ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ሰራተኞቹን የገና በዓል እረፍት ከለከለ

ከድርጅቱ ሰራተኛ

ሃገራችን የገባችበት የአገዛዝ ስርአትና ሕዝቡ ላይ የተጫነው የባርነት ስርአት፤ ለገዢው መደቦችና አቀንቃኝ ታማኝ አገልጋዮች የሃብት ማካማቻ ብቻ ሳይሆን፤ ሰውን እንደመገልገያ እቃ እንዲጠቀሙበት እየፈቀደላቸው ነው፡፡

በአሰሪና በሰራተኝው መሃል ሊኖር የሚገባው ግንኙነት መስመሩን ጨርሶ እየለቀቀ፤አሰሪው እንዳሻው ለሰራተኞቹ የግፍና የመከራ የስራ ህግ እንዲያወጣ የገዢ መደብ ወገንተኛነቱ ሙሉ ፈቃድ የሰጠው ይመስላል፡፡

ሰራተኛው በሃገሪቱ ላይ ያለው የስራ መደብ ተጠቅልሎ ለገዢው መደብ ተወላጆች በመሰጠቱና ተራፊው ወይም ተመራጮቹ የመደቡ ቤተሰቦች ሊሰሩት የማይችሉት ለሌሎች ኢትዮጵያዊያን በመቸሩ፤ ምንም ያህል መከራ ቢጫንባቸው፤ሥራቸውን ላለማጣት በሚል ሰበብ የሚመጣውን ሁሉ በመቀበል ያገለግላሉ፡፡

የአሰሪና የሰራተኛ ህግ ወጥቶ፤ በህገመንግስቱ ላይ ሰፍሮ ይነበባል፡፡ ያ ግን ተግባራዊ የሚሆነውና የሚያጠያይቀው፤ ሰራተኛው የገዢው ወገን ሲሆን፤ አለያም አሰሪው የገዢው ወገን ሆኖ በሰራተኞች የመብት ጥሰት ጥያቄ ሲነሳ፤ ያን የወያኔ ኢህአዴግ ወገን የሆነውን አሰሪ ለመጠበቅና ከተጠያቂነት ለማዳን ሲያስፈልግ ብቻ ነው፡፡

አንድ የማውቀው ሰው፤ ቀደም ሲል ከወያኔ ኢህአዴግ ባለስልጣናት ጋር፤ በተለይም ከህላዊ ዮሴፍ፤ ከበረከት ስምኦን እና ከዳዊት ዮሃንስ ጋር ለንግድ ጥቅሙ ሲል ለአገልጋይነት እራሱን አሰልፎ፤ ከአቅሙ በላይ የሆነ ንዋይ እያፈሰሰ ሲሰጥና፤ በአይነት እጅ መንሻ ሲያቀርብ፣ በዓላት በመጡ ቁጥር ለሸክም የሚያስቸግርና አንቱ በሚባል ዋጋ የሚገዛ ሙክት እና ብሉ ሌብል ውስኪ እየጫነ ሲሄድ፤ ምን በወጣህ ነው ይህን ሁሉ የምታደርገው ብለው፤ያንተ ችግር እኮ በህጋዊው መንገድ ብቻ ማለትህ ነው፤እኔ ግን በእጄ በመሄድ በዛ አተርፋለሁ፡፡ይሄ ለእኔ የስራ ዋስትና ነው፡፡ይህን ሳወጣ ነገ የጠየቅሁት ሁሉ ይሁንታ ያገኛል፡፡ያለኝ እውነት ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

በምርጫ ሰሞን ለወያኔ ኢህአዴግ ይህ የማውቀው ሰው የንብ አርማ ያለበት 500 ካናቴራ አሰራ ተብሎ ካሰራ በኋላ ደቡብ ድረስ ወስደህ አስረክብ ተብሎ በራሱ ተሸከርካሪና ነዳጅ ህላዊና በረከት የላኩት ነው ብሎ ማስረከቡን የነገረኝ ሳይሆን በቅርብ ያየሁት ነው፡፡

ይሀንና ይህን የመሳሰሉት በጥቅም የተገዙ፤ ህሊናቸውን የሸጡ አጨባጫቢዎች ናቸው ለወያኔ ኢህአዴግ የልብ ልብ ሰጥተው እንዳሻው በህዝብ ላይ እንዲፈነጭ የሚያደርጉት፡፡

አንድ አሰሪ ለሰራተኞቹ ከበሬታ ባይኖረው እንኳን፤ የሀገሪቱን ህግና ባህል ግን የማክበር ግዴታ ሊኖረው የግድ ነው፡፡ የሚተማመንባቸው የወያኔ ኢህአዴግ ገዢዎች ያወጡትንና በህገመንግስቱ ላይ ተቀምጦ የሚነበበው ደንብ ለመከበሩ ባያምንበትም ለጌቶቹ ስም ሲል ማክበር ይጠበቅበታል፡፡

ሃገሪቱ ብሔራዊ በዓል ብላ ያስቀመጠቻቸው ቀናት በሙሉ፤ የማንም ሃይማኖት ተከታይ በዓላት ይሁኑ የማንም፤ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሊከበሩ የግድ ነው፡፡ እርግጥ ሃይማኖታዊ ሲሆኑ የየሃይማኖቱ ተከታዮች እንደየእምነታቸው ቢያከብሩትም እንደሃገር ግን በነዚህ ብሔራዊ በዓላት ቀን ስራዎች ዝግ ሆነው ይውላሉ፡፡ ይህ በህግ የተደነገገ ማንም በምንም መልኩ ሊያፈርሰውና ሊጥሰው የማይችል ጉዳይ ነው፡፡

በዘንድሮው የገና በዓል ግን ይህ ህግ ተጥሶ፤በማን አለብኝነት በአዋሳ የሚገኘው ‹‹የሰንሻይን ኮንስትራክሽን›› ድርጅት ሰራተኞቹን ‹‹አንድም ሰው በዓሉን አስመልክቶ ወደ አዲስ አበባና ወደ ሌላ ክልልም ከሄደ ስራ አለኝ ብሎ ወደዚህ እንዳይመለስ›› በማለት በዓሉን በስራ እንዲያሳልፉት አድርጓል፡፡ይሀን ሲያደርግ ደግሞ በፍርሃትና በስውር ሳይሆን በግልጽ ማስታወቂያ አውጥቶ በግቢው ቦርድ ላይ ለጥፎ ነው፡፡በዚህ ቦታ አብዛኛዎቹ ሰራተኞች ከተገዢ ወገን ስለሆኑና የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ደሞ ‹‹ጠባቂ ያላት በግ ላቷን ከውጭ ታሳድራለች›› አይነት ስለሆነ እንዳሸው በሰራተኞቹ ላይ፤ ልክ ጌቶቹ የወያኔ ኢህአዴግ አባላት እንደሚያደርጉት እያደረገ ነው፡፡ ጠያቂ የለም፤ ለምን ባይም አልተገኝም፡፡ ሰራተኛው፤ስራዬን እንዳላጣ በሚል ፍርሃት ትእዛዙን ተቀብሎ ‹‹የገና በዓል›› ሳይኖረውና ቤተሰቡንም ለገና ሳያጠይቅ ተለይቶ እንዲውል በተፈረደበት መሰረት ባለበት ስራ ላይ ተተክሎ ውሏል፡፡

ያሳዝናል፡፡የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ማን አለብኝነት፤ነገ በታሪክና በትውልድ መጠየቃቸው አይቀሬ ነው፡፡

‹‹ከጠገቡ ሰው አይፈሩ›› ይሏል እንዲህ ነው፡፡