የማን መሬት?
አብርሃም በየነ
ሞት ለሰው ልጆች ፀጋም ዕዳም የሚሆንበት ጊዜ አለው። ዜጎች መብታቸው ሲደፈር፣ ነፃነታቸው ሲገፈፍ፤ ማንነታቸው ሲፋቅና የመኖራቸው ህልውና በሞት ጥላ ስር ሲወድቅ ሞት ዕዳውን ያከብድባቸዋል። የክፍያውንም ዋጋ በሕይወት ይመነዝረውና መተኪያ የሌለውን ሕይወት በሞት ወለድ አገድ ያስይዘዋል። ህዝብም የታገቱትን መብቶቹን ለማስፈታት ሞትን ይኖሩታል እንጂ አይሞቱትም ብሎ ይንቀሳቀሳል። ሰው የተፈጠረው ለመሞት ነውና ሞትን ሙቶ ሊያቸንፈው ዕምቢኝ ለሀገሬ ሲል በሞት ላይ ያምፃል። ብሎም ጅግና ይፀነሳል። ሰማዕት ይወለዳል። ህዝብም ከመቃብር በላይ የሚውል ስም በደሙ ጽፎ ለማለፍ ሆ ብሎ ይነሳል።