በጎንደር ጉዳይ የመድረክ/ዐረና ዝምታ እስከመቼ?

Medrek Logoግርማ በቀለ

መድረክ እንደ ግንባር ዐረና እንደመድረክ አባል ፓርቲና አሁን በጎንደር እየሆነ ባለው ክስተት እንደ ዋነኛና ቀዳሚ ባለጉዳይ አንድ ነገር ማለት እንዳለባቸው ይሰማኛል፡፡ በበርካታ ምክንያቶች– ዋናዎቹን ጠቅለል አድርገን ስንመለከት-

1. አንድነት ፓርቲ የመድረክ አባል በነበረበት ጊዜ አብረው እየሰሩ ከመድረክ አመራሮች አንድነት የአማራና አዲስ አበባ ልህቃን ጥርቅም ነው ተብሎ ሲነገር ነበር፡፡ በመጨረሻም አንድነት ከመድረክ በራሱ ጊዜ ወይም በመሞቱ ከአባልነት ተወገደ፡፡ ስለዚህ ዛሬ ላይ በመድረክ የ‹‹ አማራ ተወካይ›› የሚባል ቀርቶ በአማራ ተወካይነት ‹‹ የሚታማ›› የለምና ዝምታው በቀጣይ አገራዊ ፖለቲካችን ትርጉም ይኖረዋል ፡፡ መድረክ በዚህ ጉዳይ ላይ አቋሙን ግልጽ ማድረግ ለቀጣዩ የጋራ አገራዊ የለውጥ ትግልና መድረክን እንደ ኅብረብሄራዊ አገራዊ የትግል ግንባር ለምናስብ ወገኖች መጪውን የትግል አቅጣጫ ግልጽ ያደርጋል፡፡ በግልጽ ቋንቋ ዝምታው መድረክ በአማራ ላይ ተመሳሳይ አስተሳሰብ ያላቸው ስብስብ ነው የሚለውን ‹ ሃሜት › ያጠናክረዋል ፡፡

2. ከዚህ በፊት መድረክ ዘግይቶም ቢሆን በኦሮሚያ የአዲስ አበባና የፊንፍኔ የጋራ ልማት ማስተር ፕላን መነሻ አድርጎ በተነሳው ህዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ አቋሙን አሳውቆናል፣ የተወሰደውን እርምጃ አውግዟል ፡፡ ይህ የመድረክ አቋም የሁሉም የአባል ድርጅቶቹ አቋም ነው፡፡ ስለዚህ ዛሬም በጎንደርና የአካባቢው ህዝብ የወልቃይት ጠገዴን የማንነት ጥያቄ ተከትሎ የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞና የህወኃት ከአማራ ክልል ዕውቀትና ይሁንታ ውጪ እየሆነ ያለው በተመሳሳይ መድረክን ይመለከተዋል፡፡ በዚህም አቋሙን ግልጽ እንዲያደርግ ይጠበቃል ፡፡ ያለፈውን በማስታወስ ዛሬስ/በዚህ ጉዳይ ምን ይላል ? ለሚለው ጥያቄ መልስ ይሰጣል፡፡

3. ከዚህ በፊት በኦሮሚያ በነበረው ህዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ መድረክ ሲዘገይ የጉዳዩ ቀዳሚና ዋነኛ ባለቤት ኦፌኮ ከመድረክ ቀድሞና ተነጥሎ ጉዳዩን በቅርብ ተከታትሎ በመረጃና ማስረጃ አስደግፎ ስለተጨባጭ እውነታው አሳውቋል፣ አቋም ወስዷል ፡፡ ዛሬ ላይ በመድረክ ውስጥ ያለው ዐረና ይህ ጉዳይ በቀጥታ ይመለከተዋልና በተመሳሳይ በኦፊሴል አቋሙን እንዲገልጽ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ባለፈ የዐረና አቋም ‹‹ ህወኃት የትግራይ ሀዝብና ህወኃት አንድ ናቸው ›› ለሚለው ፕሮፖጋንዳውና ፣ በአንድ ወቅት አቦይ ስብሃት ለሰጡት ‹‹ ዐረና በሥልጣን ያኮረፉ ግለሰቦች የመሰረቱት እንጂ ሄደው ሄደው ከህወኃት የተለየ አቋም የላቸውም ›› ይዘት ያለው አስተያየት ግልጽ ምላሽ ይሰጣል፡፡

4. ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ህወኃት በዘራው የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲና በዘረኝነት አካሄዱ የትግራይን ህዝብ በተለይ በክልሉ ያለውን ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለመነጠል የትግራይን ክልልና ህዝብ እንደ የክፉ ቀን ዋሻ፣ መሸሸጊያና መከታ አድርጎ የሰራው ፕሮፖጋንዳ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ የዐረና አቋምና የትግራይ ክልል ነዋሪ ድጋፍ የዚህን ፕሮፖጋንዳ አከርካሪ ለመስበር፣ ጠ/ሚ/ር መለስ ‹‹ኦፕዲኦ›› ሲፋቅ ‹‹ኦነግ ›› ነው እንዳሉት ሌላው ወገን ደግሞ ‹‹ዐረና›› ሲፋቅ ‹‹ህወኃት›› ነው ወደሚል የጀመረውን ጉዞ እንዳያጠናክር በቀጣይ የለውጥ ትግላችን በኢትዮጵያዊነት መንፈስ በጭቆናና የአገዛዙ ቡድን ላይ በጋራ በአንድ ልብ በመተማመን ለዘላቂና ሰላማዊ አካታችና ፍትሃዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለምናደርገው ርብርብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

የከፋፍለህ ግዛ ፕሮፖጋንዳውን ሰብረን በመተማመን መንፈስ በኅብረት በመቆም ለአገራችንና ህዝቧ የሚበጀውን ለመተግበር ጊዜው ዛሬ ነው፡፡ የለውጡ ማዕበል የአይቀሬውን ደወል አንጠልጥሎ በፍጥነት እየተጓዘ ነውና ሁላችንን ጠራርጎ እንዳያያልፍ ከወዲሁ የመከላከያ እርከኑን በ‹‹አንድነትን›› እና በመተማመንን ከወዲሁ እንከትር ፡፡

በቸር ያገናኘን ፡፡ ሀምሌ 09/ 2008  (ግርማ በቀለ)