በኖርዝ ካሮላይና ኢትዮጵያዊነት ምሽት ከአርቲስት ታማኝ በየነ ተከበረ
በሻርለት ኖርዝ ካሮላይና አካባቢ ታይቶ በማይታወቅ መንገድ የአንድ ኢትዮጵያዊነት ምሽት አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ በተገኘበት ቅዳሜ September 18, 2010 (መስከረም ፰ ቀን ፪ሺ፫ ዓ.ም. ) በታላቅ ድምቀት ተከበረ።
ይህ ምሽት የአዳራሹ ውጭና ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለዝግጅቱ መጠቀሚያ የነበሩትን ቁሳቁስ አካቶ ማንኛውም ነገርና በአዳራሹ የተገኘውን ታዳሚ ጨምሮ በሚያውለበልበው ሕጋዊ ሰንደቅ ዓላማችን የተንቆጠቆጠ ስለነበር ለትልቁ የአንድነት ዓላማችን ከፍተኛ ድምቀትን የሰጠ ነበር።
የዕለቱ ፕሮግራም ከመጀመሩ በፊት ሕዝቡ የአንድነትንና የነፃነት አስፈላጊነትን በሚያወድሱ ዜማዋች አማክይነት ከዚህ ከስደት ኑሮ ውጣ ውረድ ወጣ በሎ በዓይነ ሕሊናው የኢትዮጵያችን ችግር ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ለማሰብ ጊዜ ሰጥቶት ነበር ማለት ይቻላል።
የፕሮግራሙ መጀመር የሚጠበቀው በአርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ መመጣት ስለነበር ሕዝቡ አይበገሬ ኢትዮጵያዊውን ለመቀበል ከመቀመጫው ተነስቶ በጭብጨባ፣ የኢትዮጵያችን ሰንድቅ ዓላማ (አረንጓዴ ቢጫ ቀይ) እና የአሜሪካን ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብ ሲጠብቀው ለነበረ ታዳሚ ምን ያህል የአገር ስሜት በውስጡ እንዳጫረ መገመት የሚያስቸግር አይሆንም።
ሻለቃ ደምሴ ዮሐንስ የዕለቱን ፕሮግራም ዝርዝር ከማሰማታቸው በፊት ለኢትዮጵያ አንድነትና ለሕዝቧ ነፃነት ሲሉ በተለያየ ወቅት ውድ ሕይዎታቸውን መስዋዕት ላደረጉ የኢትዮጵያ ልጆች በአንድ ደቂቃ የሕሊና ፀሎት እንድናስታውሳቸው አደርጉን። ከሕሊና ፀሎት በኋላ የምሽቱን ዝርዝር ፕሮግራም አስተዋውቀው የዝግጅት ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶ/ር ሰሎሞን ጉግሳን የመግቢያ ንግግር እንዲያደርጉ በመጋበዝ የምሽቱን ስነስርዓት መከፈቱን አበሰሩ።
ዶ/ር ሰሎሞን ጉግሳ የምሽቱን የክብር እንግዳ አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነን፣ ብርቱካንንና ሌሎች የሕሊና እስረኞችን ለማስፈታት በሚደረገው ትግል የጎላ አስተዋፀኦ የሚያደርገው የፍሪ ብርቱካን ግብረ ሃይል ሰብሳቢ አቶ ግርማይ ግዛውን፣ በውብና ቀስቃሽ ግጥሙ ኢትዮጵያውያንን ሲያነቃቃ ላመሸው ወጣት ሄኖክ የሺጥላ፣ የጅግኖች ምሽት ኮሚቴ ተወካዮችን፣ በዚህ ዝግጅት ለመገኘት ርቀት ሳያግዳቸው ከተለያየ ስቴት (ከአትላንታ፣ ከኖርዝና ሳውዝ ካሮላይና፣ ከዲሲ፣ ካሊፎርኒያ፣ወ.ዘ.ተ.) ለተገኙ ኢትዮጵያውያንና በአዳራሹ የተገኙም ሆኑ ለመገኘት ፈልገው በተለያየ ምክንያት ላልተመቻቸው ኢትዮጵያውያን በሙሉ ምስጋና በማቅረብ ንግግራቸውን ጀመሩ።
በመቀጠልም ስለ አገር ምንነት ከታሪክና ምሳሌ (ሶስተኛ መጽሐፍ) በማጣቀስ በአሁኑ ወቅት የአገራችን ጥያቄ የነፃነት ጥያቄ መሆኑን አስገንዝበው፤ የአቅማቸውን አስተዋፀኦ ለማድረግ ምክንያት ለሚደረድሩ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ግን አንድም ፍራቻ ሌላም አለመረዳት አለበለዚያም ጭልጥ ያለው ሆዳምነት እንደሚይዛቸው አስገንዝበው ከዚህ እንዲላቀቁ ምክራቸውን ለግሰዋል።
በሻርለት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስብስብ መሰረቱ ኢትዮጵያዊነት መሆኑን ካስረዱ በኋላ ኢትዮጵያውያን ተሰባስበን ሀገራችንን ማዳን ሊለያይን የማይገባና ኢትዮጵያን በማፈራረስ ላይ ከሚገኘው ዘረኛ ጨቋኝና አፋኝ የወያኔ መንጋጋ ኢትዮጵያችንን ማላቀቅ የምንችለው የተጋረጠብንን መጋረጃ በጣጥሰን በመውጣት አንድ ላይ ስንሰባሰብ ብቻ መሆኑን ገልፀዋል። ይህን ዕውን ለማድረግ የእያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊነት ዕምነትና ክብራችንን ማሰብ በቂ መሆኑን አስገንዝበው፤ ሆኖም በተለያዩ ሰንካላ ምክንያቶች በማቅረብ የማሰቢያ ዕድሉን ለራሳችን የነፈግንም ሆንን በተበታተነ መልኩ ድጋፋችን ስንሰጥ የቆየን በሙሉ በአንድ ኢትዮጵያዊነት እንድንነሳ ያስፈልጋል በማለት ጥሪ አቅርበዋል።
በንግግራቸውም መሃከል የምሽቱን ዓላማ ሲገልፁ፤ በኢትዮጵያችን ነፃነትና ፍትህ አንዲገኝ በዓዲስ ዓመት በአንድነት ለመታገል ቃል መግባት ነው ካሉ በኋላ፤ ቃል ስንገባም የሚከተሉትን ቁልፍ ጉዳዮች ግንዛቤ ውስጥ በማካተት ነው ብለዋል 1. ለኢትዮጵያ ነፃነትና አንድነት ሲሉ ሕይዎታቸውን ያሳለፉትን ዕልፍ አዕላፍ ኢትዮጵያውያንን በማስታወስ፣ 2. ሰብዓዊ መብቱና ነፃነቱ ተገፎ በዘረኛው አስተዳደር የሚሰቃዬውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በማሰብ፣ 3. የፅኑ ዕምነት ተምሳሌትና የነፃነት ታጋይ ኢትዮጵያዊት ብርቱካን ሚዴቅሳንና ሌሎች የሕሊና እስረኞች የሚንገላቱት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን እንደሆነ በመገንዘብና 4. ታፍኖና ተረግጦ የሚኖረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃ ለማውጣት ዘረኛውን አስተዳደር ባስፈላጊው ዘዴና ስልት ሁሉ ለመታገል ቁርጠኝነታችንን በተግባር ለመግለፅ በማቀድ ነው።
ከመግቢያ ንግግሩ በኋላ ወጣት ሄኖክ የሽጥላ “ገበሬው ምን ነካው” በሚል ርዕስ ስለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ሲሉ የሞቱላትን አሁን ካለነው ትውልድ ጋር በማነፃፀር የኛን ወኔ አልባነትን ምን ነካው፣ ሀገሬን ምን ነካት፣ በሚል ያቀረበው ግጥም ልዩ ስሜትን በማጫሩ ለወጣቱ ሄኖክ የነበረው አድናቆት በጭብጨባ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ከመቀመጫው በመነሳት ልዩ አክብሮቱን ለግሶታል።
ወያኔ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ በተለያዬ ወቅት በተለያየ አካባቢ ስለፈፀማቸው ግድያዎች ከተለያዩ ድረ ገፅ የተገኘውና አጠር ባለ መልኩ የተቀነባበረው ዶኪመንተሪ ታይቷል። ይህ ዶኪመንተሪ የወያኔ ስርዓት አስከፊነትና የኢትዮጵያን ሕዝብ ስቃይ ከማሳየቱም በላይ በወያኔ አመለካከት የማይፈልገው እስከሆነ ድረስ የሰው ዘር ማጥፋት ድረስ እንደሚጓዝ ያሳዬ በመሆኑ፤ በመሰርቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥይቄ የነፃነት ጥያቄ እንደሆነ በግልፅ እንድንገነዘብ አድርጓል።
በመቀጠል የፅኑ ዕምነት መሰረትና የነፃነታችን ታጋይ ብርቱካን ሚዴቅሳና ሌሎች የሕሊና ዕስረኞች እንዲፈቱ የሚንቀሳቀሰው የፍሪ ብርቱካን ግብረሃይል ሰብሳቢ አቶ ግርማይ ግዛው ስለ ብርቱካን ዘርዘር አድርገው አቅርበዋል።
በንግግራቸውም ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ ምንም ወንጀል ሳይኖርባቸው ለሁለተኛ ጊዜ ዕስር ቤት ከተወረወሩ 627 ቀናትን ማሳለፋቸውን ጠቅሰው ስለልጇ ሃሌና ስለእናቷ ጭንቀትና ሃዘን እጅግ በሚነካ
መንገድ አቅርበውታል። የብርቱካን መታሰር አግባብነት እንደሌለው ካስረዱ ብኋላ አቶ መለስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚቀርብላቸው የብርቱካን መፈታት ጥያቄ እንድሚያገሸግሻቸው ጠቁመው ምክኒያቱን ሲገልፁ፤ የሕግ የበላይነት ጠንካራ ዕምነቷ፣ በዕምነቷና በራዕዩአ የወጣቱን ቀልብ በመሳብ የለውጥ ተቀባዩን ትልቁን የሕብረተሰብ ክፍል ማሰባሰቧ፣ ምንም የኋላ የፖለቲካ ኮተት የሌላትና በስቴት ዲፓርትመንት በአምንስቲ ኢንተርናሽናል በሰብዓዊ መብት ተከራካሪዋችና በተላያዩ አበይት የዓለም መገናኛ ዘዴዎች ስለብርቱካን መወሳቱ ናቸው ብለዋል። ብርቱካን ከመታሰሯ በፊት የተናግረችውን በማስታወስ ከቤተሰቤና ከነፃነት እንድመርጥ ቢያስፈራሩኝም ነፃነቴን መርጫልሁ ብላ የዕስር ቤቱን ፅዋ መቀበሏ ጥንካሬዋን ከማሳየቱም በላይ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ዳግማዊ ጣይቱና የኢትዮጵያ ማንዴላ የሚል ስያሜ ማግኘታቸውን አውስተዋል። በመጨረሻም ነፃነት የትግል ተሳትፎ እንደሆነ ጠቁመው በመጨርሻም የብርቱካንን አባባል “እኔ በመንፈስም በራዕይም ጽኑ ነኝ እናንተስ?” በማስገንዘብ ንግግራቸውን ድምድመዋል። ከዚሁ ተከትሎ ወ/ት ብርቱካን በተለያየ ወቅትና ቦታ የተናገሩትን በማሰማት የብርቱካን የነፃነት ትግል የኢትዮጵያ ነፃነት ትግል እንደመሆኑ መጠን አስፈላጊው ትኩረት ተሰጥቶት አምሽቷል።
የክብር እንግዳችን አርቲስት ታማኝ በየነ ከመናገራቸው በፊትና ከወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ የነፃነት ትግል ተምሳሌነቷ ዝክር በኋላ ወጣት ሄኖክ ለሁለተኛ ጊዚ ወደ መድረክ በመጋበዝ ድንቅ የሆነ ግጥሙን አሰማን። የግጥሙ ርዕስ ጎንደር ደብረብርሃን ሥላሴ ከነበሩ አንድ አባት አባባል በመነሳት የገጠምኩት ነው ያለውን “ይህን ለማየት ነበር” የሚለውን ግጥም ነበር። ግጥሙን ሲያሰማን የነበረውን ጥልቅ የሕዝቡን ስሜት ላየ ከግጥሙ ጥልቅ መልዕክት በተጨማሪ እሰየው አሁንም ኢትዮጵያ ጠንካራና አርቆ አሳቢ ወጣቶች አሏት፤ መለስ የሚያራምደው እኩይ የመበታተን ዓላማ የማይሳካ ለመሆኑ በድጋሚ የተረጋገጠበት ምሽት ነበር።
በሕሊና ፀሎት የተጀመረው ሰብሰባችን ከዚህ በላይ ከተወሱ አንኳር አንኳር ጉዳዮች በኋላ ነበር የዕለቱ የክብር እንግዳችን በኢትዮጵያዊነታቸው ዕውነቱን ከመናገር የማያፈገፍጉ ወንድማችን አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ንግግራቸውን እንድናደምጥ የተጋበዝነው። የወንድማችን ታማኝ በየነ ንግግር የተጀመረው ከተለያዩ ድረ ገፆች ያገኘናቸውን አቀነባብረን በተለያዩ ግዚያትና ቦታዎች (ኢትዮጵያም አዚህ አሜሪካም) ሰለ አገር ጉዳይና ስለ ሕዝብ አንድነት ያደረጋቸውን ንግግሮችና ቃለመጠይቆች ዶኪመንታሪ በማስቀደም ነበር።
አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ንግግራቸውን ሲጀምሩ “ሁሉንም ማድረግ የሚችል ውለታው መከፈል የማይችል ምንም ማድረግ የሚችል ሃያሉ አምላክ እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ለሱ ይድረስ” በማለት ነበር። በማስከተልም ለኢትዮጵያ ሲሉ የወደቁ በዙ አርበኞች፣ ኢህአፓ እየተባሉ ከቤታቸው ታፍነው ተወስደው የተገደሉ፣ መኢሶን ተብለው የወደቁ፣ አገራችሁ ነው ኑ ዝመቱ እየተባሉ በየበረሃው ወድቀው በቀሩበት፣ በወያኔ ዘመንም በግፍ በተጨፈጨፉት ሰማዕታት ዓይን እኔ ምንም አይደለሁም ይህ ሁሉ ክብር የሚሰጠኝ፤ ነገር ግን ያ ሁሉ ዕልፍ ዓዕላፍ ሕይዎቱን በሰውሏት ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ስም ግን እቀበለዋለሁና በጣም እግዚአብሔር ይስጥልኝ ሲሉ የነበረው ጭብጨባ ለአንድነታችንና ለኢትዮጵያዊነታችን ዛሬም መንፈሰ ጠንካራነታችንን የሚያሳይ ነበር።
አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ በጣም ዘርዘር ያሉ የአገር ጉዳዮች፣ የነመለስ አስተዳደር አስከፊ ስራዎችና ስለነፃነት ታጋዮች አስረድተዋል። ከብዙ በጥቂቱ የሚከተለውን ብለዋል። የኢትዮጵያ ገበሬ የዕኩልነት መብት እንዲረጋገጥ ዘራቸውን ሳይጠይቁ በአንድ ኢትዮጵያ ስም ተቃቅፈው የወደቁ ለዚህም እኮ ብለው ወደ ጫካ (አሲምባ) ሲገቡ ሕውሃት (ይህ ጠባብ ቡድን) እኮ ነው ምን ልታረጉ መጣችሁ ብሎ የጨፈጨፋቸው፤ የዘር ጣጣ ያመጣብን ቡድን ነው። ታሪካችንን መርሳት የለብንም። ወደ ዘር ስንገባ ትንንሽ ነው የምንሆነው፤ ወያኔ እኮ ሰው ስንሆን ኢትዮጵያዊ ስንሆን አይወድም ኢትዮጵያዊ ሰው ነኝ እንበለው፣ ላገዛዙ ለዕኩይ ተግባሩ ዕምቢ እንበለው። ብርቱካንን እኮ ለምን ያሰራት ይመስላችኋል? ሁላችንም ቀጥ በሎ ለመቆም ሲያቅተን አጥንት አጥተን ስንወዛወዝ ስንገዳገድ አጥንት ኖሯት ስለተገኘች ዕምቢ ለዕውነት ስለአለች እኮ ነው። እስከመቼ ነው እየፈራን የምንኖረው እየፈራን አድገን እየፈራን ልንሞት ነው? እረ ይህ ነገር ይብቃን በማለት ሲይስረዱ፤ በውስጣችን ያለው ኢትዮጵያዊነታችን ጎልቶ እንዲወጣና አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ያነሳሳን ድንቅ ንግግር ነበር።
አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ብዙ ብዙ ጉዳዮችን ዳሰዋል። ስለ ሃይማኖት አባቶች ለዕውነት መቆም፣ ስለፍርሃታችን፣ ምንም ሳናደርግ ስለመተቸታችን፣ አስተዋፃኦ ላለማድረግ ምክኒያታችንን፣ ስለአድርባዮች፣ ው.ዘ.ተ. አንስተው በሰፊው አስረድተዋል። ስለነመለስ ቡድን አረመኔያው ተግባር የሰውን ልጅ በዘሩ ብቻ በመልቀም ሜዳ ላይ እንድ ቆሻሻ የሚደፋ በአንፃሩ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ስንቅ በዘዴ በማቀበል አልቅሶ የሚሸኝ መሆኑን ከማስረዳታቸውም በላይ አገራችንን በመግዛት ላይ ያለው የዘረኛው ቡድን ሕውሃት ለመሆኑ በመረጃ በተደገፈ ቅንብር ማሳየታቸውና አቶ መለስና ቡድኑ ዛሬ የተናገረውን ነገ ጨርሶ የሚሸመጥጥ ለመሆኑም በመረጃ አስደግፈው ገልጸዋል።
አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ የደርግም ሆነ የወያኔ አስተዳደር ከዚያም አልፎ የተቃዋሚ መሪዎች እንኳ ሳይቀሩ ይቅርታን ለማድረግ የሚሳናቸው መሆኑን በፊልም በተደገፈ መረጃ አቅርበው፤ ባጠቃላይ እኛ ኢትዮጵያውያን ባህሪ ይቅርታን ማድረግ ብቻም ሳይሆን ወደ አእምሮአችን ተመልሰን ቁጭ ብለን መነጋገርን በተግባር ማሳዬት ካልቻልን ችግራችን እየሰፋ ኢትዮጵያችንን የሚያዳክም መሆኑን በአንክሮ አስገንዝበዋል። አያይዘውም አንዳንድ የተቃዋሚ መሪዎች ቢያሳዝኑንም ከምናደርገው አገር የማዳን አስተዋፀኦ ልንገታ እንደማይገባን ጠቅሰው፤ ዝም ብሎ ኖሮ መሞት እንዳይሆን ያቅማችን አድርገን የሕሊና
ዕረፍት እንኳን አግኝተን እንድናልፍ ጥረት ማድረግ እንዳለብን አስገንዝበው ኢትዮጵያውያን በዚህ በካሮላይና ላደረጉላቸው አክብሮት ከልብ አመስግነው ንግግራቸውን ድምድመዋል።
አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ቁምነገሩን አንዳንዴም በቀልድ መንፈስ ስላቀረቧቸው በሕዝቡ ዘንድ ትልቅ ስሜትንና ደስታን ፈጥሮ ነበር ያመሸው።
ከወንድማችን አርቲስት አክቲቪስት ታማኝ በየነ ንግግር በኋላ የምሽቱ ዋነኛው ክፍል ከተደመደመባቸው አንዱ ክፍል ወጣት ሄኖክ የሽጥላ “በቅሎ” በሚለው ግጥሙ አንዴት ወያኔ በሚያራመደው የጎጥ ፖለቲካ ወጥመድ መተብተብ ምን ያህል ማነስና ለአገራችን ውድቀት መተባበር እንደሆነ የሁላችንንም የትውልድ ቦታ በመጥቀስ እንዲሰማን አድርጎ ያቀርበው ደግሞ ድንቅ ስራው ነበር። እንደውም ከተሳታፊ ኢትዮጵያውያን አንዱ “በሕይወቴ እንደዚህ ደስ እያለኝ የተሰደብኩበት ግጥም የለም” በማለት ከምሽቱ መገባደድ በኋላ በቀልድ መልክ የሰጡት አስተያየት የግጥሙን ጥልቀትና መልዕክት ያስገነዘበ ነበር።
ከማጠቃለያው በፊት ከታዳሚው የብርቱካንን ማስፈታት ጉዳይ እና ኢሳትን በመርዳት እንዴት ወገናችንን መርዳት እንደሚቻል ማብራሪያ ተጠይቆ ነበር። ብርቱካንን በሚመለከት አቶ ግርማይ ግዛው የፍሪ ብርቱካን ግብረሃይልን የዌብ ሳይት አድራሻና ስልክ ቁጥር የመሳሰለውን በማስተዋወቅ ማንኛውም ሰው አስተዋፀኦ ማድረግ እንደሚችል ጠቁመዋል። አርቲስት ታማኝ በየነ ደግሞ ኢሳትን በሚመለከት የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ያህል ነፃነቱ እንደጠማውና ከዛቺው ምናልባት በቆሎ ከሚገዛባት ቆጥቦ ዲሽ እንድሚፈልግ በጣም በርቀት ከሚገኙ የኢትዮጵያ የገጠር ክፍሎች መልዕክት እንደሚገኝ በማብራራት እዚህ ስታር ባክስ ሂደን የምናጠፋውን የቡና መግዣ በትንሹ አስር ብር ቃል በመግባት ኢሳትን በኢንተርኔት መከታተል ያለውን ጠቀሜታ አስረድተዋል። በነገራችን ላይ የዚህ ምሽት አዳራሽም ውስጥ ከሚገኘው የሰንደቅ ዓላም ውበት በተጨማሪ የብርቱካን ሚዴቅሳ ምስልና አባባል እንደዚሁም የአሳት ምልክትና የድረ ገፁ ምስል በየቦታው መታየቱ ራሱ ትልቅ የማስታወቂያ ስራ ነበር።
የዚህ ምሽት ዋነኛው ክፍል ማሳረጊያ ደግሞ ስንጠራው ያለምንም ማቅማማት የፈለጋችሁኝ ቦታ ባስፈለጋችሁ ግዜ እግኛለሁ ብለው አክብረውን ለተገኘልንና ይህንን ትልቅ የኢትዮጵያውያን ምሽት ዕውን እንዲሆን ምክኒያት ለሆኑት ውንድማች አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ጋር እንዳንረሳሳና የነፃነትና የአንድነት ትግሉን እንዲገፉበትና እንድንገፋበት ማስታወሻ ተበርክቶላቸው ተደምድሟል።
ይህ ስብሰባ በፀሎት ያስጀመሩልንንና የዛሬውንም የቪዲዮ ሪከርድ የመሩልን እንዲሁም ይህ ዝግጅት እንዲሳካ ከሀገር ወዳደ ኢትዮጵያውያን በሻርሎት ወንድሞቻቸው ጋር በመሆን ደፋ ቀና ሲሉ የከረሙትና በኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ለእናት አገራችን ኢትዮጵያ የሚችሉትን ሁሉ ያበረከቱ ወንድማችን ሻለቃ ደምሴ ዮሐንስ ከተለያዩ ስቴቶች የመጡትን በማመስገን ይህ ዋነኛ የምሽቱን ስብሰባ አሳርገው ቀሪውን ጊዜ የመዝናኛ እንዲሆን ከፍተውልናል። በመጨረሻም ይህ ምሽት እንዲሳክ ለተባበሩን የመግናኛ ብዙሃን እንደ አዲስ ድምፅና አትላንታ ሬዲዮ እንዲሁም የከረንት አፌርስና የኢትዮጵያን ሪቪው ድረ ገፆች ምስጋና ተደርጎ ቀሪው ምሽት የኢትዮጵያውያን የርስ በርስ ይበልጥ መተዋወቅያ መነጋገሪያና መደሰቻ ሆኖ ለወድፊት ፍቅራችንና አንድነታችን ተጥናክሮ የምንመኛትን ኢትዮጵያ ለማምጣት የሁላችንም ጥረት እንዲሆን ለመዝናኛው አንድ ሰዓት ተጨምሮ ተጠናቋል። በራት ስዓትም ሆነ ከስብሰባው መጀመር በፊትና ለዚህ መዝናኛ ጊዜ በሙሉ ድምፃዊ ሰሎሞን ሲያዝናኑን አምሽተዋል። ከበስተጀርባ ይህ ዝግጅት ውበት እንዲኖረው ከአዳራሹ ዝግጅት ጀምሮ ስብሰባውም ሆነ መዝናኛው ሲካሄድ በምስልም ሆነ በድምፅ ቅንብር የኮሚቴ አባላትን በማስተባበር ደፋ ቀና ሲሉ ያመሹት አቶ ተስፋ ጋሻረባ ምስጋና ይገባቸዋል።
በዚህ አጋጣሚ ይህ ዝግጅት እንዲሳካ ጥረት ላደረጉ የአስተባባሪ ኮሚቴ አባላት በሙሉና ምግብ አዘጋጅተው ላስተናገዱ እህቶች ብቻ ሳይሆን በዚህ ጉባኤ ላይ ከወንድሞቻቸው ጋር ተገኝተው ላበረክቱት ጉልህ አስተዋፃኦ የኢትዮጵያ ባለውለታ ናቸውና ትልቅ ምስጋና ይገባቸዋል። ከዚህ በተረፈ የተብራራውንም ሆነ ያልተብራራውን ጉድይ በሙሉ ከዚህ በታች ባለው ስዕላዊ መግለጫ ይመልከቱ።
