ማለቴ ለማኝነት ( ሄኖክ የሺጥላ )

ማለቴ ለማኝነት ( ሄኖክ የሺጥላ )

ቋር ላይ የተነጣጠረ ምስማር ቢጣመም ጥፋቱ የምስማሩ ፣ ወይም የቋሩ ወይም የመዶሻው አይደለም ። ጥፋቱ ያናጢው ነው ።
በግብርና መር ኢኮኖሚ የሚመራ ስርዓት፣ ህዝቡ በድርቅ ምክንያት ለረሃብ ወይም ረሃቡ ገፍቶ ለቸነፈር ‘ና ለጠኔ ቢዳረግ ፣ ችግሩ የገበሬው ፣ ወይም የመሬቱ ወይም የአየሩ አይደለም ፣ ችግሩ የስርዓቱ ነው ። ድርቅ ተፈጥሯዊ ክስተት ነው ። ረሃብን ግን ተፈጥሯዊ የሚያደርገው የአስተዳደር ችግር ነው ። እንድንናገር ከተፈቀደልን የሃገረችን ነገር “ለማ” ብለን ሳንጨርስ “ገለማ” የሆነውም በዚሁ በአስተዳደር ዙሪያ ባለው ችግር ነው( ይመስለናል ይላሉ ሙሁሮቹ!) ። አስተዳደር ስል ፣ እያስተዳደርን ነው ለሚሉት ቦታ መስጠቴ አይደለም ፥ ግን አለ አይደል ፎርማል ለመሆን እንጂ ። ፎርማል ስል <ፎርማሊን> ትዝ አለኝ ። አዎ ፎርማሊን በአስተሳስቡ ለሞተ ሰው የሚወጋ የ ድንቁርና ማድረቂያ መድሃኒት ቢሆን ኖሮ ፣ ወያኔን ምን ትጠብቃለህ ” ተጠቀም እንጂ !” ብዬ የማይነጥፍ ምክሬን በለገስኩ !
እሱንም በልመና ኣስገብተው በልማታችን ባይሉን ምን ኣለ በሉ !

ባደጉ ሀገሮች ድርቅ ከአንድ ተፍጥሯዊ ክስተትነቱ ባሻገር ፣ የምርምር እና የጥናት አጋጣሚን የሚፈጥር አንድ ትልቅ ቤተ ሙከራም ነው ። መሬት መንቀጥቀጥም ይሁን ፣ የመሬት መንሸራተት ፣ ከክስተትነት ባለፈ ለተሻለ መረዳት እና የወደፊት ጥንቃቄ ትተውት የሚሄዱት ለጥናት እና ምርምር ናሙና የሚሆን ሳይንሳዊ አሻራ አላቸው ። በኛ ሀገር ግን ሰውነቱን ጉበት ቀብቶ እንደሚንዘፈዘፍ አጭበርባሪ ለማኝ ፣ መንግስት ድርቁን እንደጉበት ሰውነቱን ተቀብቶ ፣ ሀገሪቷን እያንዘፈዘፈ ስንዴ መለመኛ ከማድረግ ባሻገር ፥ ከዛሬ ተምሮ ነገን ምን ማድረግ እንዳለበት ወደሚወስድ ሰዋዊ ባህሪ ለመመለስ ሲሞክር ኣላየነውም ። ይህ የመንግስት ባህሪ አንገት የሚያስቀረቅር ከሆነ ደሞ ሰንበት በት ብሏል ።
እንደውም ሳስበው ፣ የሀገራችን ኢኮኖሚ መሰረቱ ወረቀት ላይ ” ግብርና መር ” በተግባር ግን ” ልመና መር ” መሆኑ ነው ። ይህ ደሞ ስልጣንን ያለ እውቀት መቆናጠጥ ከሚያጎናጽፈው ንቀት እና ትቢት ባሻገር ፣የስልጣን ባለቤት ነኝ ለሚለው አካል፥ አብሮ በተጨማሪነት የሚደጉመው ውል አልባነት ፣ ሃሳብ አልባነት ፣ ጥበብ አልባነት ከፖለቲካ ኪሳራነት በተጨማሪ የክሽፈቱ ምንዳና ማሳያም በመሆኑ ነው ! ማለቴ ለማኝነቱ እና እግር ስር እንደ ህጣን ኣለሁ የሚለው ፈጣጣ (ፈንጣጣ) ልማቱም የግራ መጋባት እና የእውቀት ማነስ ውጤት ነው። ወጠጤ ጎልማሶች ኣልረዳ ኣሉን እንጂ!
በክላሽ እና በ ትራሽ ፖለቲካቸው ኣደከሙን እንጂ ! ስለ ሰ’ብኣዊ መብት ስትጠይቅ ስለ ኮብል ስቶን እያወሩ የመረዳት እና የማስረዳት ኣቅማችንን ለነሱ ስንል ” እታች” ኣወረዱት እንጂ ። ሀገር ስንል ጎሳ እያሉ ፥ መሬት ስንል ኣፈር እያሉ ፥ ህዝብ ስንል ፥ ዝንብ እያሉ ፥ ቆሻሻ ሌጋሲያቸውን ታሪክ ብለው ኣሰፈሩት ! “ያስፈራሉም ” ያሳፍራሉም !