የሰሜን አፍሪካው አመፅ በኢትዮጵያም የማይከሰትበት ምክንያት እንደሌለ ተገለፀ

ሰሞኑን እየተካሄደ ያለውና የአለምን ቀልብ የሳበው የሰሜን አፍሪካ አመፅ በኢትዮጵያ የማይከሰትበት ምክንያት እንደሌለ ሰርክ አዲስ የዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ዋና ፀሀፊ አቶ አንዱአለም አራጌና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡ የአንድነት ለፍትህትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ወጣት አንዱአለም አራጌ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰሞኑን በአመፅ ላይ ከሚገኙት የሰሜን አፍሪካ ሀገራት ህዝቦች በከፋ የኑሮና የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ተመሳሳይ አመፅ ማድረጉ እንደማይቀር አስታውቋል፡፡ ይህንን እንዲል እርግጠኛ የደረገውን ምክንያትም “የኢትዮጵያ ህዝብ በታሪክም ሆነ በሞራል ከሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት ስለማያንስ ነው” በማለት አስረድቷል፡፡

መንግሥት አየወሰደ ያለው የዋጋ ማረጋጊያ እርግጠኝነቱን ይቀንስበት እንደሆነ የጠየቅነው አቶ አንዱአለም “50% ያህል የንግድ እንቅስቃሴውን የያዘው ኢህአዴግ ራሱ እንደመሆኑና ዋጋዎች እየናሩ ሲሄዱ በዝምታ እንደመመልከቱ ከተጠያቂነት የሚድንበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡” በማለት መልሷል፡፡ የመንግስትን እርምጃ “ኢህአዴግ ነጋዴ እንደ መሆኑ ይህን እርምጃ መውሰዱ ዘረፋውን ቀንሶ በስልጣን ለመቆየት መምረጡን ያሳያል” ሲል አጣጥሎታል፡፡

ከአስተያየት ሰጭዎቻችን አንዱ የሆነው የስነ-ልቦና ባለሙያ ወጣት እስጢፋኖስ “እስከአሁንም ድረስ ህዝቡ የ97 ምርጫ የፈጠረበት ፍርሃት ይዞት እንጂ የቱኒዚያና የሌሎች የሰሜን አፍሪካ ሀገራት ህዝቦች ያለባቸው ችግሮች ሳይኖርበት ቀርቶ አይደለም፡፡ በመሆኑም በእርግጠኝነት ህዝቡ ሆ ብሎ መቼ እንደሚነሳ መተንበይ ባልችልም መነሳቱ ግን አይቀርም፡፡” በማለት ከአቶ አንዱአለም ጋር የሚቀራረብ አስተያየት ሰጥቷል፡፡ አቶ እስጢፋኖት የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን የሚኝበትን ሁኔታ በሙያ ቋንቋው የ “approach-approach conflict ነው” በማለት ያስረዳል፡፡ ሀሳቡንም “ህዝቡ በመልካም አስተዳደር እጦት፣ በስራ እጦት፣ በሰብአዊ ክብር እጦት፣ በአጠቃላይ በብዙ እጦቶች ውስጥ ይገኛል፡፡ እነዚህን እጦቶች የፈጠረበትን መንግስት መቃወምና ለውጥ ለማምጣት መሞከር ደግሞ በ97 እንደሆነው ሁሉ እንደሚያስገድለው ያውቃል፡፡ ስለዚህ ከሁለት መጥፎ የመምረጥ አጣብቂኝ ውስጥ “approach-approach conflict ውስጥ ገብቷል፡፡” በማለት አብራርቷል::

የስነ-ልቦና ባለሙያው ችግሮቹ በዚሁ ከቀጠሉ ከፍርሃት በላይ ሊሆኑ እንደሚችሉና ህዝቡ የሚፈልገውን ለውጥ ሕይወቱን ከፍሎም ቢሆን ሊያመጣው እንደሚችል ይናገራል፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን የሰጠን ሌላው ወጣት የትያትር ባለሙያ ወርቅነህ ነው፡፡ ወርቅነህም እንደ እስጢፋኖስ ሁሉ በኢትዮጵያም አመፁ ለመከሰቱ ምንም ጥርጣሬ የለውም፡፡ አመፁ እንደይከሰት በመስጋት መንግስት እየወሰዳቸው ያሉት እርምጃዎች የበለጠ አመፅን ሊያቀርቡ የሚችሉ እንደሆኑ ይናገራል፡፡ ሀሳቡን ያብራራውም “መንግስት በአንዳንድ ሸቀጦች የመሸጫ ዋጋ ላይ ቅናሽ ማድረጉና የኑሮ ውድነትን የፈጠሩት ነጋዴዎች እንደሆኑ መወትወቱ የህዝቡ ጣት ወደ ነጋዴው እንዲቀሰር በማሰብና ኃጢያቱን ከራሱ ለማውረድ ነበር፡፡ ሆኖም ይህ የማታለል ሙከራ ችግሩ የቱ ጋር እንደሆነ በሚገባ የሚገነዘበውን ህዝብ የበለጠ ሲያበሳጨው መንግስትን ደግሞ ከነጋዴው ጋር አላትሞታል፡፡” በማለትና የመንግስትና አተርፍባይ አጉዳይነት በማሳየት ነው፡፡

ወርቅነህ ከዜና አገልግሎት ክፍላችን በጉዳዩ ላይ ተቃዋሚዎች ሊኖራዋቸው የሚገባውን ሚና አስመልክቶ ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው አስተያየት ተቋዋሚ ፓርቲዎች አምባገነን መንግስትን ለማስወገድ ግንባር ቀደም ሚና መጫወት የነበረባቸው ቢሆንም ይህንን ሚናቸውን በሚገባ እየተወጡ እንዳልሆነ ገልፆአል፡፡ ወጣቱ አክሎም ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ከድክመታቸው በመታረም ከሰሞኑ በሰሜን አፍሪካ እንዳየነው በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ሁኔታ ቢከሰት ስልጣኑን የሚይዝ ተተኪ ሃይል ጠፍቶ ወታደሩ ክፍል ሀገራችንን የሚቆጣጠርበት ሁኔታ እንዳይፈጠር ተቃዋሚዎች የውስጥ ችግሮቻቸውን በመፍታት ይህን ክፍተት ለመሙላት ሊዘጋጁ እንደሚገባ ተናግሯል፡፡

ሦስቱ ወጣቶችም ሆኑ ሌሎች የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሰሜን አፍሪካን አመፅ በተመለከተ በርካታ ተመሳሳይ አቋሞችን ይጋራሉ፡፡ በተለይ ወጣት ወርቅነህ “እኛ ኢትዮጵያውያን ለነፃነት ያደረግነው ተጋድሎ ለሌሎች አፍሪካውያን ወገኖቻችን ተምሳሌት እንደሆነው ሁሉ እነሱም አሁን ከአምባገነን መንግስታት ነፃ ለመውጣት እያደረጉት ያሉት ትግል ለኛ አርአያ የማይሆንበት ምክንያት የለም” በማለት የገለፀውን ሀሳብ አብዛኞቹ አስተያየት ሰጪዎች የሚጋሩት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡