በአይነቱ ልዩ የሆነ የግጥም ንባብ በገጣሚ ኤፍሬም ስዩም ቀረበ
ከዚህ ቀደም “ሶልያና” በሚል ርዕስ በሰራው ሲዲ ላይ ባሉ ተወዳጅ ግጥሞቹ የሚታወቀው ወጣት ገጣሚ አፍሬም ስዩም ትላንት ምሽት በአሊያንስ ኢትዮፍራንሲስ የግጥም ስራዎቹን አቀረበ፡፡ በሳክስፎን ታጅቦ የግጥም ስራዎቹን አዳራሹን ለሞሉት ታዳሚዎቹ ያቀረበው ኤፍሬም ያነበባቸው ግጥሞች በዚህ ወር መጨሻ በሲዲ ከሚለቀቁት የግጥም ስራዎቹ መሀል የተወሰዱ መሆናቸውንም ገልጿል፡፡ ገጣሚ ኤፍሬም ስራዎቹን ያቀረበበትን ዕለት በኢትዮጵያ ስነፅሑፍ ታሪክ ውስጥ አዲስ ቅርፅ አስተዋውቋል ላለው ለደራሲ አብርሀም ረታ መታሰቢያነት አውሎታል፡፡ በዕለቱ ገጣሚው ካቀረባቸው የግጥም ስራዎቹ መሀል ጌቴሴማኒ፣ ሴትና ሀገር፣ ሁለት ክንፎች፣ ፍቅርና ክራር፣ ክረምትና ፀደይ እንዲሁም የጲላጦስ ዕድፍ በኢትዮጵያ አናት በሚሉ ርዕሶች የተፃፉት ግጥሞች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በተለይ “የጲላጦስ ዕድፍ በኢትዮጵያ አናት” የተሰኘው የግጥም ስራ ታዳሚውን ያስደመመ ነበር፡፡ የግጥም ስራዉ አፄ ምኒሊክ ሌላውን የኢትዮጵያ ክፍል በጣልያን ቅኝ ከመገዛት ሲያድኑ ኤርትራን ግን በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ገብተውም ቢሆን ለጣልያን መተዋቸው የእሳቸውም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ራስ ምታት እንደሆነ እስከ ዛሬ መዝለቁን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህንን ሀሳቡን ገጣሚው በተለይ “ለአንድ ሀገር ነፃነት አንድ ሀገር ሰውቶ” በሚል ስንኝ የገለፀው ሲሆን የተጠቀሰው ድርጊት ያስከተለውን ውጤትም በሚከተሉት ስንኞች ገልፆታል፡፡
ከዚህ ጊዜ ኋላ ከዚህ ጀምሮ ነው
ታላቁ ምኒሊክ በራስ ምታት ህመም ሲሰቃይ የኖረው
ከእቴጌ ጣይቱ እራፊ ጨርቅ ወስዶ ምኒሊክ ራሱን ማሳመር የጀመረው
ኤፍሬም አፄምኒሊክ ራሳቸው ላይ ለሚያስሩት ሻሽ በገጣሚ ምናቡ ተጉዞ የሰጠው ትርጉም ብዙዎችን አስደንቋል፡፡ ገጣሚው በዚህ ስራው በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ ሴቶች ገሚሱ ፀጉራቸውን በሻሽ የሚሸፍኑት፣ ገሚሱ ጸጉራቸውን ተቆርጠው ጐፈሬ የሚያደርጉትና ሌሎቹ ደግሞ እጅግ በጣም የቀጠነ ሹሩባ የሚሰሩት የውበታቸው መገለጫ የሆነውን ፀጉራቸውን በመጉዳት የአፄ ምኒሊክን ሀዘን ለመጋራት መሆኑን አሳይቷል፡፡ ግጥሙን የቋጨውም “ግን እስከመቼ ድረስ?” በሚል ጥያቄ ነበር፡፡ ገጣሚ ኤፍሬም ከራሱ ወጥ ስራዎች በተጨማሪ 107 የሚሆኑ የግዕዝ ቅኔዎችን በነፃ ትርጉም ወደአማርኛ መመለሱን ገልፆ ከነሱ ውስጥ ሰባት የሚሆኑትን ለታዳሚዎቹ አቅርቧል፡፡ አብዛኞቹ የግዕዝ ቅኔዎች ከብርሀኑ ድንቄ “አልቦ ዘመድ” የተሰኘ መፅሐፍ የተወሰዱ መሆናቸውም ታውቋል፡፡ “ጥንታዊ አባቶቻችን ፈላስፎችም ጭምር ነበሩ” ያለው ገጣሚ ኤፍሬም ይህንን ሀሳቡን ይገልፁልኛል ካላቸው የግዕዝ ቅኔያት መሀል ወደአማርኛ የመለሰው የሚከተለው ግጥም ይገኝበታል፡፡
ብቻውን ለመኖር እግዜርን ቢያስፈራዉ
ከአለመኖር እንቅልፍ ይሄን አለም ሰራው
ገጣሚው የግዕዝ ቅኔያቱን ወደ አማርኛ ሲመልስ ቅኔ ቃል በቃል የማይፈታ እንደመሆኑ እርሱም ይህን እንዳላደረገ ገልፆ ቅኔ ታሪክን፣ ሰምና ወርቅን የያዘ እንደመሆኑ እርሱም ሶስቱን ታሳቢ ያደረገ ስራ መሰራቱን ተናግሯል፡፡ ገጣሚ ኤፍሬም በዚህ አመት እንደአሁኑ አይነት ዝግጅቶች ሲያቀርብ የአሁኑ ሶስተኛው ሲሆን ከዚህ ቀደም የነበረውን ዝግጅት ያቀረበው በድሬዳዋ ከተማ እደነበር ይታወሳል፡፡