ጋምቤላ – የፌደራሊዝሙ ክሽፈት ማሳያ?

የጋምቤላን ጉዳይም ስንመለከት አብዛኞቹ ችግሮች የፌደራል መንግስቱ በጋምቤላ ሊጭነው ከፈለገው የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ የዘውግ ፌደራሊዝም ተነስተው፤ ኢሕአዴግ ለጋምቤላ በተለያዩ ጊዜያት የራሱን ፓርቲና የራሱን ግለሰቦች ሲሾም – ሲሽር የነበረበት ሂደት ጋር የሚያያዙ ናቸው፡፡ የጋምቤላ ልሒቃንም ‹‹የፌደራል መንግስቱ እንደፈለገ ኢ-ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ጣልቃ እየገባ ስለሚያውክ ነው የጋምቤላ አበሳ የበዛው፡፡ ክልሉን በዘውግ ደረጃ ከሶስት ከፍሎ፣ የጋምቤላን መሬት ለውጭ ባለሃብቶች እንደፈለገ እያከራየ፣ የፌደራል መንግስቱ ፖሊስና ወታደሮች በፈለጉት ጊዜ እየገቡና የፈለጉትን እየፈፀሙ፣ የፈለገውን ሰውና ፓርቲ ለክልሉ ከማዕከል እየሾመ ጋምቤላ ሰላም እንድትሆንና እድገት እንዲመጣ መመኝት ድካም ነው› በማለት በተለያየ ጊዜ ሃሳባቸውን ያቀርባሉ፡፡ እንዲያውም የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ሊያጣጥም የሚገባውን የአንድነትና የተገንጣይ ሃይሎችን ፍላጎት ከመመለስ ይልቅ አዳዲስ ተገንጣይ ሃይሎች (secessionist movements) በማፍራት ዛሬ ጋምቤላን ከፌደሬሽኑ መገንጠልን እንደ ዓላማ በፕሮግራማቸው ይዘው የተነሱ ሃይሎችን ማየት ጀምረናል