍረስና የማዳከም ስራ ሲሰሩ ከኖሩት ውስጥ በፊት የ Ethiopian ICT Development Agency -Director General የነበሩትና በአሁኑ ወቅት የመገናኛና ትራነስፖርት ሚኒስቴር ተብለው የተሾሙት ግለሰብ ማንነት ነው፡፡

ከአስተማማኝ ምንጮች ለመረዳትና ለማጣራት እንደቻልኩት ከሆነ ሰውየው እንደተለመደው ተጋዳላይ እንደሆኑና የመጀመሪያ ድግሪያቸውንም ወያኔ ስልጣን ከያዘ ከአንድ 7 ዓመታት በኋላ ከአዲስ አበባ የኒቨርስቲ ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ በኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ አግኝተዋል፡፡የሚገርመው ግን የግለሰቡ ተጋዳላይ መሆን ሳይሆን ግለሰቡ ከዚሁ ዩኒቨርስቲ እጅግ ከባድ እንደሆነ ከሚነገርለት የዚህ ትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ያገኙበት መንገድ ነው፡፡የሚገርመውም ትምህርታቸውን በተለመደው አይነት በስርዓትና በትጋት መከታተል ሳይችሉ ለይስሙላ በፈተና ሰሞን ትንሽ ለታይታ ብቅ እያሉና ፊታቸውን ለይምሰል እያስመቱና እየተፈተኑ ውጤት ግን በውስጠ ሚስጥር በትእዛዝና በመመሪያ እየተሰጣቸው ሌላው ግን እጅግ በጣም ፈግቶ የሚያገኘውን የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ከዚሁ ዩኒቨርስቲ እንደቀልድ ማግኘታቸው ነው፡፡ እንግዲህ አቶ መለስና ወያኔ በዚህች ሀገር ላይ የሚሰሩት ጥፋትና መሰሪነት ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ የአምስት ዓመት እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱም አላማውና ተግባሩም በአደባባይ እንደሚወራው ሳይሆን እውነተኛውና ዋነኛ ድብቅ ዓላማውም በሚቀጥሉት አምስት አመታት በዚህች ሀገር ላይ ከምንጊዜውም በላይ ታይቶ በማይታወቅ መንገድ በአቶ መለስ ወያኔ ከፍተኛ ዝርፊያና ጥፋት በረቀቀና በተቀነባበረ መንገድ የሚፈፀምበት ዘመን ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህም ነገሩ እንደዚህ ከሆነ አይቀር ምናልባት ይህንንም ዝርፊያና ጥፋት በጥሩ ስኬት ለማስፈፅም አቶ መለስ ለምን ከውጪ ሀገር አማካሪ ባለሙያዎችን ሚኒስትሮችንና እንዲሁም የራሳቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴርነትን ስልጣን እንደ ቴሌ በውድ ዋጋ በውጪ ምንዛሪ ቀጥረው እርሳቸው ደግሞ የመቶ አለቃ ግርማን የፕሬዜዳንትነት ስልጣን ተቀብለው ለምን አርፈው ቁጭ ብለው እንቅልፋቸውን አይለጥጡም ያስብላል፡፡

ድፍረት አይሁንብኝና በእርግጥ አቶ መለስም ቢሆኑ ለመላው ኢትዮጵያውያን ምንጊዜም ቢሆን ቅንጣት ታህል እውነተኛ ፍቅር አክብሮትና ታማኝነት የሌላቸውና ሙሉ የተለመደው የኢትዮጵያዎነት ስብእና ያልተላበሱ ሰው ስለሆኑ እሳቸውም ቢሆኑ እኮ ከባእድ ቅጥረኝነት ብዙም የተለዩ ግለሰብ አልነበሩምም አይደሉምም፡፡ የዚህችም ሀገርና ህዝቦቿም አጠቃላይ ወቅታዊ ሁኔታም እጅግ የተወሳሰበና ግራ የሚያጋባ የሆነውም በዚህ ምክንያት ሳይሆን ይቀራል? ስለዚህም ምናልባት የሚሻል ከሆነ አቶ መለስና የወያኔ መንግስትም ለጥቂት ጊዜም ቢሆን እንደ ቴሌ ለውጪ ሰዎች ቢሸጡና ቢያዙ ምን ይመስላችኋል?