ንዴትን መቆጣጠር ይቻላል?
ሰው ሆኖ የማይናደድ የለም። ንዴት የተፈጥሯችን አንዱ አካል ቢሆንም በአግባቡ ካልተያዘ ሊያስከትል የሚችለው ጥፋት የትእየለሌ ነው። ለአብነት ያህል ወጣት እያለሁ ግራኝ እንደተከለው ድንጋይ መሠረቱ የጠና ትዳር በንዴት ጦስ እንዴት እንደፈረሰ ላውጋችሁ።
ነገሩ እንድህ ነው። በባልና ሚስት መካከል በተፈጠረ ንትርክ ሚስት ደሟ ተክ ይልና ባል ለተወሰኑ ደቂቃዎች የቡጢ፣ ቡጥጫና ጥፊ ሰለባ ሆኖ ይቆያል። ያለወትሮው በሚስቱ ላይ ድንገት በተቀሰቀሰው ንዴት ግራ የተጋባው ባለቤቷ” እባክህ ወንድሟን ይዤ እስከምመለስ በህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳታደርስ ጠብቅልኝ” ብሎኝ ወጣ።
ደህና ሲታጣ ይመለመላል ጎባጣ ሆኖ ነው እንጅ ባልና ሚስት ሲጣሉ በገላጋይነት ለመግባት የሚያስችለኝ ክህሎት ኖሮኝ አይደልም። መቼም አደራ ከሰማይ ይርቃልና በራሷም ሆነ በንብረት ላይ ጉዳት እንዳታደርስ በተቻለኝ ለመከላከል የመንፈስና የአካል ዝግጅት አደረግሁ። እኔና እሷ ብቻ ነን። አምርራ ታለቅሳለች። የብር እንክብል ከሚመስሉት ዓይኖቿ ያለማቋረጥ የሚወርደው እምባዋ እንኮይ የመሰሉ ጉንጮቿን አረስርሶታል። ኩርፋድ ከምትስቅ ቆንጆ ሴት ስታለቅስ የሚያምርባት መሆኑ ፍንትው ብሎ የተገለጸልኝ ያን ዕለት ነው። ይሁን እንጅ ሆድ ሲብሳት ማየት ከፋኝ፣ ልቅሶዋ አስጨነቀኝ። ምን ብዬ እንደማረጋጋት ጠፋብኝ። ኧረ አይገባም ተረጋጊ የሚል ቃል ሳላስበው ካንደበቴ አፈትልኮ ወጣ። ምክር ቢጤ መሆኑ ነው። በልቅሶ የቀሉት ዓይኖቿ ከረከቦቱ ላይ በድንገት ተተከሉ። ጀበናና ስኒ በረከቦትፓራሹት ወደላይ መጠቁ፤ የስበት ህግ ሆነና ከጥቂት ሰኮንዶች ቆይታ በኋላ በወለሉ ላይ ተከሰከሱ፤ እነዚያ በኢትዮጵያዊ ከናፍር ተመጥነው የተሰሩ የባህር ማዶ ስኒዎች አመድ ሆኑ። ጥፋት አንድ።
እጆቿን በመጨምደድ ተማጸንኩና አስቀመጥኳት። ልመናዬ ልቧን ገዝቶት እንጅ በጉልበት እንደማልችላት ገምታኛለች። ግራ ተጋባሁ። የምይዘውና የምጥለውን ሳጣ የስኒ ስብርባሪውን አጎንብሸ መልቀም ጀመርኩ። እሱ ላይ ስንደፋደፍ በቁና ሞልቶ የተቀመጠ በርበሬ ላይ አንድ ባልድ ውሃ ቸለሰችበት። ጥፋት ሁለት። ምን ይሆናል ለፋሲካ የተዘጋጀ ነበር ሳልደርስለት ቀረሁ።
እንደልማዴ ዕጅና እጇን ይዤ ኤሎሄ ብዬ ለመንኩና ከአልጋዋ ጠርዝ ላይ እንደገና ተቀመጠችልኝ (አስቀመጥኳት ማለቱ ትዝብት ላይ መውደቅ ይሆናል ብዬ ነው)። የቤቱ ወለል በርበሬ ሳይሆን የበሬ ደም የፈሰሰበት መሰለ። ከዚህ በኋላ አንዲም ጥፋት እንድትፈጽም መፍቀድ የለብኝም ብዬ ለራሴ ቃል ስገባ ብዙ ወጭ የተደረገበት የሳሎን ጠረጰዛቸውን በምሳር ከሁለት ተረከከችው። ጥፍት ሶስት።
እንጨት እንደዋጠ በቆምኩበት ተገትሬ ቀረሁ፤ ጭንቅላቴን የከፈለችው መስሎ ተሰማኝ። ምሳር ቀልድ አያውቅም። በተወለድኩበት አካባቢ በምሳር የጠፋውን ነፍስ ቤት ይቁጠረው። ልቤ በፍርሃት ራደ፣ ማምለጥ እንደሚሻል ተሰማኝ፤ አድሬናሊን በደሜ ውስጥ በእጅጉ ጨመረ።ነፍሴን እታደጋት ዘንድ በሩን በፍጥነት ከፈትኩና እንደ ቀስት ተወርውሬ ወጣሁ።
በግምት ከአንድ ሰዓት በኋላ ባሏ ወንድሟን ይዞ ተመለሰ። የሠፈሩ አየር በተቃጠለ ጨርቅ ሽታ ታጅሏል።የቤቱን ዕቃ ሰብራ ስትጨርስ ፍቅራቸው በደራበት ወቅት ለባለቤቷ የገዛችለትን ሸሚዞችና ሶሪዎች እንደጧፍ አቀጣጠለቻቸው። መቼም ሲያልቅ የሚያምር ነገር የለም። በዚያው ዕለት ከወንድሟ ጋር ቤቷን ለቃ ወጣች። አልተመለሰችም። ብዙ የተለፋበት ጎጆ ባንድ ቀን ጀምበር ፈረሰ። እኔም አደራዬን በላሁ፤ የአስታራቂነት ሞራሌም ከባህር ጠለል በታች ወርዶ ቀረ።
ህብረተሰባችን ንዴን አስመልክቶ የተጻፉ ምርምሮች ተጠቃሚ ቢሆን ኖሮ ምናልባት የዘመን ጅረት ሊያደብዝዘው ያልቻለው ከላይ የገለጽኩላችሁ አለመግባባት ከርሮ ሳይበጠስ መፍትሄ ያገኝ ነበር። ንዴት በቁጥጥሩ ስር እንዳያውለን እንዴት መቆጣጠር እንደምንችል የሚያስረዳ ጠቃሚ ምክር በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተጽፎ ሳገኘው የልጅነቴ ገጠመኝ አገረሸና በአማርኛ ቢተረጎም ኢዮጵያውያን ይጠቀሙበታል ብዬ ገመትኩ። ወከባ በበዛበት፣ ሰው ከሰው፣ ዕጅ ከእግር በሚጋጭበት ዓለም የንዴት ፈውስ በአማርኛ ተርጉሜ በነጻ ተቀበሉኝ ስላችሁ ንዴት ራስ ካልሳማችሁ በስተቀር አሻፈረኝ የምትሉበት ምክንያት አልታየኝምና እነሆ።
ንዴት ምንድነው?
ዕቅድዎን ወይም ፍላጎትዎን ዕውን ለማድረግ ጎንበስ ቀና ሲሉ ለስኬቱ ደንቃራ የሚሆን ሳካ ሲያጋጥምዎ ተስፋ መቁረጥ፣ ብሎም የጥላቻ መንፈስ ስሜት ይፈጠርብዎታል፡ ይህ ስሜት በሌላ አጠራር ንዴት ይባላል።
ምሳሌ 1፡ ሉሲ ማዕድ ቤቱን ለማጽዳት ፈልጋለች፤ ባለቤቷ ግን ዕረፍት እንድታደርግ አስገደዳት። ሉሲ ባለቤቷ ልክ እንደህጻን ልጅ እንደቆጠራት ስለተሰማት በጣም ተናደደች።
ምሳሌ 2፡ ሱዚ ከሃኪሟ ቢሮ ተደውሎ ለዛሬ አስይዛ የነበረው ቀጠሮ ተሰርዞ ለነገ መተላለፉ ተነገራት፤ የዛሬውን ቀጠሮ በጣም ጠብቃው የነበረ በመሆኑ ሳታስበው መቀዬሩ አናደዳት።
ምሳሌ 3፡ ጆርጅ ሁለት የቅርብ ጓደኞቹ ቴኒስ ሲጫዎቱ ተመለከተ፤ በአካሉ ላይ የደረሰው ጉዳት እንደጓደኞቹ መጫዎት እንዳይችል ስላደረገው ተናደደ።
ምሳሌ 4፡ የዮሐንስ እናት ራሱን ቢጠብቅ ጤነኛ ልጅ ሊሆን እንደሚችል መከሩት። የእናቱ ትችት በጣም አናደደው።
ንዴት በሶስት ይከፈላል
ጋሪያት፡ ጋሪያት እጅግ አደገኛ የሆነና ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የንዴት መገለጫ ነው። ጋሪያት የከረረ ንዴት ሆኖ በድንገት የሚከሰትና ጉዳት የሚያስከትል ሊሆን ይችላል። በምሳሌ 1 የተጠቀሰችው ሉሲ በባሏ ንግግር ተበሳጭታ በዕጇ የያዘችውን ሸክላ ሳህኖች ግድግዳ ላይ በማላተም ብትሰባብራቸው እንድህ ዓይነቱ ያልተለመደ ዕርምጃ ቁጣ ይባላል””
ቁጣ/ኩርፊያ፡ ቁጣ/ኩርፊያ በሰው ወይም በጠላነው ቁሳካል ላይ የተሰማንን ቅሬታ አምቀን በመያዛችን የሚሰማን ስሜት ነው። ኩርፊያ በውስጣችን በመቀጣጠል ሠላም ከመንሳቱ ባሻገር የአካልና የስነልቦና ጉዳት ያስከትላል።በምሳሌ 4 የተጠቀሰው ዮሃንስ በእናቱ ለተሰነዘረው አስተያዬት አኩርፎ አቋሙን ከማስረዳትና ከመግለጽ ከተቆጠበ የቁጣ/ኩርፊያ ስሜት ያድርበታል።
ቅሬታ፡ ቅሬታ አግባብ ያለው ሆኖ ራስን ተቅጣጥሮ የሚገለጽ ገንቢ የንዴት ዓይነት ነው። በምሳሌ 2 የተጠቀሰችው ሱዚ ቀጠሮዋ መሠረዙ ተደውሎ ሲነገራት ማልቀስ ቢቃጣትም ቀጠሮው መተላለፉ ቅሬታ ያሳደረባት መሆኑን በተረጋጋ መንፈስ ለጸሃፊዋ ጠቁማ ሌላ ቀጠሮ በመያዙ እንደምትስማማን ገለጸች።፡
ከላይ የተገለጹት የንዴት ዓይነቶች (ቁጣ፣ ኩርፊያ፣ ቅሬታ) እንደሁኔታው በተናጠል ወይም በአንድነት ሊከሰቱ ይችላሉ። እነዚህን የንዴት ዓይነቶች ጠንቅቆ በመረዳት እንድፈጠሩ ምክንያት የሆኑ ክስተቶችን በቀላሉ ለመቆጣጠር ይቻላል።
ንዴትና አስተሳሰብ
ንዴት የሚኖረው በህሊናችን ውስጥ ስለሆነ የአስተሳሰባችን ነጸብራቅ ነው። ንዴትን የሚጭረው የሚያጋጥመን ክስተት ሳይሆን ስለዚያ ክስተት ያለን ግንዛቤና በራሳችን አመለካከት የምንሰጠው ትርጉም ነው። ንዴትን ለመቆጣጠርና በአግባቡ ለመያዝ ይቻል ዘንድ ጠቃሚ ዕርምጃዎችን መውሰድ ይቻላል።
- የንዴት ሰለባ መሆንዎን ይመኑ። ንዴት የያዘዎ መሆኑን ራስዎን ማሳመን ማርከሻውን ለማግኘት የመጀመሪያው ዕርምጃ ነው። አንዳንድ ሰዎች መናደዳቸውን ለማመን በጣም ይቸገራሉ ምክንያቱም መናደድ ተገቢ ያልሆነና የሚነቀፍ ጠባይ ነው ብለው ስለሚገምቱ ነው። እንድህ ዓይነት ሰዎች ስሜታቸውን በመካዳቸው የተነሳ መፍትሄም ለማፈላለግ ዝግጁ አይደሉም።
- የንዴትዎ መንሥኤዎች ምን እንደሆኑ ለይተው ይወቁ። የንዴትዎ መንሥኤ ምን እንደሆነ ለይቶ ማወቅ ለችግርዎ መፍትሄ ለመሻት ፈር ቀዳጅ ነው። አንዳንድ ጊዜ ዋናው ምክንያት አነስተኛ ከሆኑ የግል ስሜቶቻችን ጋር ይሳከራል። በምሳሌ 1 ላይ የተጠቀሰችው ሉሲ የንዴትዋ መንሥኤ የባለቤቷ ንግግር ነው ወይስ የዕለት ከዕለት ተግባሯን በትክክል እንዳታከናውን የደረሰባት የጤና ዕክል ዕንቅፋት ስለሆነባት? ሉሲ የንዴቷን መንሥኤ ያለአግባብ ከጤናዋ መታዎክ ወደባለቤቷ ንግግር ከቀየረችው ችግሩ ይባባሳል።
- በንዴት እየጨሱ ነው? ለምን? ለንዴትዎ መንሥኤ የሆኑ ምክንያቶችን ለይቶ መረዳት ንዴትን ለመቆጣጠር የሚያስችልዎ የመጀመሪያው ዕርምጃ ነው። ንዴት የጫሩብዎትን ምክንያቶች በዝርዝር ከተመለከቱ በኋላ ንዴትዎ አመክንዮ የሚሰጠው ወይም ተገቢ መሆኑን በህሊናዎ በመመዘን ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ። ንዴትዎ የማይገባና መሠረት የሌለው ሆኖ ካገኙት የዚያ ዓይነት ስሜት ከውስጥዎ እንደ ጢስ ብን ብሎ እንድጠፋ ዕርምጃ ይወስዳሉ። በአንጻሩ ንዴትዎ አግባብ ያለው ሆኖ ከተገኘ ደግሞ እንዴት ሊቋቋሙት እንደሚችሉ መፍትሄ ያሰላስላሉ።
ንዴትን መቆጣጠር
ኣስተሳሰብዎን ብሎም ንዴትዎን ለመቆጣጠር የሚያስችሎት የተፈተሹ ዘዴዎች አሉ።
ድርጊትን በአዕምሮዎ ሰሌዳ መሳል፦ የከረረና በንዴት የተወጠረ ስሜትዎን በአይነ ህሊናዎ በሚቀርጹት ሥዕል እንድተን ማድረግ ይችላሉ። ለምሳሌ የንዴትዎ መንሥኤ የሆነውን ሰው በሃሳብዎ እንደ ሳዳም ሁሴን ይስቀሉት። እንድህ ዓይነቱን ዘዴ በመጠቀም ስብዕናዎን ከሚያውከው የንዴትን ጠኔ ቀስ በቀስ መገላገል ይቻላሉ።
ንዴት የሚያቁት አስተሳሰብን ማስወገድ፦ ንዴትን የሚጭሩና የሚያጎለምሱ አስተሳሰቦች በህሊናዎ ውለው እንዲያድሩ ዕድል መስጠት የለብዎትም። ሃሳብዎን ወደሚያስደስትዎና ወደሚዎዱት ክስተት በማዘንበል እነዚህን ጎጅ የአስተሳሰብ ሂደቶች ፊት ይንሷቸው።
ያሰቡትን ለማግኘት ከመጠን ያለፈ ጉጉት አለማሳደር፦ የሰው ልጆች(እኔን ጨምሮ) የጠብቁትን ሲያጡ ለንዴት ጦስ ይዳረጋሉ። እንድፈጸምልዎ የሚፈልጉትን ነገር እንደሁኔታው የሚለዋውጡ ወይም የሚያስተካክሉ ከሆነ ከጅምሩ የንዴት መቋሪያ አይሆኑም። ለዚያ ካልታደሉ ደግሞ ንዴትዎን መቆጣጠር ይችላሉ።
ተግባብቶ ለመኖር መጣር፦ አንድ ሰው ለምን የዚያ ዓይነት ጠባይ እንዳሳየና ለምን በዚያ መልኩ እንደተናገረ ለመገንዘብ መቻል መግባባት ላይ ለመድረስ ይረዳል። ራስዎን በሰውዬው ቦታ በማስቀመጥ ሁነቶችን ከሱ አንጻር መገምገም ብልሃት ነው።
ንዴት ጉዳት የሚያስከትል መሆን የለበትም
- በተናደዱ ጊዜ ቀጥሎ የተዘረዘሩት ፊዚዮሎጅካዊ ለውጦች በውስጥዎ ይከሰታሉ፡
-
- የደም ግፊት መጨመር
- የአተነፋፈስና የልብ ምት መጨመር
- የጡንቻዎች መወጠር
- ንዴት ብዙ ጊዜ እንድቆይ ከተፈቀደለት በራስና በሌሎች ላይ ጉዳት ያደርሳል። ንዴት ኤነርጅ ነው። ከሰውነታችን ውስጥ ቀስ ብሎ እንድወጣ የሚያስችሉ እርምጃዎች በቅደም ተከተል መውሰድ ያስፈልጋል። ንዴት ጉዳት የሚያስከትል መሆን የለበትም። እንድያውም በብልሃት ከተያዘ ንዴት ችግሮቻችንን ለመፍታት የመግባቢያና የመደራደሪያ መሣሪያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል።
- ከላይ የተጠቀሱትን ምክሮች ተግባራዊ በማድረግ ንዴትን ምርኮኛዎ ያድርጉት። በርጥብ በደረቁ ደምዎ ተክ አይበል። ለጤንነትዎ፣ለትዳርዎ፣ ለቤተሰብዎና ለጓደኞችዎ መድን ይሆኑ ዘንድ ንዴትዎን ለመቆጣጠር የራስዎ ፖሊስ ይሁኑ።
ትርጉም፡ በወርቁ ለገሠ ሙላት ([email protected])
ምንጭ፡ Carol & Richard Eustice, About.com