ሀበሻ በየመን በየመን ክፍል 11
ኢትዮጵያዊያንን ያሰቃየው ግለሰብ በየመን ለፍርድ እንዲቀርብ ተጠየቀ
ሀበሻ በየመን በየመን ክፍል 11
በግሩም ተ/ይማኖት
ተንደርድሬ ጥልቅ ሳልሰናበት ውልቅ ማለት አለመደብኝም እና ወደ ዋናው ጉዳይ ከመግባቴ በፊት የዚህ ሰሞኑ ዜናዎች እንደመክፈቻ ላቋድስ፡፡ ታዲያ ዜና ዘገባው ከተለያየ አቅጣጫ በመሆኑ እና በዛ በማለቱ የዜና አምድ እንዳይመስል ስል አሳጥረዋለሁ ስለዚህ ቅድመ ይቅርታ ላቅርብ፡፡ እለት ከእለት ወደ የመን የሚፈልሰው ስደተኛ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ እንዳሳሰባቸው ቀይ መሰቀል፣ አይ ኦ ኤም እና በጉዳዩ በጥምረት እየሰሩ ያሉ ድርጅቶች አስታወቁ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከሶማሊያዊያን ይልቅ ይበልጥ እየተሰደዱ ያሉት ኢትዮጵያዊያን መሆንቸውን እና ለጉዳት ተጋላጭ እየሆኑም እንደሆነ ጨምረው አስታውቀዋል፡፡ ጉዟቸው በመረጃ ያልተደገፈ እና ህጋዊ ባልሆነ መንገድ /ህገ-ወጥ/ በመሆኑ ለዘራፊዎች ከመጋለጣቸውም በላይ ለሞት እየተዳረጉ መሆኑንም ድርጅቶቹ አስምረውበታል፡፡
በዚህ ዙሪያ ማለት የምፈልገው አይ.ኦ ኤምም ሆነ ቀይ መስቀል ከመግለጫ የዘለለ ሊያደርጉ የሚገባውን ነገር ባለማድረጋቸው በስደተኛ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሰዎችን ወደ ህግ ባለማቅረባቸው ክፍተት ፈጥረዋል፡፡ ለስደተኛው ማን ተቆርቋሪ አለ? ማን ይጠይቀናል? በማለት ሁሉ እንደፈለገ ስደተኛውን ያሰቃያል፣ ይዘርፋል፣ ይደፍራል፡፡
ከወር በፊት የየመን ሁለተኛ ከተማ ወደ ሆነችው አደን ስጓዝ ያገኘሁት ልጅ በባህር ሲመጣ አፍነው ኩላሊቱን እንደሰረቁት ሲነግረኝ ውስጤ ሁሉ ነበር በሀዘን የተርገደገደው፡፡ ይህን ሁኔታ በውስጤ ይዤ ተጨማሪ መረጃዎችን መፈላለግ ያዝኩኝ፡፡ታዲያ አንድ አጋጣሚ ያገናኘን ወዳጄ ሀረዝ ወደ ሚባል የሳዑዲ አረቢያ ጠረፍ የመብራት መስመር ዝርጋታ ስራ ላይ የተሰማራ ነው፡፡ እዚህ ቦታ ላይ አይ ኦ ኤም እና ቀይ መስቀል የመሰረቱት አንድ ካምፕ አለ፡፡ ባህር አቋርጠው የየመንን መሬት የረገጡትን ወደ እዚህ ካምፕ እንዲገቡ ታስቦ ነው የተዘጋጀው፡፡ አካባቢው ላይ ግን የተዘጋጀ ሀይል አለ፡፡ ‹‹…ከባህር እንደ ወረዱ በፒክ አፕ ሀረዝ ድረስ በሁለት መቶ የየመን ሪያል እናድርሳችሁ ይሉና ይጭኗቸዋል..››አለኝ ያ- አጋጣሚ ያገናኘን ትውልደ ኢትዮጵያዊ ወዳጄ፡፡ ምን ክፋት አለው ሀያ ኪሎ ሜትር በሁለት መቶ ሪያል ከወሰዷቸው ብዬ ወሬውን እንዲቆርጥ ላደርገው አፌን አወሬ ሳቀባብል ‹‹…በሰላም ቢያደርሷቸው ጥሩ ነበር..›› አለና ልቤን አንጥልጥሎት እርፍ፡፡
‹‹መሀል ላይ መንገድ ቀይረው ወደሚፈልጉት ቦታ ይወስዷቸዋል፡፡ አግተው ይይዙዋቸው እና ስልክ እየሰጡ ከቤተሰባቸውም ሆነ ሌላ ቦታ ካለ ዘመዳቸው ገንዘብ እንዲያስልኩ ያስደርጋሉ፡፡ የራሳቸው እስር ቤት አላቸው ወር እና ከዛም በላይ የታሰሩ ሰዎች እንዳሉ ሰምቻለሁ..›› የሚያወራው እውነት ለመሆኑ ማጣሪያ ግንባሩ ላይ ያለ ይመስል ትክ ብዬ አየሁት፡፡ ጭንቆኝ የሰማሁት አሞኝ ነው ትክ ብዬ ማየቴ እንጂ እንዳልኩት የሚነበብ ኖሮ አይደለም፡፡ አንድ ሁለቴ የየመን ጋዜጠኞች ስብሰባ ላይ በተገኘሁበት አጋጣሚዎች የማውቀው የመናዊ የግል ጋዜጣ አዘጋጅ ጋር ለመማከር ቀጠሮ ያዝንና ነገርኩት፡፡ የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ መረጃ አሰባሰበ እኔ ያላገኘሁትን ሁሉ አገኘ፡፡ ኩላሊት መሰረቁን ግን ሁላችንም ያገኘነው ነገር የለም፡፡ በረቀቀ መንገድ የሚያደርጉት ሲሆን የተገኘ ተጨማሪ መረጃ ባይኖርም ተሰረኩ ያለው ልጅ ተመርምሮ ለመታየት ተስማማ፡፡ ያለው ማራጭ ጭላንጭል ቢሆንም ከዳር መድረሱ አይቀርም እና…. በሌላው ጉዳይ ላይ ግን ጋዜጣው ለሀገር ውስጥ ሚኒስቴር፣ ለሁማን ራይት፣ ለአምንስቲ ኢንተርናሽናል ግልፅ ደብዳቤ ጻፏል፡፡ ይህ የመን ውስጥ የሚታተም ‹‹አል ብላግ››የተባለ ነፃ ጋዜጣ እንደ አቋም መግለጫ ርዕሰ አንቀጽ አድርጎ ጋዜጣውም ላይ በግልፅ አሰፈረው፡፡ እነሆ ትርጉሙን ላቅርብልዎ…
በርካታ አፋሪካዊያንን በባህር በሞካ በኩል አድርገው ወደ የመን ሲገቡ የተቀናጀ በሀይል ዘረፋ እየተደረገባቸው ነው፡፡ (ሞካ የየመን የወደብ ከተማ ነች፡፡ ሞካ ቡና በሚለው የምታስታውሱ ትኖራላችሁ፡፡ ደግሞ ለሞካ ቡና ማስታወቂያ እየሰራሁ እንዳይመስልብኝ፡፡) ሞካ በዘራፊዎቿ የታጠረች ስትሆን በርካታ ስደተኞች ለስቃይ፣ ለመከራ እየተዳረጉ ነው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያዊያን ለከፍተኛ መከራ፣ መታሰር እና መደብሰብ ተዳርገዋል፡፡ ይህ የሆነው አብዱል ገዊ የተባለ አንድ የመናዊ በርካታ ጋሻ ጃግሬዎችን አሰማርቶ ያሰዘርፋል፣ ያስራል፣ ይደበድባል፡፡ ይህን የሚያደርገው በባህር ወደ የመን የሚገቡ ኢትዮጵያዊያን ላይ መሳሪያ የታጠቁ ተከታዮቹን እያሰማራ ነው፡፡ ራሱ ያዘጋጀው እስር ቤት ያለው ሲሆን በዚህ ሰዓት ሁሉ ከወር በፊት የታሰሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ ታውቋል፡፡
በእሱ እስር ቤት ሆነው የደበደባቸው፣ የገረፋቸው፣ ጀርባቸው ቁስል በቁስል የሆነ ሞልተዋል፡፡ የተገረፉበት ሰውነታቸው የተላ፣ የደማ፣ የቆሰለ እና ጠባሳ የያዘ ሆነው ከእስር ቤቱ ውስጥ ስለሚወጡ በሞካ ጠረፍ በኩል የገባ ሀበሻ ሁሉ አብዱል ገዊን ያውቃል፡፡ በእሱ ያልተያዘ፣ ያልተገረፈ፣ ያልተዘረፈ ሀበሻ አይኖርም እና ያውቁታል፡፡ ከድብደባው ከስቃዩ ለመገላገል ሲሉ ያላቸውን ሁሉ ይከፍላሉ፡፡ የሌላቸውም ሳዑዲም ሆነ ገንዘብ ሊልክ የሚችል ዘመዳቸው እንዲልክ አስደርገው ከፍለው ይወጣሉ፡፡ መውጣት ካልቻሉ ታስረው ይበሰብሳሉ፡፡ ተዘርፈው ባዶ የቀሩት በእግር ከሞካ ተነስተው ረድዓ ድረስ ሄደው ነው ሰርተው ማግኘት የሚችሉት፡፡
አብዱል ገዊ የተባለው ግለሰብ ባረደሰው ዘረፋ ብዙዎች ተሰናክለዋል፡፡ አካል አጥተዋል፣ ሞተዋል..ስለዚህ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ፍትህ ሚኒስቴር፣ የየመን ሰብዓዊ መብት ቢሮ፣ ሁማን ራይት..ወንጀለኛው አብዱል ገዊን ለፍርድ እንዲያቀርቡ ጋዜጣው ጠይቋል፡፡ አያይዞም የወንጀለኛው እስር ቤት ተፈትሾ ያሉት እስረኞች ነፃ እንዲወጡ ሲል አበክሮ ጠይቋል፡፡ ይህን ጥያቄ ይዘን ለማናገር የሞከርናቸው አዳዲስ ባለስልጣናት ከአፍ ያልዘለለ ጥሩ ተስፋ ሰተውናል፡፡
ወደ ሌላ ዘገባ ስዞር በዚህ በያዝነው ወር ብቻ አንድ ሺህ አካባቢ ኢትዮጵያዊያን ባህር መሻገራቸውም ዋናው እና አሳሳቢው ነገር ሆኗል፡፡ ግን የተሻገሩት በሙሉ በሰላም አልደረሱም፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከአስር ቀን በፊት ከአልጀዚራ ጀምሮ በተለዩ የመገናኛ ብዙሀን የተላለፈ ዜና አንድ ጀልባ ሰምጦ ለወሬ ነጋሪ እንኳን አንድ ሰው ሳይተርፍ በሙሉ ማለቃቸው ተነግሯል፡፡ ከጅቡቲ በጀልባ ተሳፍረው ወደ የመን ሊሻገሩ ጉዞ የጀመሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እና ጥቂት ሶማሊያዊያን ጀልባው በመስመጡ በሙሉ ህይወታቸው አልፏል፡፡ ከመቶ በላይ ኢትዮጵያዊያን እንደነበሩበት የመን ውስጥ የሚታተም አንድ ጋዜጣ ሲዘግብ የጀርመን ድምፅ ራዲዮ ደግሞ ባህሩ መሀል ላይ ስለነበሩ ከውስጣቸው ሊተርፍ የቻለ አለመኖሩን ገልጽዋል፡፡ ከአይ ኦ ኤም እና ከቀይ መስቀል ያገኘሁት መረጃም ይህንኑ ዘገባ የሚያጠናክር ነው፡፡
ወደ ሌላ ዜና ስንዞር አሁንም በህገ ወጥ መንገድ አጓጓዦች ድንበር ለማሳለፍ በኮንቴነር እንደ እቃ ጠቅጥቀው ሲወስዷቸው ታፍነው አየር በማጣት ከአስራ አምስት በላይ ተጓዦች ህይወታቸው ጠፍቷል፡፡ እነዚህ ህገ-ወጥ አጓጓዦች በተለያየ ጊዜ የሚያሳልፉበትን ዘዴ በመቀያየር ይሞክራሉ፡፡ አሁንም ከቁጥጥር ለማምለጥ በርካታ ሰዎችን ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ በሚጓዝ ከባድ መኪና ላይ በተጫነ ኮንቴነር ጠቅጥቀው ረጅም ርቀት ሲሄዱ ከተጓዦች መካከል በአየር ማጣት ሞቱ፡፡ ሬሳውም ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰ ለመሆኑ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ጨምሮ የተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ዘገባ ደግሞ እንዲሁ በህገ-ወጥ መንገድ ወደ የመን ሊጓጓዙ ተዘጋጅተው ከነበሩ መካከል ጅቡቲ ውስጥ አራቱ ታርደው ተገኝተዋል፡፡ ከከተማው ወጥቶ ጀልባ የሚሳፈሩበት ቦታ መሄጃ መንገድ ላይ ታርደው ስለተገኙት አራት ኢትዮጵያዊያን የጅቡቲ ፖሊስ እያጣራሁ ነው ብሏል፡፡ ቢጣራም ባይጣራም በየቦታው ማለቃችን፣ መርገፋችን እንደቀጠለ መሆኑ ግን አሳዛኝ ነገር ሆኖ ቀርቷል፡፡
ወደ ሌላ ርዕስ ስንዞር ሶማሊያ ውስጥ ካሉት የኢትዮጵያ ወታደሮች ጋር የዘመቱ እንደሆኑ የተናገሩ ሁለት ወታደሮች ከድተው ወደ የመን የገቡት ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡ በተያያዘ ዘገባ አርባ ስምንት የኤርትራ ወታደሮችም ከነ መሳሪያቸው ወደ የመን በዚህ ሳምንት ገብተዋል፡፡
አንድ እሁድ ማታ እንደ እድል ሆኖ ጨለማ በዋጣት የመን መብራት አገኘንና አሜሪካን ድምጽ ሬድዮን አዳመጥን፡፡ ታዲያ ሁለት ነገሮች ሳቡኝ፡፡ አንደኛው በሊቢያ የፈላ ውሀ የተደፋባት እና በማልታ በህክምና ላይ ስለምትገኘው ሸዋዬ…. ስላለችበት ሁኔታ ቃለ-ምልልስ የተደረገበት ነው፡፡ ጉዳይዋ እየተድበሰበሰ በመሆኑ ለአስታዋሽዋ የቪኦኤ ጋዜጠኛ ምስጋናዬን በውስጤ ቸርኳት፡፡ ቀጣዩ ፕሮግራም በኢትዮጵያዊያን ሴቶች በተለይ አረብ ሀገር በሚሰደዱ እና በሚደርስባቸው ችግር ላይ አንድ ስብሰባ አሜሪካን ውስጥ ሊዘጋጅ መሆኑን ያበሰረ ነበር፡፡ ደስ ይላል፡፡ ግን የችግሩ ተጠቂዎች በጉባኤው ላይ እንዲገኙ ያልተጋበዙ በመሆኑ ያለውን ችግር የሚያስረዳቸው ማን ይሆን? የሚል ጥያቄ ውሰጤ ተላወሰ፡፡ ወይስ በመላምት ይወያዩበት ይሆን የሚል እሳቤ ስንቅር አለብኝ፡፡
ባለፈው ስሰናበት ‹‹…ወደ አደን ወዳደረኩት ጎዞ እናምራ፡፡ በየቦታው ድልድይ ማየቴን አስታውሳለሁ ግን ውሀ የሚባል የምራቅ ጠብታ ያህል አለመኖሩ ገርሞኛል፡፡ ታዲያ ይህን ግርምቴን ቋጥሬ ከምጓዝ አልኩ እና አንዱን ‹‹ወንዝ ነው እንዳይባል ድልድይ ብቻ ነው ውሀ የለውም ለምንድን ነው?›› አልኩት ‹‹..ኢንሽ አላህ አንድ ቀን ሲዘንብ ወንዝ ይሆናል›› ብሎ አሳቀኝ፡፡ አደን እስክደርስ የተለየ ነገር የለም፡፡ ያው ተራራ፣ የጫት እርሻ ነው፡፡ አደን ካየኋቸው ቦታዎች ግን በሳቲን የገረመኝ ነውና ስለ እሱ በሰፊው ማውጋት ፈለኩ፡፡ በመጀመሪያ የገጠመኝ ኢትዮጵያዊ የኔ ቢጤ ነበር፡፡..›› ብዬ ነበር፡፡ በዛ ፅሁፌ የየመን ሁለተኛ ከተማ ስለሆነችው አደን አንስቼ በሳቲን ስለሚባለው ቦታ ለማውራት ነው ቀጠሯችን እነሆ እኔ ቀጥያለሁ…..
አንድ ኢትዮጵዊ የኔ ብጤ ነው መጀመሪያ የገጠመኝ፡፡ ‹‹ነፍሱ በባህር ከመጣሁ ቅርብ ጊዜዬ ነው እባክህ ለዛሬ እራት ላስቸግርህ?…›› ቢለኝም ከእኔ በፊት ባለ መኪናውን ሲለምን እያየሁ ስለነበረ አልገረመኝም፡፡ ያው በባህር ሲገባ መለመንም ሆነ መኪና ማጠብ…የመሳሰሉት ያለ ነው እና አዲስም አልሆነብኝም፡፡ በአንድ ወቅት ጥበቡ የሚባል አሁን ሰነዓ ከተማ ውስጥ ታዋቂ የሀበሻ ፀጉር ቆራጭ የመን ውስጥ ማሳተም ጀምሬ ለነበረው ‹‹ጣዕም›› የተሰኘ ጋዜጣ ቃለ-ምልልስ ሳደርግለት ‹‹..ባሳቲን የደሀ ማረፊያ ሳሎን…›› ብሎ የነገረኝን አስታወስኩ፡፡ ስለዚህች ቦታ ሲገልፅልኝም‹‹…ማንም በባህር የመጣ የሚያርፍባት..በሀምሳ የየመን ሪያል ምሳ የሚበላባት…ሀበሻዎችና ሶማሌዎች በልመናም ሆነ በተለያየ ነገር እስኪቋቋሙ የሚከርሙባት… ብሎኝ ነበር..››ልጁን ላወራው ፈለኩ፡፡ እሱ ደግሞ የምሰጠውን ሰጠቼው ወደ ሌላ ሰው ዞሮ ስራውን ሊያጧጡፍ እንደቸኮለ ነው ሁኔታው ያሳበቀልኝ፡፡ታዲያ እንደሜትሮሎጂ ግምቴ መሆኑን ልብ በሉልኝ፡፡የአየር ትንበያ ሳይሆን የፍላጎት ትንበያ ቢባልም ያስኪዳል፡፡ እራት አብረን እንብላ የሚለው ጥያቄዬን መጠነኛ ግልምጫ በታከለበት ሁኔታ ተቃራኒ መልስ ሰጠኝ፡፡ ‹‹ለእኔ እራት የምትከፍለውን ብትሰጠኝ ለነገ ሙሉ ቀን አብቃቃዋለሁ›› አለኝ፡፡ በዶላር የማወጣ ብዙ የምመዝ መስሎት ይሆናል..እኔም ‹‹..አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው ታላቅ ችሎታ ነው..›› የሚለውን ዜማ በውስጤ እያጠነጠንኩ እንደሆነ ማን በነገረው፡፡ ቀነስ ያለ ምግብ እና መኝታ ያለበት እንዲጠቁመኝ መፈለጌን እኔ ካልነገርኩትስ በምን ያውቃል?
እኔም ቀነስ ያለውን ቤት ፈልጌ እንደሆነ እና ለነገውም የሚሆን ልሰጠው እንደምችል በዛውም የሚቀንስ መኝታ ያለበት ሆቴል እንዲያሳየኝ ነገርኩት፡፡ ፍልጥ ፍልጥ የሚያክል ባቄላ ያለበት ፉል በላን፡፡ ‹‹..ኬሻ በጠረባ አለ እዛ ትደቅሳለህ..›› የአሜሪካ ጊቢ ቋንቋ በመሆኗ የአዲስ በአበባ ልጅ ይሆን አልኩና ጠየኩት፡፡ ትግራይ አዲግራት አካባቢ መሆኑን እና አዲስ አበባ ትራንዚት ሲያደርግ አሜሪካን ጊቢ ሁለት ጊዜ እንዳደረ ነገረኝ፡፡
‹‹ታዲያ ኬሻ በጠረባ ያልከው…›› አቤት ፍጥነቱ…ቀልቀል ያለ ፈጣን ምላሽ ሰጠኝ፡፡ ‹‹ አሀ አልተግባባንም ማለት ነው አነ ፈከርት ሙምኪን ትሽቲ በናት?›› ምናልባት ሴቶች ትፈልጋለህ ብዬ አስቤ ነው..ማለቱ ነበር፡፡ አረቢኛ አነጋገሩ የከረመ መሆኑን ያቃጥራል፡፡ ለምን ዋሸኝ ስል በውስጤ አልጎመጎምኩ፡፡ ቢሆንም ሳልጠይው አላለፍኩትም፡፡ ደግሞ ለመጠየቅ አረቢኛ እንዴት ለመድክ የመጣሁት በቅርቡ በባህር ነው ብለኸኛል አልኩት፡፡ ወደ የመን ስመጣ የመጀመሪያዬ አይደለም፡፡ ለሶስተኛ ጊዜ ነው፡፡ ወደ ሳዑዲ እሄድና ስያዝ ዞሬ በዚህ እመለሳለሁ፡፡ እንዴት አይነት ነገር ነው ይህን ስቃይ እያዩ የሚመላለሱትን ሁሉ አሰብኳቸው፡፡
‹‹ለምን ይሆን የእሳት እራት ያደረገን?
መጥፊያችንን ያስወደደን›› ብዬ የጻፍኳት ባለሁለት መስመር ግጥም ትዝ አለችኝ፡፡ ወዲያውም ትንሽ አንከስ ሲል አይቼ ለጠየኩት ጥያቄ የሰጠኝ መልስ ‹‹ከዚህ በፊት ስመላለስ ምንም ያልገጠመኝን ዘንድሮ ገና ጉድ ተሰራሁ ገላዬን አጣሁ፡፡ተጫወቱብኝ..›› በቁጭት ራሱን ወዘወዘ እንባው ተንቆረዘዘ፡፡ ገላህን ያጣኸው በምን ሰበብ ነው አልኩት፡፡ እጄን አፈፍ አድርጎ ሲይዘኝ ደነገጥኩ፡፡ በሆዴም ያስደንግጥህ የአባቴ አምላክ ብያለሁ መሰለኝ ብቻ አሁን አላስታውሰውም፡፡ ጎኑ ላይ ወስዶ አስዳበሰኝ፡፡ ያበጠ ነገር ለመኖሩ አልተጠራጠርኩም፡፡ ግን ምን ሊያስረዳኝ እንደፈለገ አልገባኝም፡፡
አስደንጋጩን ዜና ያሰማኝ ግን እንዳልገባኝ ከነገርኩት በኋላ ነው፡፡ ኩላሊቴን የተሰረኩ ጎዶሎ ሆኛለሁ እንደልብ አልንቀሳቀስም አለኝ፡፡ ሰውነቴ ተብረከረከ፡፡ፈራሁ ለእሱ አይደለም ለራሴ ነው የፈራሁት፡፡ ሳላስበው በስሜት ተውጨ የራሴን ኩላሊት አካባቢ ዳበስኩ፡፡
ተመስጌን አለ፡፡
ከእዛ አካባቢ ቶሎ መሄድም አስቤያለሁ፡፡ የመን ከገባሁ እንደዛን ቀን ፈርቼ አላውቅም፡፡ ይበልጥ መስማትና ማወቅ ፈለኩ፡፡ እንዴት ሰረቁህ አልኩት መንተባተብ እና ፈርሃት በታከለበት ድምጸት፡፡
ከባህር እንደወረድን ሀረጥ ድረስ እናደርሳችኋለን ሲሉ እውነት መስሎን ተሳፈርን ሶስት ነን፡፡ መሀል ላይ አቁመው አወረዱን፡፡ ገንዘብ አምጡ አሉን፡፡ የለንም ነበረና ታሰርን፡፡ የሚገርመው ሁላችንም ታመምን ምን እንደሰጡን አናውቅም በሁዋላ ራሴን ያገኘሁት ወደ አደን ከተማ መግቢያ አንድ ኪሎ ሜትር ሲቀረው ነው፡፡ የሆነ ዛፍ ስር አድርገውኝ… ራሴን እንድመግብ ነው መሰለኝ አጠገቤ ምግብ አስቀምጠው ሄደዋል ስነቃ እርቦኝ ስለነበር ጥርግ አድርጌ በላሁ፡፡ከምን ያህል ሰዓት በኋላ ወይም ስንት ቀን ራሴን እንደሳትኩ አላወኩም፡፡…ባነቀው እንባ ንግግሩ ተቋረጠ፡፡
ምን ማለት እንዳለብኝ ግራ ገባኝ ሆድ ብሶኝ የተናነቀኝን እንባ ለቅቄ ቁስሉን ቀስቅሼ ሆድ እንዳላስብሰው ፈለኩ እና ርዕስ ለማስለወጥ ‹‹ቅድም ሴቶች ከፈለክ ብዬ ነው ያልከኝ በገንዘብ የሚሰሩ ሴቶች አሉ እንዴ?›› አልኩ፡፡
እግዚአብሄር ይስጠው ልብ ሳይለው ለጠየኩት ምላሽ ሰጠኝ፡፡ ‹‹በሳቲን በሁለት መቶ፣ በሶስት መቶ፣ እስከ አምስት መቶ የሚሰሩ አሉ፡፡ ታዲያ አዳር ሙሉ አይደለም፡፡ ቀምሰህ ወደምትተኛበት አንዱ ጥግ መደቀስ ነው፡፡ ተረኛው ደግሞ…›› ሶማሊያዊያን እና ኢትዮጵያዊያን እንደሆኑ የሚሰሩት ነገረኝ፡፡ ጎበዝ ልብ በሉ ይሄ የተጠራው ብር እዛው በሳቲን ውስጥ ካልሆነ ከዛ ክልል ውጭ ምሳ እንኳን የሚገዛ አይደለም፡፡ በሳቲን የተባለው ቦታን ለማየት የነበረኝ ጉጉት በእጥፍ ጨመረ፡፡ እንደ ሰባተኛ በዝቅተኛ ሳንቲም የሚቸረቸረው ሰውነት ግን አምሮኝ አይደለም፡፡ ወገኔ በስደት አለም የሚኖረው ኑሮን ማየት ለእለት ጉርስ በማይሆን ገንዘብ ገላን የሚሸቅጡብትን ህይወት ማየት ነበር ሀሳቤ፡፡ በማግስቱ ያየሁት ነገር ግን በጣም ተስፋ የሚያስቆርጥ ሆኖ ነው ያገኘሁት ሙሉውን ምን እንደሚመስል አስዳስሼዎት ሀበሻ በየመንን ባጠናቅቀው መረጥኩ፡፡ ስለዚህ እመለስበታለሁ ብዬ ብንሰነባበት መረጥኩ፡፡
የከርሞ ሰው ይበለን፡፡
አሜን!!!