የጅዳው አለም ዐቀፉ ትምህርት ቤታችንና ጎርፉ

ተፃፈ-ከጀማል መሀመድ

በበረሀ ዝናብን መፍራት ያልተለመደ ቢመስልም የጅዳና አካባቢዋ ነዋሪዎች ከአምናው የማይረሳ ትራጄዲ ወዲህ ሙቀትን በማማረሩ ሰንፈናል፡፡
በተንጣለሉትና አለምዐቀፋዊ ስታንዳርዳቸውን በጠበቁት ውብ የጅዳ ጎዳናዎች ጎርፉ ሲገማሸር ጥቃቅን ውዳቂዎችን ብቻ ሳይሆን ሽንጣም አውቶሞቢሎችን ሲያገላብጥ መመልከት ማስገረሙ እያለፈበት ነው!በውድና ውብ መኪናዎች ልቡ የማለለ አድናቂ ፍቅሩን መቀነስ ከዳዳ በክረምት የጅዳን ቀለበት መንገዶች ይጎበኝ!

ዝቅተኛና በጣም ዝቅተኛ ሞዴል መኪናዎችን በመጠቀም የምንታወቀው ሀበሾች ይህች አጋጣሚ ሞራላችን የሚስተካከልባት ወረክሾፕ ናት፡፡በሚሊዮን በሚቆጠር ሪያልና በጥቂት ሺ ሪያል የተገዙ መኪናዎች እንደመቃብር ጉድጓድ እኩል የሚሆኑባት የጎርፍ ዕለታት ለሰማዩ ጌታ ምልጃና ምስጋና የሚዘወተርባቸው ናቸው፡፡

ወደርዕሴ ስመለስ…ልጆቻችን ት/ቤት ሆነውና ቤት ውስጥ ተቀምጠው ሲዘንብ የሚሰማን ስሜት በጣም ይለያያል፡፡እንደሌላው ዜጋ በትምህርት ቤቱ ሰርቪስ ከመጠቀሙ በላይ እኛው ስለምናመላልስ ሰማዩ ማኩረፍ ሲጀምር ካለንበት ስራችንን ጥለን ወደ ት/ቤቱ እንራወጣለን፡፡መምህራኖቹም ሆኑ የት/ቤቱ አስተዳደር በሚያደርጉት የተመሰገነ መረባረብ ልጆቻችንን ተቀራምተን ወደየአቅጣጫችን እንበታተናለን፡፡

በዝናቡ ተማሪዎችን ለወላጆች በማስረከብ ሂደት የት/ቤቱ አስተዳደር የሚያከናውነው ተግባር እንዳለ ሆኖ በዝናብ ምክንያት ትምህርት በማይኖርባቸው ቀናት መረጃውን አስቀድሞ በመግለፁ በኩል ድክመት ይታያል::

መደበኛ ትምህርት ከመጀመሩ በፊት በተከሰተ ዝናብ ትምህርት ማስተማር እንደማይቻል የወሰኑ አንዳንድ ት/ቤቶች ተማሪና ወላጅ እንዳይንገላቱ በማሰብ አስቀድሞ ባስመዘገቡት ተንቀሳቃሽ ስልክ ለእያንዳንዱ ወላጅ መልዕክት ይልካሉ፡፡ሲታሰብ አስቸጋሪ ቢመስልም ለመፈፀም ከተፈለገ ተግባሩ ቀላል ነው፡፡ የአጠቃላይ ወላጅ ተንቀሳቃሽ ስልክ ቁጥር ተሰብስቦ ከተዘጋጀ በኋላ በአንድ ጊዜ ጫና ብቻ በሺህ ለሚቆጠሩ መስመሮች ተመሳሳዩን መልዕክት
ማስተላለፍ ይቻላል፡፡

ባለንበት የቴክኖሎጂ ዘመን በሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎችን የያዘ ት/ቤት የራሱ ዌብ-ሳይት ባይኖረው ምን ይሰማችኋል?ኢ-ሜይል አድራሻ ባይኖረውስ? ወደ ግቢዎቹ መግቢያ በር ከተሰቀሉት የት/ቤቱ ስም፣ስልክና ፋክስ ቁጥር የሚያመለክቱ ማስታወቂያዎች ‘billboard’ በተጨማሪ የገቢ መሰብሰቢያ ደረሰኙ ላይ ይህን ባለመመልከቴ ነጥቡን አንስቼ ከት/ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ አብዶ አባፉጊ ከወር በፊት በተወያየሁበት ወቅት ይህን ከግዴለሽነት ያልዘለለ ጉዳይ ማስተካከል እንደሚገባ አበክሬ ገልጨላቸዋለሁ፡፡

ዝናብን በተመለከተ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የት/ቤቱና ወላጅ መካከል ያለውን ግኑኝነት ከማጠናከር አንፃር ድህረ-ገፅ የሚጫወተው ሚና ከግምት መጨመር የግድ ነው፡፡

ትምህርት ቤቱን በሞግዚትነት የሚመራው የኮሚዩኒቲው ማህበር ወይም የት/ቤቱ አስተዳደር ያቋቋሙት የህዝብ ግኑኝነት ዘርፍ ባለመኖሩ ይህ አይነቱ ጉዳይ የማን ሀላፊነት እንደሆነ ግልፅ ባይሆንም በቅርቡ የተመረጠው የወላጅ ኮሚቴ መፍትሄ ይፈጥራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን!

ተፃፈ-ከጀማል መሀመድ
ጅዳ-ሳዑዲ አረቢያ
[email protected]