ነፃ መውጣት እንፈልጋለን አንፈልግም?
ዳዊት ዳባ
ዛሬ እየሰፋ እየገዘፈና ጉልበት እያገኘ የመጣው ህዝባዊ እንቢታ ከዐረቡ ሀገሩ ህዝባዊ አልገዛም ባይነት የጀመረ ይመስለኛል። ያኔ ከዚህ ሥርዓት በዚህም መንገድ መገላገልም ይቻላል ለካ? የሚለው እሰቦት በአዕምሮው ያልዞረ ኢትዮጵያዊ ነበር ለማለት አይቻልም። የሥርዓቱም ደጋፊዎችም ቢሆኑ በግልባጩ እንቅልፍ ያጡበት ጉዳይ ነበር። አልገዛም ባይነቱ በኛ ሀገር ይሄ-ያ ይጎድለዋል። ይህ አደጋ አለው። በዚህ አንመሳሰልም ይሉ የነበሩትም ቢሆን ግምት ውስጥ አስገብተው አስበውበት ስለነበር ነው። ኃላፊነት ወስደው ይሠሩበት የጀመሩ ስብስቦች እርግፍ አድርገው ቢተዉትም። ድርጅቶች የስትራተጂ ለውጥ ቢያደርጉና ትኩረታቸው ወደሌላ ቢያዘነብልም ሂደቱ የሚገታ አልሆነም።