የሃይማኖት አባቶች የሰላም ጥሪ እንዲያቀርቡ ተጠየቁ
በሀገሪቱ የሚታየው የእርስ በእርስ ግጭትና ህዝባዊ አመፅ ሀገር ከመበታተኑ በፊት የሃይማኖት አባቶች ተሰሚነታቸውን ተጠቅመው የሰላም ጥሪ እንዲያቀርቡ ተጠየቁ፡፡
የመግባባት አንድነትና ሰላም ማህበር (ሰላም) ባወጣው መግለጫ፤ በሌሎች ሀገራት የሚታየው የእርስ በእርስ ግጭት ያስከተለው ጉዳትና ቀውስ በአገራችን እንዳይፈጠር የሃይማኖት አባቶች የሽምግልና ሸንጎ በማቋቋም፣ በሀገሪቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ የብሄራዊ እርቅ ጥሪ እንዲያቀርቡ ተማፅኗል፡፡
ሀገርና ዜጎች ከዚህ ቀደም እንዲህ ዓይነት ጭንቀት ውስጥ የገቡበት አጋጣሚ አለመከሰቱን የጠቆመው ማህበሩ፤ የሃይማኖት አባቶች በሀገሪቱ የሚታየው በዘር፣ በጎሣ፣ በሃይማኖትና በቀዬ የመከፋፈል አባዜ እስራትና ስደት እንዲሁም፣ ግጭትና ጦርነት መፍትሔ ይበጅለት ዘንድ እንዲተጉ ጠይቋል፡፡ በሃይማኖት አባቶች መካከል ያለው ግጭትም እልባት እንዲያገኝ ማህበሩ ተማፅኗል፡፡
ኢትዮጵያ አንፃራዊ ሰላም ሰፍኖባት መቆየቷ ባይካድም ያልተቋረጠ ግጭት እያስተናገደች ባለበት በአሁኑ ሰዓት “ፍፁም ሰላም የሰፈነባት አገር ናት” በሚል ከእውነታው መሸሽ ተገቢ አይደለም ያለው ማኅበሩ፤ “በሀገሪቱ የበቀል እርምጃ እየሰፋና እየከፋ በመምጣቱ ምክንያት ማብቂያ ወደሌለው የጥፋት ጎዳና እያመራን እንገኛለን” ብሏል፡፡
“አስከፊ የእርስ በእርስ ግጭትና ህዝባዊ አመፅ እንደሚመጣ አስቀድመን ስጋታችንን ተናግረን ነበር” ያለው ማህበሩ፤ ሆኖም ለእርቀ ሰላም ስንማፀን “በሀገሪቱ ፍፁም ሰላም ሰፍኗል” በሚል ሰሚ ጆሮ ሳናገኝ ቀርተናል ብሏል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት በመተባበር ሀገሪቱ አሁን ከገባችበት አስጊ ሁኔታ ትወጣ ዘንድ እንዲፀልዩና የሀገር ሽማግሌዎች ሸንጎ ለማቋቋም ለሚደረገው ጥረትም እገዛ እንዲያደርጉ ማኅበሩ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡