እየተሞዳሞዱ ሥራ በሚያንቀሳቅሱበት መልካም አስተዳደርን መመኘት የዋህነት ነው፡፡

ረዥም ጉዞ የሚጠብቀን መንገደኞች መተማመን ይገባናል፡፡ በአንድ ልብ የማይጓዙ መንገደኞች አገር አይገነቡም፡፡ ይልቁንም ቶሎ የመፈራረስ፣ እርስ በርስ የመጠራጠር፣ አንዱ አንዱን ለመጣል የመጣር፣ የመተነኳኮስና የመካካድ ባህሪ ያነግሳሉ፡፡ ተቋማዊ አደረጃጀታቸውን ጥያቄ ላይ የሚጥለው ይህን ዓይነት ባህሪ ሲኖር ነው፡፡ ቡድናዊነትና ወገናዊነት ከበዛ መንገዶች እንቅፋት ይበዛባቸዋል፡፡ ይህ በፈንታው አገሬውን ይበድላል፡፡ መልካም አስተዳደርን ለማምጣት አስተዳዳሪዎቹ መልካም መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ መልካምነት በድንገት የሚከሰት ነገር አይደለም፡፡
የልብ ንፅህናን ይፈልጋል፡፡ የእጅ ንፅህናንም ይፈልጋል፡፡ ብስለትን ይፈልጋል፡፡ የሙሰኞች ፀር መሆንን ይጠይቃል፡፡ ከስህተት ተምሮ በየጊዜው ራስን ማሻሻልን ይጠይቃል፡፡ ባለጉዳይን ማክበርን ይጠይቃል፡፡ ምዝበራን መከላከልን ይጠይቃል፡፡ ፍትሐዊነትን ይጠይቃል፡፡ እነዚህ ባህርያት ሂደታዊ ናቸው፡፡ እያደር ራስን በመለወጥ የሚመጡ ናቸው፡፡ አብዛኛውን የለውጥ ጉዞ አዲስ አበባ ላይ ማየት የዋና ከተማችን እምብርትነትና ከተሜነት (ሜትሮፖሊታን መሆን) አመላካች ነው፡፡ ብዙ ጥፋቶችም ልማቶችም የሚታዩት ዋና ከተማ ላይ መሆኑ ቁልፍ ቁልፍ ተቋማትም፣ ሹማንንትም እዚችው ከተማ ላይ መከማቸታቸውን ይነግረናል፡፡ ከየክልሉ ወደ ዋና ከተማይቱ የሚፈልሰው ህዝብ፣ የነዋሪውን ህዝብ ቁጥር መጨመሩ ብቻ ሳይሆን ባለጉዳዩን ያበረክተዋል፡፡ ባለጉዳዩ የመሬት ጉዳይ አለው፡፡
የመኖሪያ ቤት ጉዳይ አለው፡፡ የፍትህ ጉዳይ አለው፡፡ የከፋ የኢኮኖሚ ጉዳይ አለው፡፡ ይህንን ጉዳይ የሚፈታለት፣ የሚያስተናግድለት መልካም አስተዳደር ይሻል፡፡፡ በንፁህ መሰረት ላይ የተቋቋሙ መሥሪያ ቤቶች ከሌሉ፣ ባለጉዳይ አስፈፃሚ ጋር እየተሞዳሞዱ ሥራ በሚያንቀሳቅሱበት ከተማ፣ መልካም አስተዳደርን መመኘት ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ብርቱ ቁጥጥርና ብርቱ እርምጃን ይጠይቃል፡፡ እርምጃው እውነተኛ እርምጃ እንዲሆን የተሿሚዎች እከክልኝ ልከክልህ ሰንኮፍ መነቀል አለበት፡፡ ዘረፋና ምዝበራ መቆም አለበት፡፡ ከቢሮ ውጪ የሚደረጉ ውሎችና ድርድሮች መወገድ አለባቸው፡፡ ይህ ትግል ከባድ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል፡፡ተግባሩ ላይ ሳይሳተፉ ወይም ተግባሩን እያደናቀፉ፣ የአደባባይ ስብሰባ ላይ አንደበት ቢያሳምሩና ቢያስጨበጭቡ “ለጌሾው ወቀጣ ማንም ሰው አልመጣ የመጠጡ ጊዜ ከየጎሬው ወጣ!” እንደሚባለው ነው እሚሆነው፡፡ ተግባሪ ሳይኖር፣ ስለመልካም አስተዳደር ዘማሪው በዛ እንደማለት ነው፡፡ ተግባሪ አመራር ይኖር ዘንድ ውስጡ መፈተሽ ይኖርበታል!

Addis Admass