ስለ ራስህ ስትል ይቅር በል!

ከዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

አንዳንድ ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣውን የተሳሳተ ግንዛቤና አስተሳሰብ የተነሳ መንፈሳውያን በሀገራዊ ጉዳይ ላይ መሳተፍም ሆነ የበኩላቸውን (የሚጠበቅባቸውን፣ ድርሻቸውን) መወጣት እጅግ አድርገው አጥብቀው የሚቃወሙና የማይዋጣላቸው ለምን እንደሆነና መሰረተ ሃሳባቸውን ምን እንደሆነ ለመረዳት ካደረግኳቸው ጥረቶች መካከል አንድ በዚህ ጎራ ከተሰለፉ ወገኖች የረጅም ጊዜ የጽሑፎቼን አንባቢና ተከታታይ ከብዙ ጊዜ በኃላ “በኢ-ሜይል” ባድረግነው የሃሳብ ልውውጥ በቅርብ ጊዜ በስልክ ተገናኝተን አውርተን ነበርና አበው “ፀጉር ሲመለጥ ምላስ ሲያመልጥ አይታወቅም” እንዳሉት ለካ ምስጢሩ ይህ ሆኖ ኖሯል።

እናማ ዲያቆን ሲባል የሀገሬ ሰው የለመደውና የሚያውቀው ጥዋፍ ይዞ ሲዞር፣ ቃጭል ሲመታ፣ ሙዳዬ ምጽዋት አነግቶ ጭል ባለች ቁጥር እግዚአብሔር ይቀበልሎት የሚል፣ ከዚህ አልፎ የጎበዘም እንደሆነ ዚኬ ቤት ጠጅ ሲያሰልፍ ነው። ተዉ! ማለት በዲያቆን አንደበትና ብዕርስ ምን አመጣው ነበር ለካ እስከ ዛሬ ድረስ የሚያስፋጨን። ቢሆንም እግዚአብሔርም ቢሆን በልዓምን የመሰለ ሰው ትቶ የመላዕክን ገጽና ድምጽ ለአህያ የመግለጡ ሚስጥር ከአህያ ያነሰ ነቢይ ሲያጋጥመው ነበርና ራዕይን ጥርት አድርጌ አያለሁ ለሚል ሰውዬ ማየት ሲሳነው አህያ ታይለት ዘንድ ማድገሩን ሳስታውስ እንዲህ ዓይነቱ ኃላቀር አስተሳሰብ ዕንቅፋት ባይሆነንስ?

ዲቁና ጥዋፍ ይዞ መዞር ብቻ ሳይሆን ዓለም፣ ሥጋና “ሰይጣን” ግራ ላጋባው ፍጥረት ኮምፓስ፣ ቃጭል መምታትም ሳይሆን ኑሮ፣ ክፉ ምኞት፣ የሥልጣን ጥም ናላውን ላዞረበትና ለተምታታበት ዜጋም ምርኩዝና ኸይ ባይ፣ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” የሚል ጥቅስ የተለጠፈበት መዳዬ ምጽዋት የተለጥፈበት (በመሰረቱ ይህን ጥቅስ በሙዳዬ ምጽዋት ላይ ለጥፈው ለመለመኛ ማዋል ከክህደት በላይ የእግዚአብሔር ቤተ-ክርስቲያንን መሳደብ ነው) ይዞ ይቀበልሎት ማለት ብቻ ሳይሆንም መጽሐፍ “ደፍሮ የሚገጽስ ሰላምን ያመጣል” እንዲል እውነቱን እውነት ውሸቱን ደግሞ ውሸት የሚል በመጨረሻም ዲያቆን ማለት ከዘኬ ቤት የማይጠፋ ጠጅ አሳላፊም ብቻም ሳይሆን እየጠፈጥዎት የሚመገቡት ትምህርተ ሥጋ ወነፍስ አእምሮን የሚያልፍ ሰላም የሚያነግስና የሚያመጣ ቃል (እውቀትን) እንደየ አስፈላጊነቱና የተቀባይ ልብ እየቃኘ የጥበብን ቃል የሚመግብ ዘመን ሲያመጣም በትናንተ አእምሮ እየተመላለስን የሚበጀንን ከመቀበል ንፍጎች ባንሆን ይመከራል “ጥሩ ውሀ የጥቅምት ነበርሽ ማን በጠጣሽ, ጥሩ ምክር የደሀ ነበርሽ ማን በሰማሽ” አይሁብን እያልኩ “ስለ ራስህ ስትል ይቅር በል!” ስል ወደ አዘጋጀሁትን የዛሬ ዕለት መልዕክቴን ላዝግም።

አመሻሹ ከአንዳንድ ግላዊ ዕለታዊ ክንውኖቼ መልስ ነበር ሙቀት ከማይጠፋባት ወንበሪና ለጥቂት ሰዓታት የተለየኃት የላቀ አእምሮ ውጤት የሆነችውን ኮምፒተሬ የተገናኘነው። ነካ ዳበስ ባደረግኳት ቁጥር አዲስ ነገር አስለምዳኛለችና ዛሬም አላሳፈረችኝም አንድ ትልቅና የምስራች የሆነ ዜና (ለእኔ) ይዛ ጠብቃኛለች። የጽሑፉ ርዕስ “ሌ\ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም በፍቃዳቸው ለፍርድ ለመቅረብ ዝግጁ ናቸው…” ብ\ጄ ታመነ ድልነሳው የኮ\ሉ የቅርብ ወዳጅ” የሚል ሲሆን የዜናው ርዕስም የተሰራ የቀድሞ ወታደራዊ የሀገር መሪ ከሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ አንደበት የተገኘ ሳይሆን ከጽሑፉ ለመረዳት እንደቻልኩ ከቅርብ ወዳጃቸው ከሆኑ ከብ/ጄ ታመነ ድልነሳው አንደበት የተገኘ ቃል ነው።

ወደ ዝርዝር ሃሳቤ ከመግባቴ በፊት ይህን ርዕስ አንስቼ ግላዊ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ክርስቲያናዊ አመለካከቴን ለአንባቢዎቼ ለንባብ ሳበቃ አንድ ነገር አስቀድሜ ግልጽ ላደርግ እወዳለሁ። ይኸውም እኔ በእነዚህ ስማቸው ከላይ ከፍ ብሎ በተጠቀሱ ግለ ሰቦች (የሀገር መሪና ከፍተኛ ወታደራዊ ሹም) ዘመን የነበርኩ ዓይነት ሰው አይደለሁም። እንደማንኛው ዜጋ ዕድሜዬ ለንባብ በቅቶ ካገላበበጥኳቸው በርካታ በሀገሪትዋ ሰዎችም (ኢትዮጵያውያን) ሆነ ማተሚያ ቤቶች የታተሙ መጻሕፍት የሀገሬን እና የሕዝቤን ታሪክ ለማወቅ ከነበረኝ እና ካለኝ ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ ለመብረቅ መከላከያ ያክል በጥቂቱም ቢሆን የተቋደስኩትና የሸመትኩት ካልሆነ በቀር ስለ የደርግ መንግሥት ክፋትም ሆነ ደግነት ምንም የማውቀው ነገር አለመኖሩን ለክቡራን አንባቢያን ግልጽ ለማድረግ እወዳለሁ። ይህ ማለት ግን በዘመኑ ስላልነበርኩ ብቻ ጭብጥ ላይ ተንተርሼ ማለት የሚገባኝን ከማለትም የሚያግድ ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ ሕግ አለመኖርን በማከል ነው።

ስለማላውቀው ነገር እየተናገርኩ ነኝ፣ መናገር እችላለሁ እያልኩ እንደሆነም በድጋሚ ክቡራን አንባቢያን ልብ ልትልሉኝ እወዳለሁ እያልኩ ያለኹተይ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርና ፈጠረ ስንል እንደ እውነቱ ከሆነ እግዚአብሔር ሰማይና ምድር ሲፈጥርም ሆነ የሰው ልጅ ዘር የመጀመሪያ ሰው አዳም ለመሆኑ እግዚአብሔር አስቀድሞ አዳምን ብቻ ፈጠረ በማለት ስለ ፍጥረት መጀመሪያ አፋችን ሞልተን ስንናገር ሰማይና ምድር በእግዚአብሔር ለምፈጠራቸውም ሆነ አዳም የሰው ልጅ የፍጥረት መጀምሪያ ለመሆኑ ስንናገር እግዚአብሔር እነዚህ ነገሮች ከአለመኖር ወደ መኖር ሲያመጣቸው የዓይን ምስክሮች ነበርን ማለት አይደለምና ለእንዲህ ዓይነት ታሪካዊ ክስተት የበኩሌን ጠጠር ለመወርወር በመታደሌና በመብቃቴ ከምንም በላይ ደግሞ የምሕረትንም ቃል ለመናገር ኦዱሉን በማግኘቴ አንድ ብዬ ሁለት ለማለት ወደ ሐተታዬ ሳልፍ ደስታ እየተሰማኛ ነው።

የዛሬ ጽሑፍ ዓላማ ስለ ይቅርታ ማለትም ይቅርታ እንዲህና እንዲያ ማለት ነው እያልኩ የአንባቢ ጊዜ መብላትና ፌደል ለማስቆጠር ሳይሆን ይቅር ማለትና አለማለት ከግለሰብ እስከ ሀገር ድረስ የሚያመጣው ለውጥና የሚያስከትልው መዘዝ በአጭሩ ይስቃኛል። ይቅርታ ማድረግ ማለትም ራስህን ለማልካም ነገር ማጨት ሲሆን በአንጻሩ ደግሞ ይቅርን አለማለት ደግሞ ከበሽታነት አልፎ የዕድገትና ብልፅግና ማነቆ እንደሆነ የመልዕክቴ ክፍል ይሆናል። ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ መነሻ የሆነንኝ በጽሑፍ ያገኘሁት ቃለ-ምልልስ ከአንዴም ሦስቴ ከላይ ወደ ታች ከምስራቅ ወደ ምዕራብ በሚገባ እየመላለስኩ እንብቤዋለሁ ዳሩ ግን የንባቤ ውጤት ከደሜ ጋር ለተዋሃደችና ጉሮሮዬ ላይ ወደ ተቀመጠች መጽሐፍ (መጽሐፍ ቅዱስ) አመራኝ። እናም መጽሐፍዋም ተቀብላ ይህን ምዕራፍ አስነበበችኝ “ለራሳችሁ ተጠንቀቁ ወንድምህ ቢበድልህ ገሥጸው፥ ቢጸጸትም ይቅር በለው” (ሉቃ. 17፥3) የሚል የጌታ ቃል።

ይቅር ማለት ያሳርፋል እንጂ አያቆስልም። ዘወትር የሚያደማንና የሚያሳክከን ይቅር ማለታችን ሳይሆን ላይበጀን ቋጥረን የምንይዘው ቂምን እህህ ማለትን ነው። የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው እንዲሁም በብሉያት መጻህፍት “ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፥ ማስተዋልም ይጋርድሃል” ተብሎ እንደተጻፈ በበደል ላይ በደል እያደረሰ ያለውን መንግሥት (የኢህአዴግ) እንገስጸዋለን ነገ አላየሁም አልሰማሁም ዕዱንም አለገኘሁም እንዳይል ያለፈውን ግን አልፎዋልና በበደሉ ቢጸጸት ይቅር ማለት “የክርስትና ደሴት” ተብላ ከምትታወቀው ምድር የተገኘን ዘሮች ይህን ከእኛ ይጠበቃል።

ምንም ይቅርታ ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል የለመድን ዜጎች ብንሆንም በሀገርም ሆነ በመንግሥት ደረጃ ይቅር ማለት በእኛ የተጀመረ ሳይሆን ያለና የነበረ ነው። ፈጽሞ ስህተቱን አምኖ ለተቀበለና እጁ ለሰጠ በምሕረት ማሰናበት የትኛውም የኃይማኖት አስተምህሮ ሆነ በጎ ህሊና ያለው ፍጡር አይቃወምምና። አባት እናቶቻችን ወንዶችና ሴት ልጆቻችንን እንዲሁ በቀላሉ ማጣታችን በእርግጥ ከባድ ሐዘን ነው። ቢሆንም ግን የደማ ልባችን የሚጽናናው ክፉ አድራጊውን ሲጸጸት ይቅር በማለትና በማቀፍ ነውና የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ ይቅርታህን ለሚሻ ወገን ሁሉ ይቅር በል።

የኢህአዴግ ማለት የመላዕክት ቁራጭ (ዘር) ማለት አይደለህም። ይቅር ይህ የተራ ሽፍቶች ስብስብ በእውቀትም በኃይል የታጠቁ ራሳቸውን ከፈጣሪ እኩል እስከማስተካከል ድረስ የዘለሉም ዛሬ ድምጻቸውም አይሰማም። ዓለማችን ከዚህም በላይ ሌሎችን አስተናግዳ ሸኝታለች። ይቅር በል! ኃያላን ይቅር እንደ ፉከራቸው ገዝተው ሊያስገብሩ ዛሬ መቃብራቸው ቢፈተሽ አጥንት ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብም እንደሆነ ነገሩ “እያነቡ እስክስታ” ሁኖበት እንጂ በዛሬ መሰሪና አጥፊው ስራህ (የኢህአዴግ መንግሥትን) ነገ በፍርድ ወንበር ፊት መቆሙህ አይቀርም።

አሁንም ቢሆን ይቅር የቀድሞ ወታደራዊ የሀገር መሪ ያደረጉትንና የፈጸሙትን ድርጊት ለሀገር አንድነትና ለሕዝባቸው ደህንነት ተብሎ በሰዓቱ ትክክል መስሎኝ ያደግኩ ነበር አሁን ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረደኝ ፍርድን ሻለሁ ሲሉ ነገም እንደ ጥላ ማለፉ የማይቀርለት የኢህአዴግ መንግሥትም ቢሆን ነገ ሳይሆን ዛሬ ዓይኑ እያየ ጆሮው እየሰማ መውጣትም መግባትም የሚያስችል ጉልበት ሳለው ተመሳሳይ እርምጃ ቢወስድ ስህተቱን አምኖ የበታተነውን ሕዝብና ሀገር ወደ ቀድሞ መለያዋና አንድነቱ ለመመልሰ ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታም ሳያቀርብ ዜጎች ኢትዮጵያዊነታቸውን ብቻ አምኖ በመቀበል በቅንነት ተቀራርቦ ለጋራ ጥቅም ለመስራት ቢወድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ካልሆነ በቀር ይህ ዕድል የሚዘጋ ምንም ዓይነት ኃይል ሊኖር እንደማይችል ነው የማምነው። ጥፋተኛ ከጥፋቱ ቢፀፀት ከልቡ ምህረት የጠየቀ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅር የማይልበት ምክኒያት የለውም። ይህ ሳይሆን ቀርቶ

o ይህቺ ምድር ይቅርታን የማታውቅ፥
o ለተጸጸተ የማትመለስ፥
o ምሕረትን ለጠየቀ ምሕረት፥
o ይቅርታን ለጠየቀ ይቅርን ማለት፥
o ጥፋቱን አምኖ ለተጸጸተና፥
o አጥፍቻለሁ፣ ስቻለሁና ፍርድን እሻለሁ ሲል ድምጹን ለሚያሰማና ራሱን ላዋረደ አቤት የማትል በምሕረት ዘርዋን የማትቀበል ብትሆን ግን ወልዳ መቅበር ዕጣ ፈንታዋ ይሆናል። መጽሐፍ ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ፥ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና፤ (ማቴ 6፥ 14) ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፥ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም። (ማቴ. 6፥15) እንደሚለው የምድሪትዋ የሕዝብዋ መጨረሻ አጭርና ግለጽ ነው።

ይህ ብቻም አይደለም መጽሐፍ “በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል” እንዲል ግለሰብም ሁን መንግሥት ዛሬ የምንዘራት ዘር ነገ ማጨዳችን አይቀርልንም። ዛሬ ልባችን ብናደነድን፣ ይቅር ማለት ለማናራምደው ሰንካላ ፖለቲካ የሚበጅ ሆኖ ስላታየን ብቻ ለሰዎች የጸጸት ድምጽ በራችሁን ለምህረት በእንጨት መዝግያ ብትዘጉ ነገ በእናንተ ላይ በናስ ብረት ለመዘጋቱ ለአፍታ አትጠራጠሩ። ይቅር ማለት ለማንም አይደለም ይቅር ማለት ለራስ ጥቅም ነው!! ይቅር ስንልንም ስለ ማንን ብለን አለመሆንኑም እርግጠኞች እንሁን። ይቅር ስለ እግዚአብሔር ሳይሆን ይቅር ስለ ራሴ በማለት ይቅር እንበል። ይቅር በማለት ተጎዢም ተጠቃሚም የሚሆነው እግዚአብሔር ሳይሆን ይቅር በማለትና በአለማለት ተጠቃሚዎችም ተጎዢዎችም የምንሆነው እኛው ራሳችን ነን።

በግዕዙም ይሁን በአማርኛ በዜማም ሆነ በንባብ “እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን” (ማቴ. 6፥12) ሲል የሚጸልየውንና የሚናገረውን የሚያውቅ ትልቅም ይሁን ትንሽ ግለሰብም ይሁን ድርጅት በደሉን አምኖ የተጸጸተ ዕለት እሺ በማለት ይቅር ከማለትና ምሕረት ከማድረግ ውጭ ምንም ዓይነት አማራጭ የለውም። ማናችንም ብንሆን ይቅር የፈጣሪና የሰውን ምሕረትና ይቅርታ ባናገኝ የዘመናችን ብዛት በደል ዛሬን ለማየት ባልበቃንና ብላታደልን ነበርን። ዛሬ በሕይወት የመኖራችን ምስጢር ካገኘነውና ከተደረገልን ይቅርታና ምህረት ብዛት የተነሳ ለመሆኑ ስንቶቻችን ነን ልብ የምንለው? እንደ በደላችንና እንደ ሥራችን ቢሆን ኖሮማ ብዙዎቻችን በእናታችን ማህጸን ሳለን የውኃ ሽታ ሆነን በቀረን ነበር። ሰው በተፈጥሮው ተሳሳች ፍጥረት ለመሆኑ ኃይማኖታዊ አስተሳሰብ ብቻም ሳይሆን ከበረት ውጭ በሚገኙ ዘንድም እውነትነት አለው።

ክቡር ዜጋ ሆይ! ዛሬ በምትወስደው እንርምጃና በምትደርሰው ድምዳሜ ነግ በእኔ ላይ ማለት ማስተዋል ነው። የማይሳሳት፣ የሚያደርገውንና የሚሰራውን የሚያውቅ፣ አማካሪ የማይሻ፣ ዘመን የማይቆጠርለትና የማይሽረው፣ ወንበሩ በብዙ ሠራዊትና ትጥቅ የማይጠብቅ፣ ዛሬም ለዘልአለምም ያለ ተቀናቃኝ የሚገዛ፣ ያው የሆነው ፈጥሮ የሚገዛ፣ ምርጫ ቦርድ የማይሻና የማይቋቋምለት ፈታሔና ጻድቅ ገዢ፣ ሰማይን ሰርቶ ምድርን ያጸና አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ሁላችን እንስታለን የሀገር መሪዎች ይሳሳታሉ፣ ወላጆች ይሳሳታሉ፣ ልጆች ይሳሳታሉ በአጠቃላይ ስህተት ለአዳም ዘር የተፈጥሮው ክፍል ነውና በደልን እየቆጠርን ቁልቁል አንውረድ።

ተሳሳች መሆኑን ያልተቀበለና ራሱን ፍጹም አድርጎ የሚቆጥር ሰው ብቻ ይሆናል የሰዎች መሳሳትና መጸጸት የማይገባው። በሌላ አማርኛ አጥፋቻለሁ ማለት የማይገባው ሰው እሱ አጥፍቼም ሆነ ተሳስቼ አላውቅም የሚል ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ውሸታም ያደርገዋል። ደግሞም በቤቱ ለቤተሰቦቹ ምሕረት ማድረግ የተለማመደ አባት በደባባይ ለሌሎች ይቅር ማለትን በደልን ሳይቆጥር በምሕረት ማሰናበትን ዳገት የመውጣት ያክል ከባድ አይሆነውም። የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ሆይ! በድጋሜ አሁንም ሰለ ራስህ ስትል ይቅር በል እንቢ ብትል ግን፥

o ቂመኛ ሕዝብም ሆነ መንግሥት ውርደትን እንጂ ክብርን አያይዋትም፥
o ቂመኛ መንግሥት ዝቅጠትን እንጂ ዕድገትን፥
o አሁንም ጥላቻ የነገሰበት ሕዝብም ሆነ መንግሥት ለቅሶና ዋይታ እንጂ ደስትና ሀሴትን አይቋደስዋትም፥
o አሁንም ደግሜ እላለሁ ይቅር ማለትን ምሕረት ማድረግን የማያውቅ ሕዝብና መንግሥት ብልጽግና ልማትንና ሰላምን በሩቅ ይሳለማትዋት እንሆነ እንጂ አይቀምስዋትምና የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! በቀል የእግዚአብሔር ነው በማለት (አልተጎዳህም ሰለባ አልሆንክ ማለት ሳይሆን) ነገርህን በውኃ ላይ ጣለው። እያኮመሳህ ማኘክ የክብት ባህሪ እንጂ የሰው ልጅ ስብዕና አይደለምና ስለ ራስህ ስትል ይቅርታህን ለሚሹ ይቅር በል። ብትለቅ ይለቀቅልሃል ነክሰህ ብትይዝ ደግሞ እሄው መደማመጥ አቅቶህ እንደ ጅብ እርስ በርስ እየተነካከስ ማየት የሚገባህን ሳታይና ለተፈጥሮህ ያልተገባህን ሁነህ እንዲሁ ታልፋለህ።

በመጨረሻ ይቅርታን ለማያውቅ ሕዝብ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታን አገኛለሁ ብሎ እንዳያስብም ይጠንቀቅ። ምሕረትን ተለምኖ አሻፈረኝ ለሚል ሕዝብም ሆነ መንግሥት ወዮ! በመፈራረሳቸው ምክንያት ለጥገና ደፋ ቀና የምንልባቸውን ገዳማትም እንደሆነ ቱሪስት ይጎበኛቸው እንደሆነ እንጂ እግዚአብሔርንም ማንን አገኛለሁ ብሎ ዓይኑ ይጥልባቸዋል። መጽሐፍ “ልበ ንጹሐን እግዚ አብሔርን ያዩታል ሲል እኮ ልበ ልጽሐን ማለት ምን ማለት ነው በማለት የጠየቀን እንደሆነ በልባቸው በደልን የማይቆጥሩ ቸሮችና ይቅር ባዮች ማለት ነው። እንደው በቁማርተኛ ሕዝብና መንግሥትማ የእግዚአብሔር ቁጣ በላይ ይጤሳል ይህም ብቻ አይደለም በመጽሀፍ የተጻፈ እርግማንም ሁሉ በእነርሱ ላይ ይኖራል እግዚአብሔርንም ስሙ ከሰማይ በታች ይደመስሰዋልነው የሚለው መጽሐፉ። ጥበብ በዚህ አለ! በአንድም በሌላም ምክንያት የሰው ልጅ አፈር መልብሰ አይቀርምና ተበድለንም ቢሆን ምሕረት ለለመነ ምሕረታችንን አንንፈገው። ስለ ራሳችን ስትል ይቅር እንበል! ልቀቅ!! እንቢ ብትል ግን በሰፈርከው መስፈሪያ ይሰፈርልኃል። አዎ!

+ ቂም አርግዘህ ዕድገት
+ ጥላቻ ታጥቀህ ለውጥ
+ መራራነትን አዝለህና ተሸክመህ ክብርና ዕረፍት እንዳታልመው!! ምንም ያድርግ ምን በደሉን አምኖ ለተጸጸተ ምሕረትን ማድረግ የመሰለ ነገር የለም።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
[email protected] (USA)