የጎንደሩ ሰልፍ የትናንቱ ሰልፍ ብዙ ነገር አስተምሮን አልፏል

የጎንደሩ ሰልፍ የትናንቱ ሰልፍ ብዙ ነገር አስተምሮን አልፏል። ምናልባትም ለዲሞክራሲ በሚደረገው ትግል የአዲስ ምዕራፍ መጀመሪያ ገጽ ሳይሆን አይቀርም የሚል ተስፋ አጭሮብኛል፡፡

46

1. ሰልፉ ከመካሄዱ በፊት “መፈቀድ የለበትም” የሚል አዝማሚያ ያላቸው አንዳንድ ሰዎች በፌስቡክ ብቅ ብለው ታይተዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች በዚህች አገራችን ላይ እንዲሰፍን የሚፈልጉት ምን አይነት ሥርዓት እንደሆነ ለመገመት ከብዶኛል፡፡ የተቃውሞ ሰልፍ ማለት እኮ ዲሞክራሲ ለታይታም ቢሆን አለ በሚባልባቸው አገሮች እንኳ ሳይቀር የዕለታዊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አካል ተደርጎ የሚታይ ተግባር ነው፡፡ “የእኔን አቋም የተቃወመ ሰው መሰለፍ የለበትም” ካልንማ ከደርግ በምን ተሻልን?

2. ካለሁበት ሆኜ እንደታዘብኩት ሰልፉ “ጥያቄያችንን በሰላማዊ መንገድ እስካቀረብን ድረስ አንድም የምንፈራበት ምክንያት ሊኖር አይችልም” ብለው የተነሱ አስተባባሪዎች የነበሩት ይመስላል፡፡ ሌላው ቢቀር መፈክሮችን ለመምረጥና እነሱን በጥሩ ሁኔታ አትሞ ለማዘጋጀት የሚያስፈልገው አቅም ይህን ይመሰክራል፡፡ ይህ የተለያዩ ጥያቄዎችን አንግበው ለመሰለፍ እያሰቡ ላሉ ወገኖች ጥሩ ምሳሌ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡

3. ሰልፉ በሰላም ተጀምሮ በሰላም ማለቁ ለመንግሥት ትልቅ ትምህርት ሰጥቷል፡፡ ሰልፍ የወጣን ሁሉ ‘መንግሥት ሊገለብጥ፣ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን ሊንድ..’ የተሰማራ አድርጎ ከማየት አባዜው ያላቅቀዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

4. ‘ህወሃትን የሚቃወሙ ኃይሎች ድርጅቱንና የትግራይን ሕዝብ ለይተው አያዩም’ ለሚለው ስሞታ ሰልፉ አጥጋቢ መልስ ሰጥቷል፡፡ የዚህ መልዕክት ግልባጭ ግን የህወሃት አባል ወይም ደጋፊ ላልሆኑ የትግራይ ልጆች የተላከ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ‘እኛ ይህን ብለናል፤ እናንተስ?’ ብሎ ኳሱን ወደነዚህ ወገኖቻችን የወረወረ ይመስለኛል፡፡ ምናልባትም መልሳቸውን መቀሌ ላይ ተመሳሳይ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ ያሳዩን ይሆናል፡፡

ሰልፉን ተከትሎ ምን ይመጣ ይሆን የሚለውን አብረን የምናየው ይሆናል፡፡

ስለሰልፉ ከሚሰጡት አስተያየቶች አንዳንዶቹ ሌላ ውይይት የሚያስነሱ ናቸው፡፡ ያንን በተቻለ አቅም እየተመላለስን እንሟገትበታለን የሚል ተስፋ አለኝ፡፡

ሰልፈኛው ከያዛቸው መፈክሮች ያንዳንዶቹን መልዕክት የማይደግፉ ወገኖች እንኳ ሕዝቡ ፍርሃትን ሰብሮ ድምጹን ለማሰማት መውጣቱን ማድነቃቸው ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡

Endalamaw Aberra