ለዳኛቸው ምህረቱ የግጥም መልእክት የተሰጠ ምላሽ
(ተፈራ ድንበሩ ዘብሔረ ኢትዮጵያ ታህሣስ ፳፻፫ ዓ. ም.)
ያልተነካ ግልግል ያውቃል
እንዲየው በደፈናው ሁሉንም ይንቃል፤
ድሮስ ያልቆሰለ ምኑ ይታመማል?
ምኑ ተነካና ምኑ ይሰማዋል?
እንዲየው በደፈናው ይቅር በሉ ይላል።
ይቅርታ መጠየቅ ፍየል ለሠረቀ
ምህረት መጠየቅ ሕግን ላላወቀ፤
በችሎታ ማነሰ ልማትን ላነቀ
ሰው እየሰዯበ በትዕቢት ለሳቀ
በሰው ትዳር ገበቶ ልብሱን ላወለቀ።
የሰው ልጅ እንደሸት
እንደጓሮ አትክልት
በተከተፈበት፤
ፍርድ ሳይገባበት
ገላ በየሜዳው በተነጠፈበት፤
ማዘንና ማልቀስ ተከልክላ እናት፤
ሬሳ ለመውሰድ ዕድል ያጋጠማት
የጥይቱን ወጭ መክፈል ነበረባት።
ዳኘቸው ምህረቱ
እስተውል በውነቱ።
ዳኛ ሳይቀመጥ
ቃሉ ሳይዯመጥ
ሰው ለሞት ሲመረጥ
አንገቱ ሲቆረጥ
ሲጣል ወደረመጥ፤
መንግሥት ቢለወጥ
ሕግም ቢቀያየጥ
በይቅርታ ፈሊጥ
ነፍሰ ገዳይ ያምልጥ?
ለእንዲህ ያለ በደል
ይቅርታማ አይደል፤
እነዲየው ፍርደገምድል፤
ዳኛቸው ምህረቱ
አስተውል በውነቱ።
ፍትህ መድሐኒቱ
ነግ በኔ ማለቱ
መቀጣጫነቱ
እንዳይደግም ጥፋቱ
ሰው እንዳይቀር ከንቱ
እንዲከበር መብቱ።
ሠላም መሠረቱ
በሕግ መዳኘቱ
ተከብሮ እንዲኖር ሰው በሰውነቱ።
ጋሻ ሲሸነቁር
ሲያበላሽ ጦር
ሲያጠፋ ፍቅር
እናትን ሲያስዯፍር
አፍርሶ አገር?
እንዴት ይባል ይቅር?
ባበጃጁት ቀንበር
ራስ መግባቱ አይቀር፤
አሣሪ እንዲታሠር
ፍርድም እንዲቀየር
ተአባይ እንዲያፍር
ሥልጣንም እንዲሻር
እግዜር በማይረሣት
የተፈጥሮ ሥራት
የለም ወድቆ መቅረት
አይቀርም መነሣት።
ይልቅስ መፍጨርጨር
ብዙ እንዳንደርፈር፤
ተያይዘን አንድጋር
እንሁን አጥር
ወይኔ ወይኔ እንዲቀር!
እንዳይበዛ አሣር
ክፉው ቀን እንዲያጥር።