የወያኔ ውድቀት የአደባባይ ምሥጢር መሆኑን የሚያመላክት አጋጣሚ
ማስተዋል በለጠ (ከአዲስ አበባ)

ከደቂቃዎች በፊት ከአንዱ የመሥሪያ ቤቴ ቅርንጫፍ ወደ ዋናው መ/ቤት ስመጣ እንዲህ ሆነ። መኪናዋ ውስጥ በተላላኪነት የምትሠራ አንዲት ወጣት፣ ሹፌራችንና እኔ ብቻ ነን የነበርነው። የዛሬው ቀን የከተማችን ወሬ የሆነውን የማትሪክ ፈተና መሰረቅ አነሳሁና የተለጎመውን የሦስታችንንም አንደበት በጋራ የሀገር ጉዳይ ከፈትኩት። በዚህን ዓይነት ሁኔታ እኔ ብዙውን ጊዜ ነገር እለኩስና ዋና ሥራየ ማዳመጥ፣ ማዳነቅና ማውጣጣት ነው። ቀዳሚው ሥራየ ግን የማዋራቸው ሰዎች በኔ ላይ እምነት እንዲኖራቸው ጥረት ማድረግ ነው፤ ሰው ከተጠራጠረህ የልቡን አይናገርም። ዝም ሊል ወይም ሊዋሽህና ሊያታልልህም ይችላል።