ለልጅ የሳቁለት፣ ለውሻ የሮጡለት፣ ለፖለቲከኛ ያጨበጨቡለት
ይገረም አለሙ
የአበው ተረት ለልጅ የሳቁለት ለውሻ የሮጡለት ነው የሚለው። ለፖለቲከኛ ያጨበጨቡለት የሚል ቢጨመርበት ተስማሚ ይመስለኛል። ልጅ ከሳቁለት ሁሉ ቦታ እየገባ ነገር ያበላሻል፤ ውሻ ከሮጡለት ጥሎ ካላንደባለለ ወይ ካልቦጨቀ አይመለስም ፖለቲከኛም ካጨበጨቡለት አበው ልቤ አደገና ያለ ቁመቴ አላስገባ አለኝ የገዛ ቤቴ እንደሚሉት ይሆንና ከእኔ በላይ ለአሳር በሚል መታበይ ብዙ ጥፋት ያደርሳል ኋላም ራሱን ያዋርዳል። እኛም ጥሎብን ይሁን ባህል ሆኖብን ባይታወቅም እየኮተኮቱ ማሰደግ እየገሩ ለወግ ማዕረግ ከማብቃት ይልቅ እያሞካሹ ማበላሹትን እያጨበጨቡ ወደ ገድል መግፋቱን ተክነንበታል። በዚህ መንገድ ስንት ለሀገርና ለወገን ሊጠቅሙ ይችሉ የነበሩ ሰዎችን አጥተናል።