ዳግማዊ የደም ምድር

ከበልጅግ አሊ

ተመስገን ክላሸኑን እንደያዘ ተወልዶ ወደ አደገበት ሠፈሩ ልደታ ያመጣውን ሹፌር አመስግኖ በእግሩ ጉዞውን ጀመረ ።የለበሰው የሠራዊቱ ልብስ መቆሸሹ በግልፅ ከማስታወቁም በላይ ካለ ልኩ የተሰፋ ይመስል ላዩ ላይ ይዋልላል።ሸሚዙ ከሱሪው ወጥቶ ተንዘላዝሏል።ልደታ ቤተክርስቲያን ጋ ሲደርስ ምስጋናውን ለማድረስ ዞር አለ። ልደታን ይወዳታል። ሲቸግረው የምትደርስለት፣ ሲከፋው የሚያማክራት ፣ የሚምልባት ልደትዬ ምስጋና ሲያንሳት ነው ። አካሌ ሳይጎል ፣ ጥይት ሳይነካኝ ፣ ጠብቃ፣ ከለላ ሆና ያመጣችኝ እሷ አይደለች? ብሎ ወደ ግቢው አመራ ።ከነመሣሪያው ወደ ቤተክርስትያን ቅፅር ውስጥ መግባት ስላልፈለገ ከበራፍ ቆሞ ካማተበና በማጉተምተም ፀሎቱን ካደረሰ በኋላ ተሳልሞ ወደ ቤቱ ጉዞውን ቀጠለ። ።

ብሪሞ ያደገበት ሠፈሩ ነው ። ብዙ አሳዛኝና አስደሳች የልጅነት ትዝታዎች ስለተፈራረቁበት እንባው ዓይኑ ላይ አቀረረ ። ወፍጮ ቤቱ፣ ልብስ ሰፊዎቹን፣ ግርማ ፎቶ ቤት… እየተመለከተ ቁልቁል ወደ እናቱ ቤት ተጓዘ ። እናቱ ጉልት ሲሸጡ የነበራቸውን የድሮ መደብ ተመለከተ። የማውቀው ሰው ካገኘሁ እያለ እየተገላመጠ ቁልቁል ወደ ወንዙ በሚወስደው መንገድ ወረደ ። እናቱን አየር ወለድነት ከተቀጠረ በኋላ ተቆራጭ ገንዘብ አድርጎ ጉልት መሸጡን አስቁሟቸው ስለነበር፣ እዚህ እንደማይገኙ ስለሚያውቀው ዓይናቸውን እቤት ደርሶ ለማየት ተጣደፈ።እስከ አሁንስ በእኔ ደሞዝ ኖረናል ከአሁን በኋላ ምን ልንሆን ነው ? ጦሩ ተበትኗል። ደሞዝ የመቀበላችን ነገር አይታወቅም።ተመልሳ ጉልት ልትቀመጥ ? ብሎ ተከዘ። እንኳን እዚህ ደረስኩ እንጂ አይሆንም ! ይህንን በዓይኔ ቆሜ አላይም ! ኩሊነትም ቢሆን ሠርቼ ትኖራለች እንጂ እንደገና ጉልት አትቀመጥም ብሎ ለራሱ ቃል ገባ ። ይሁን ለአሁኑ ይበል እንጂ ውስጡ ግን የነገ ኑሮው ከባድ እንደሚሆን ልቡ እየነገረው ነበር። ሁኔታው በጣም አስፈራው ። ሰሞኑን ያየውን ሕልም አስታወሰ።

ከስቴዲዮም መጥቶ ታጠቅ የገበያ አዳራሽ ጋ የቆመ ይመስለዋል። ባለ ታክሲ መጥቶ ዮሴፍ በራሪ የሞላ አንድ ሰው የጎደለው ግባ ይለዋል። አልገባም ብሎ ይላል። አለፍ ብሎ ደግሞ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በራፍ ላይ ሲደርስ ደግሞ እንደገና ያው ታክሲ ይመጣና የሞላ ዮሴፍ አንድ ሰው የጎደለው ይለዋል። አሁንም እንቢ ይላል። ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ጋ ሲደርስ እንደገና ያው ታክሲው መጥቶ የሞላ ዮሴፍ አንድ ሰው የጎደለው ትገባለህ ብሎ ይጠይቀዋል። አሁንም እንቢ ይላል። ስለዚህ ሕልም ትርጉም እናቱን ለመጠየቅ ቸኮለ። የህልሙን ትርጉም ከሰሞኑ ግርግር ሊያያይዘው ሞክሮ ነበር። ግን ለምን ዮሴፍ ? ምን ይሆን ? ።ስለ ህልሙ ማሰቡ እንደገና ፍርሃት ቀሰቀሰበት።

ሕልሙን ትቶ ስለ ወቅቱ ሁኔታ ማሰብ ጀመረ ።መንግሥቱ ሃገር ጥሎ ይጠፋል ብሎ አስቦትም፣ አልሞትም አያውቅም። መጥፋቱ ከተሰማ በኋላ በጦሩ የተፈጠረውን ግራ መጋባት ከዚያም ተስፋ መቁረጥ ደግሞ አይቶታል። እሱና ጓደኞቹ ጦሩን ለማረጋጋት ሞክረው ነበር ግን ማን ሰምቶ ?የደርግ ካድሬዎችና ባለሥልጣናትማ መጀመሪያ ጥለው የጠፉት። ጦሩ ሲበታተን እሱም ተበትኖ ከአንቦ አካባቢ ወደ አዲስ አበባ መጣ።

ገና ቤት ሲገባ እናቱ በጭንቀት እንዳልሰነበቱ፣ በልቅሶ ድምፃቸው እንዳልተዘጋ ፣በዕልልታ አካባቢውን በጠበጡት። ይህንን የሰሙ ጎረቤቶች ተሰበሰቡ ። እንኳን ደስ አሎት የሚለው በዛ ። ጭውውቱ ቀጠለ፡

አንዷ ጎረቤት “ልደታ ድህነታቸውን አይታ ፣ ጉልት ሸጠው እንዳሳደጉት ተመልክታ ፣እምነታቸውን በማሰብ ነው እንጂ እንዲህ በሰላም ያመጣችላቸው ማን ይህንን ዕድል አገኘ”።

ሌላኛይቱ ደግሞ “የስንቱ ልጅ እንደወጣ ቀረ አይደለም፣ መላ ቶሎሳ ሰፈር ጥቁር ለብሷል እኮ” እያሉ ጎረቤቶቻቸው የሳቸውን ዕድል ያዳንቁ ጀመረ ። ጠላ ተገዝቶ መጥቶ ለሁሉም ግብዣ ተደረገ። የተመስገን መመለስ ወረ ጋር ጎን ለጎን ተወርቶ ስለ ወያኔ መግባት ይወራ ጀመር ።ስለጦርነቱ ፣ ስለ ሠራዊቱ ፣ ስለ ሁኔታው ጎረቤቶቹ በጥያቄ አጣደፉት። ጎረቤቶቹ እስኪሄዱ ሲቁነጠነጥ የነበረው ሕልሙን ለእናቱ ነገራቸው።መጀመሪያ ህልም በጨለማ አይፈታም አሉና ቀጠል አድርገው “ምንም አደል ጥሩ ሕልም ነው ግን ሰሞኑን ጠንቀቅ በል ብቻ ” አሉት ። ግን ፊታቸው ላይ ያለው ትካዜ “ጥሩ ነው” ከሚለው እናታዊ ማፅናናት ጋር አልተጣጣመላቸውም። ተመስገን እናቱን ላለማስጨነቅ በትርጉሙ ምንም ሳይገፋ እሺ ብሎ ዝም አለ።

ሠፈሩ በተመለሰበት ሰሞን ግርግር ስለነበር ተመስገን ራቅ ብሎ መሄድ አልፈለገም። በራፉ ላይ ተቀምጦ በሃሳብ ይናውዛል። አንዳንድ ጊዜ በብስጭት ሌላ ጊዜ በትካዜ ለረጅም ጊዜ ተውጦ ይቀመጣል።እንዴት ወታደርነት መቀጠር እንደፈለገ ማሰብ ጀመረ።

የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ውጤት እንዳልተሳካለት እንዳወቀ ነበር ተመስገን ለልደታ ልጆች ሁል ጊዜ ክፍት የነበረውን ወታደርነት ለመቀጠር የወሰነው ። ለማንም ሳይናገር ሰሞኑን ወታደሮች የሚቀጠሩበት ጃንሜዳ መሄድ እንዳለበት አሰበ ። በአጠገቡ የቀበሌ ተማራጮች ሲያልፉ ሰላም ብሏቸው ሊሄድ ሲል

“እንዴት ነበር ማትሪክ ?” ብሎ አንዱ ጠየቀው።

“ለዲፕሎም አልፌለሁ”። ብሎ ዋሸ።

“እንኳን ደስ ያለህ ኧረ! የድጋፍ ወረቀት እንድንጽፍልህ የውጤት ወረቀቱን ይዘህ ና” ብለውት የውሽት ፈገግታቸውን አሳይተውት አለፉ።

ምን እንደፈለጉ ስለገባው በልቡ “ሞኛችሁን ፈልጉ፣ እንዲዚህ እንደቋመጣችሁ ባላስቀራችሁ፣ እኔን ብሔራዊ ውትድርና ለመላክ መወሰናችሁን ያልሰማሁ እንዳይመስላችሁ። ግን አታገኙኝም ።ብሔራዊ ውትድርና ከምሄድ እናቴ እንኳ ጡረቴዬን ብታገኝ ውትድርና ብቀጠር ይሻለኛል” ብሎ ለብቻው እያጉተመተመ. . . ወደ ጃንሜዳ ጉዞውን ቀጠለ ።ጃንሜዳ ሌሎች የሚቀጠሩ ወጣቶችን አግኝቶ ተደባለቀ።

አንዱ “ዛሬ አየር ወለድ ነው የሚቀጠረው ይላል”

ሌላኛው ደግሞ “ታንከኛ ነው ሲባል ሰምቻለሁ”

የተለያየ ወሬ ጃንሜዳን ሞልቶታል ።ተመስገን ግን ለወሬው ግድ አልነበረውም ። እናቱ ጉልት ሸጠው የሚያገኙትን ገንዘብ መካፈል አይፈልግም ። የሚተማመንበት ዘመድ ወገን ስለ ሌለው ሌላ ሥራም እንደማያገኝ አውቆታል ። መድፈኛም ይሆን ታንከኛ ፣ አየርወለድም ይሁን እግረኛ መቀጠሩ ነው ዋናው ነገር ።

“ለመቀጠር የምትፈልጉ ከወገባችሁ በላይ ልብሳችሁን አውልቁና በዚህ በኩል ተሰለፉ ” የሚል ማስታወቂያ በድምፅ ማጉያው ተነገረ ፡፡ ተመስገን ልብሱን አውልቆ እብብቱ ሥር ሸጉጦ ከሠልፉ ተደባለቀ ። ቀጠን ብሎ ዘለግ ያለው ተመስገን ከሌሎቹ ረዘም ብሎ ይታይ ነበር ። ውስጥ እግራቸውን ፣ጥርሳቸውን ፣ ቁመናቸውን አንድ በአንድ እየተመለከቱ በሁለት ወገን አስቆሟቸው ። አንዱን ቡድን እዚያው እንዲቆይ ተደርጎ እነ ተመስገንን የተመደቡበት ሠልፍ ወደ ሌላ ቦታ ተወሰዱ ። ለአየር ወለድነት እንደተመረጡ ተነግሯቸው እዚያው የቅጥር ፎርም ሞልተው የተሟላ የጤና ምርመራ የሚያደርጉበትና የሚሰለጥኑበት ቦታ ተነግሯቸው ተበታተኑ ። ተመስገንም በኩራትና በደስታ ልቡ ተሞልቶ ወደ ቢሪሞ ተመለሰ።

ይህንን ሲያወጣና ሲያወርድ፣ አንዴ ፈገግ ፣ አንዴ ኮስተር ሲል የተመለከቱት እናቱ በንዴት በሽታ ላይ እንዳይወድቅባቸው በመስጋት፡

“ልጄ እዚህ ከምትተክዝ ወጣ ብለህ ከድሮ ጓደኞችህ ጋር እዚሁ አካባቢ አትጫወትም? ” ሲሉት ተመስገን እሺ ብሎ በፈገግታ ከሸኛቸው በኋላ እንደ ገና በሃሳብ ነጎደ።

የዚያን ጊዜ የተሰማውን ኩራት የተሞላበት ደስታ አሁን ካለበት ሁኔታ ጋር ሲያነፃፀር እፍረት ተሰማውና ራሱን እየደባበሰ የወደፊቱን ማሰላሰል ጀመረ ።ተመስገን ከጦር ሜዳ ሲመለስ ምንም ይዞ የመጣው ጥሪት የለውም። መንግሥቱ በጠፋበት ወቅት ፣ ምንም እንኳ በጦርነቱ እየተሸነፉ መምጣታቸውን ቢረዳም ፣ከአሁን አሁን ተጠናክረን መልሰን ወደ መጡበት እንልካቸዋለን በማለት ተስፋ ሳይቆርጥ ከጥቂት ጓደኞቹ ጋር በመሆን ተዋግቶ ነበር ። የመንግሥቱ መጥፋት ጦሩን ካለ መሪ ሲያስቀረው ፣የፖለቲካና የጦር መሪዎቹም ለመፈርጠጥ የመጀመሪያ ሲሆኑ፣ የቀሩትም እንደዚሁ ሲበታተኑ፣ እሱም –

በእጁ ያለችውን አንድ ክላሸን ፣ ራሱን ከዘራፊ ለመከላከል ይዞ ወደ ተወለደበት ሠፈር ተመለሰ።በዛ ሁሉ መሣሪያና ሠራዊት ያልተሸነፈ ወያኔን በአንድ ክላሽንና የተወሰነ ጥይት ምን ሊያደርግ ይችላል?

ትካዜው ወደ መፍትሄ ያጣ ጭንቀት ሲያደላበት እናቱ እንዳሉት እስቲ ለማንኛውም ብሎ ወጣ ። በከተማው ውስጥ ግርግሩ በዝቷል ። ሰው ያለ የሌለውን በመግዛት ይሰበስባል ። መጥፎ ጊዜ ሊመጣ እንደሆነ አካባቢው ያሳብቃል ። የተወሰኑትን የቀደሞ ጓደኞቹ ሱቁ ጋ ተሰብስበው አገኛቸው ። ሰላም ከተባባሉ ወዲያ ጨዋታቸውን ቀጠሉ።

“ወያኔ ሆለታን ተቆጣጥሮታል፣ አዲስ አበባም በእነርሱ የተኩስ ኢላማ ሥር ገብታለች ይላል አንዱ ።

“ሌላው ደብረዘይትም ገብተዋል” ይላል ።

“የመንግሥቱ ቅልቦች ቤተመንግሥቱን አለቅም ብለዋል” ይላል ደግሞ ሌላው ።

“ቶሎሳ ሰፈር መሣሪያ እየተቸበቸበ ነው” አለ አንዱ ።

“ወስላቶች መርካቶን መዝረፍ ጀምረዋል” አለ ሌላው።

“ወያኔዎቹ የአዲስ አበባን ውሃንና መብራት እንቆርጣለን ብለዋል” አለ ሌላኛው ደግሞ።

ተመስገን ሁሉንም ሲሰማ ቆይቶ መሣሪያ ይሸጣል የሚለውን ብቻ ማሰላሰል ያዘ ። ይዞት የመጣውን ክላሸንኮቭ ሸጦ ትንሽ እንኳ ቀለብ ለቤት ቢገዛ የሚሻለው መሆኑን አሰበ ። እናቱም ገንዘብ ይዞ የመጣ ስለመሰላቸው ከእሱ ነው የሚጠብቁት ። የቀድሞ ጓደኞቹን ተሰናብቶ ሊሄድ ሲል አንዱ ከመካከላቸው ነጠል ብሎ ተከተለውና፡

“ክላሸንኗን ምን አደረግሺያት ?” ብሎ ጠይቀው ።

“ምነው ፈለግሻት እንዴ?”አለው ተመስገን ።

“እናሻግራት እንጂ ?ታቅፈሻትም ምን ትሰራልሻለች? ”

“ለራስ መጠበቂያ ነዋ ” አለ ተመስገን ፡፤

“ምን አለሽና ምንሽን ነው የምትጠብቂው ፡፤ወይስ መንጌ ከመበጠሱ በፊት ትንሽ ገፍቶልሻል ።

“የሚገዛ የት ይገኛል?” አለ ተመስገን ።

“እሱን ለእኔ ተይው ማታ ብቻ ቤት ጠብቂኝ” ።አለው ።

“እሺ ተባብለው ተለያዩ ።

ያ ጓደኛው እውነትም እንዳለው ቃሉን ጠብቆ ማታ መጥቶ ገንዘቡን ሰጥቶ መሣሪያውንና ጥይቶቹን ይዞ ሄደ ። ተመስገንም በአንድ በኩል ትንሽ ገንዘብ ስላገኘ ደስ ሲለው በሌላ በኩል ደግሞ ከስንት ጊዜ በኋላ በዚህ ምንም ባለየበት ጊዜ ባዶ እጁን መሆኑ ቅር አለው።

“ወሬው ሃሜቱ ከንቱ ሆኖ አልቀረም። እንደተፈራው ግንቦት 20 አዲስ አበባን በቁጥጥር ሥር አደረገ ። ሠርጎ ገብቶ የነበረው የወያኔ ጦር የከተማውን ቁልፍ ቦታዎች ተቆጣጠረ።የልደታ አስተዳደር አንድ ቡና ቤት ለነበረው የትግራይ ተወላጅ ተሰጠ ።በዚህ ሰው ወያኔ ሆኖ መገኘት ሕዝብ ጉድ አለ።

– “የዛ ቡናቤት ባለቤት ወያኔ ሆነ እኮ! “ይላል አንዱ ።
– ሌላው ” ድሮስ ምን ሊሆን ነበር ?” ባለመደነቅና እኔ አውቅ ነበር በሚል ዓይነት ስሜት፡፤
– “ከባሬስታነት ይህንን የሚያክል ቡና ቤት ሲከፍት ዝም ሲሉት ነው እኮ ሃገራችንን የገደሉት ” ይላል ሌላኛው።
– “ደህንነቶች ከእሱ ቤት አይወጡም ነበር እኮ ”
– “እያበላ እያጠጣ ነው እኮ አፋቸውን የለጎማችው ። እነዚህ ሆዳሞች! ”
– “ይኸው አሁን በየቦታው ውሃ የገባች ድመት ሊመስሉ እሱ ቡና ቤት ውስጥ ምንም ሳናደርጋቸው ሽጉጥ እየመዘዙ ሲያስፈራሩን አልነበር እንዴ ? ይበላቸው! ሲያንሳቸው ነው ። እኔ የማዝነው ለጦሩ ነው እንጂ ኢሠፓውንና ደህነቱንማ ይበላቸው”
– “ገና ነው ወያኔ ሁላችንንም ነው በጠላትነት የፈረጀው ። በእነሱ ተጀመረ እንጂ እኛንም አይለቀን ” ይላል ሌላው ፍርሃት በሞላበት ድምፅ ።

የቡና ቤቱ ባለቤት ሠፈሩን በደንብ ያጠናውና መረጃ ያጠናከረበት በመሆኑ ብዙም ጊዜ ሳያጠፋ ከወያኔዎቹ ጋር በመሆን በአካባቢው የተበተነውን የጦር መሳሪያ ማሰባሰብ ጀመረ ። ተመስገን የቀድሞው የሠራዊቱ አባል ስለነበረ ከዚህ ሰው ጥቆማ ሊያመልጥ አልቻለም ። ትልቁ ስህተቱ መሣሪያውን በአደባባይ አንጠልጥሎ መምጣቱ ነበር ። ሠርገው የገቡ የወያኔ ቅጥረኞች በጠራራ ፀሐይ ከነመሣሪያው –

መምጣቱን ተመልክተውታል ። ወያኔዎቹ እንደሚፈልጉት ሲሰማ አክስቱ ወደ አሉበት አየር ጤና አካባቢ ሄዶ ተደበቀ።

ወያኔዎቹ እናቱን አስረው አሰቃይተው ወዴት እንደሄደ ደርሰውበት ነበርና የአክስቱ ቤት ድረስ በወታደር ጅፕ ሆነው መጡ። መጀመሪያ የጠየቁት ስለ መሣሪያው ነበር።

“አንታ ክላሸኑን የት አደረግከው?”

ብሎ አንዱ መሪያቸው የሚመስለውና ቀደም ቀደም የሚለው ወያኔ ጠየቀው።

ተመስገን “እነዚህ ናቸው ያሸነፉን?” በሚል በጥላቻ ዓይን እየተመለከተው “የቱ ክላሸን?” ብሎ መልሶ ወያኔውን ጠየቀው።

“አንታ ሰምተናል እኮ! ዋይ! አንጠልጥለህ የመጣኸው ነዋ!”

አለው ፀጉሩን ያጎፈረው አማርኛ የሚናገረው ወያኔ።

“ማነው የነገረህ?” አለ ተመስገን ምንም ዓይነት ፍርሃት ሳይታይበት።

ወያኔው ለተመስገን ሳይመልስለት ስልክ ደወለና “ታከለን አቅርቡልኝ” ብሎ ጠየቀ።

ታከለ ሲቀርብለት “እቺ አማህራይ ክዳለች። ምን እናድርጋት?” ብሎ ጠየቀ።

ታከለ “እናቱ ቤት ጋ ይዛችሁት ምጡ እዛ እጠብቃችኋለሁ። እናቱ እንድታስረዳው እናደርጋለን።” ብሎ ታስረው የቀረቡትን የተመስገንን እናት እየተመለከተ አዘዘው።

ተመስገንን ያን ሁሉ ጀብዱ በሠራዊቱ ውስጥ እንዳልሠራ፣ እንደ ተራ ሌባ ተይዞ ወደ ሠፈሩ መሄዱን ባይፈልገውም የአክስቱን ቤት ላለመረበሽ እንሂድ ሲሉት ምንም ሳያንገራግር ወጥቶ በእነሱ መኪና ማሃከላቸው አጣብቀው አስቀምጠውት ጉዞ ጀመሩ። በመንገድ ላይ በሃሳብ ተዋጠ። አባቱ ትዝ አሉት።

በጡረታ የተገለሉ አባት ጡረተኞች “አባት ጦር” ተብለው ወደ ግንባር ይሂዱ ተብሎ በደርግ የክተት ጥሪ ሲወጣ ነበር እንደ ገና ከጦሩ የተቀላቀሉት። ከዛም ወደ ሰሜን ዘምተው ነበር። አንድ ቀን እናቱ ደሞዝ ሊቀበሉ በሄዱ ጊዜ ደሞዙ መቋረጡ ተነገራቸው። ተቆራጭ ገንዘቡ ሲያቆም ሞቷል ወይም ጠፍቷል ማለት ስለሆነ እናቱ እርማቸውን አወጡ። ተመስገን ግን ተስፋ አልቆረጠም ነበር። ሰሞኑን ብዙ የሠራዊቱ አባላት አዲስ አበባን ሲያጥለቀልቋት፣ አባቴ ይመለስ ይሆናል ብሎ ዓይኑ የተንከራከተው አሰበ። እንደገና አባቱን ትቶ ወንድሙን አሰበ።

በእድሜ ልጅ በመሆኑ ወንድሙን ብዙም ባያስታውስም እናቱ ሁልጊዜ የቢሪሞን ገደል እያሳዩ፡

“እዚህ ጋ ነው ወንድምህን ገድለው የጣሉት። ሲያቃዠኝ አድሮ በጠዋት ተነስቼ እስቲ ልደታን ተሳልሜ ልምጣ ብዬ ሽቅብ ስሄድ ብሪሞ ጋ ሬሳ ተጥሏል ሲሉ ሰማሁ። መቼም ያን ጊዜ ልጅ የታሰራበት እናት ሁሉ በጠዋት ተነስታ ሬሳ በተጣለበት እየዞረች ማሰስ ነበር። እነማን ይሁኑ ብዬ ጠጋ ብል አልታይ አለኝ። ለካ አብዮት ጠባቂዎቹ አውቀው ኖሮ ልጠይቃቸው ስጠጋ ሸተት፣ ሸተት አሉኝ። ምን ሆነው ነው በማለት ጠጋ ብዬ ብመለከት ጉዴን ተዘርሮ፣ በደም አበላ ተሸፍኖ አየሁት። ጉልበቴ ከዳኝ። ሰማይ ምድሩ ተደባለቀብኝ። በእንፉቅቅ ሄጄ አጠገቡ ቁጭ ብዬ አንገቱን ቀና አድርጌ እጭኔ ላይ አድርጌ የቀዘቀዘ ሰውነቱን ሳም፣ ሳም አደረግሁት። ቀበሌዎች ለፀረ-አብዮተኛ ይህ ሁሉ አይገባም ብለው እኔን መንጭቀው አንስተው አስከሬኑን በእግራቸው እረገጡት። አይ ያ ዓይን፣ አይ ያ ቁመና እንዲህ የሽንት መሽኛ ገደል ውስጥ ይውደቅ? የዚህ ሁሉ ግፍ መጨረሻው ምን ይሆን ይሆን?”

እያሉ ክስት ያለ ደረታቸውን እየደቁ የሚነግሩትን አስታወሰ።

ይህ ሲሰማውና ሲያየው ያደገው ታሪክ ነው። የአባቱ መውደቂያ ታሰበው። ትግራይ ይሆን? ኤርትራ? ያወጣና ያወርድ ጀመር። የአባቴ መውደቂያም ማንም አያውቀውም። ለደሃ ቢታወቅስ ምን ጥቅም አለው?

እንደገና ስለ ራሱ አሰበ። ሁላችንም ለዚህ ሃገር በተለያየ ሁኔታ እየሞትንላት ነው። እኔ እንደነሱ ጀግና አይደለሁም። እንደ አንድ ሌባ ተይዤ ወደ ተወለድኩበት እየተወሰድኩ ነኝ። የሚሉትን መሣሪያ ልሠጣቸው ስለማልችል ምን እንደሚደርስብኝ አላውቅም። የሸጥኩለትን ልጅስ የት አገኘዋለሁ? እሱም ይክድ ይሆናል?

ይህንን ሲያወጣ ሲያወርድ እናቱ ጉልት ይሸጡበት የነበረው ቦታ ሲደርስ በልጅነቱ የደረሰበት ችግር ሁሉ ታሰበው። እናቱ እሱን ለማስተማር ለማሳደግ፣ ለቁም ነገር ለማድረስ ምን ያህል እንደ ደከሙ ታወሰው።

“አሁን እናቴ ተይዤ ስመጣ ስትመለከት ምን ትሆን ይሆን?”

ሕይወት ለተመስገን ትርጉም አጣች። ወንድሙ የተገደለበትን ቦታ ሲያልፋት እንዲህ ሆኖ ከመኖር መሞትን መረጠ።

“ምነው ልደታ የወንድሜንና የአባቴን ቀን ብትሰጪኝ? ምነው እንዲህ ባታዋርጂኝ? ምነው እንደነሱ እየፎከርኩ በሞትኩ?”

አይኖቹ በእንባ ተሞሉ።

ተመስገን በሃሳብ ተውጦ አይስማው እንጂ አጠገቡ የነበረው ወያኔ በተደጋጋሚ “ሃድጊ አማሃራይ፣ ደርግ ኢሠፓ…” እያለ ይሰድበው ነበር።

ተመስገን ስለ ዘሩ ለማሰብ ሞከረ። የሚያውቀው አባቱ አማርኛ በኮልታፋ አንደበት የሚናገሩ መሆናቸውን እንጂ እሱ አማራ ይሁን አይሁን አስቦትም፣ አልሞትም አያውቅም። የልደታ ልጅነቱን ነው የሚያውቀው። ወታደርነት ከመቀጠሩ በፊት ከአዲስ አባባ ሌላ የሚያውቀው ክፍለ ሃገር እንኳን አልነበረም።

የተመስገንን እናት አግቶ ወዲያና ወዲህ ሲንቆራጠጥ የነበረው ታከለ የሠፈሩ ሰው ተመስገን መያዙን ስለሰማ ለመመልከት ሲሰበሰብ ሲያይ ተጨማሪ ኃይል ጠየቀ። እነ ተመስገን ከመኪና ወርደው ወደ ግቢው ሲያመሩ አንዱ ወያኔ በሰደፍ ተመስገንን ጎሽም እያደረገ “ቶሎ በል! ወዲ ሸርሙጣ” አለው።

ተመስገን ወደ ሕዝቡ ሲመለከት እናቱ በተሸማቀቀ ሁኔታ መሣሪያ በታጠቁ ወያኔዎች ተይዘው ቆመው ተመለከተ። ልጄ እያሉ በደከመ ድምፅ ሲያለቅሱ ተሰማው።

ለመጨረሻ ጊዜ ተመስገን እናቱን እንዴት እንዳሳደጉትና በእሱ ምክንያት “ሸርሙጣ” እንደተባሉ ሲያስበው ሊታገስ አልቻለም። ሁሉም ነገር ትዝ አለው። የአባቱ መሞት፣ የወንድሙ መገደል፣ የእናቱ መሠቃየት፣ የሃገሩ አንድነት መፍረስ፣ አጠገቡ የሞቱት ጓደኞቹ ተስፋ የሌለው ኑሮ፣ …ሁሉም ጭንቅላቱን አዞረው። ዓይኑ ደም ለበሰ… ሰውነቱ ተንቀጠቀጠ። አጠገቡ የነበረውን ወያኔ እንዴት እንደመታው ሳይታወቅ መሬት ላይ ጥሎ በቅልጥፋና መሣሪውን ከእጁ ነጥቆ “አንተው ነህ ወዲ ሸርሙጣ” ብሎ አዳፈነበት ።

ከመቅስፈት ትርምስና ጩኸት ሆነ። ተመስገን የገደለው ወያኔ አጠገብ በርከክ ብሎ በአካባቢው የከበበውንና የተደናገጠውን ሕዝብ ላይ ተኩሶ ንፁሕ ደም እንዳያፈስ ሲያነጣጥር ከኋላው በበርካታ ጥይቶች ተመታ። በእጁ አነጣጥሮ ይዞት የነበረውን መሣሪያ ወርውሮ ተዝለፍልፎ በደረቱ ድፍት አለ።

በጥይት የተበሳሳው ሰውነቱ የደም ምንጭ ማፍለቅ ጀመረ። ደሙ እየተንኳለለ ሞቱን ለማብሰር የሚጣደፍ መልዕክተኛ ይመስል የቢሪሞን ምድር ያደርስ ጀመር። ተመስገን ተወልዶ ባደገበት ምድር በጥይት ተደብድቦ ተገደለ። መጀመሪያ በቀይ ሽብር፣ ዳግም በወያኔ ታጣቂዎች ልደታ (ብሪሞ) የደም ምድር ሆነ ።

ስለ ተመስገን የሚያስብ ሁሉ በሰላም ይክረም !

ቡሄ በሎንዶን ፳፻፪

(ጸሀፊውን በዚህ ኢሜይል አድራሽ ማግኘት ይቻላል፤ [email protected])