ወያኔ መሞቻውን፤ እኛ መሰንበቻውን
ይገረም አለሙ
“ወያኔ የራሱን መቃብር እየቆፈረ ሞቱን ሲያፋጥን፤ ተቃዋሚዎች ገንገንዘው ሳጥን ለመክተትም ሆነ ከቀብር ስፍራ አድርሰው አፈር ለመመለስ የሚችሉ አልሆኑም”

እኔ ከምኑም የለሁበት ተቀዋሚም ደጋፊም አይደለሁም በሚል ጭንብል ተሸፍኖ የሚኖረው ክፍል ሲቀር ሌላው በሁለቱ ጎራ ይመደባል። በወያኔ ጎራ ያለው ወገን ለአባልነትም ይሁን ለደጋፊነት ያበቃው ምክንያት ምንም ይሁን ባለው አቅም በሚችለው መንገድ የወያኔን ዕድሜ ለማራዘም ያስችላል ብሎ ያመነበትን ይሠራል። እንደውም አንዳንዱ ያለ ወያኔ መኖር እንደማይቻል ራሱን አሳምኖ ሞቴን ከወያኔ ጋራ ያለ ነው የሚመስለው። በዚህ ጎራ የተሰለፉ ሰዎች ሆነ ብለው አቅደው ሊገኝ የሚችለውን ውጤት ናፍቀው የወያኔን ዕድሜ በሚያሳጥር ተግባር ላይ አይሰማሩም። የውስጥ አርበኞች ካልሆኑ በስተቀር።