ከኤፍል ታወር የገዘፈች፣ የፓሪስ የፍቅር ሃውልት – ኤልሳ!… Ante-ነህ

ከኤፍል ታወር የገዘፈች፣ የፓሪስ የፍቅር ሃውልት – ኤልሳ!…
.
እሷ ለልጇ የተተኮሰን የአሸባሪ ጥይት፣ በደረቷ የተቀበለች እናት ናት!

(በሰሞኑ የሽብር ጥቃት የተከሰተ እውነተኛ ታሪክ)
.
.

ኤልሳ ዴልፕላስ ሙዚቃ ትወዳለች፡፡
ስለምትወድም ነው፣ ያለፈችዋን አርብ ከብቸኛ ልጇ ከሉዊስ እና ከእናቷ ፓትሪሺያ ጋር የሙዚቃ ኮንሰርት በማየት ለማሳለፍ ያቀደችው፡፡
.

አርብ ደረሰች…

የ35 አመቷ ቺሊያዊት ኤልሳ ዴልፕላስ፣ እንደ ነፍሷ የምትወደውን ብቸኛ ልጇን፣ የ5 አመቱን ብላቴና ሉዊስን እና እናቷን ፓትሪሺያ ሳን ማርቲንን ይዛ፣ ፓሪስ ውስጥ ወደሚገኘው ስመጥሩ ባታክላን ቲያትር ቤት አቀናች፡፡

“ኢግልስ ኦፍ ዴዝ ሜታል” የተሰኘው የሙዚቃ ኮንሰርት ተጀምሯል፡፡

ካፒቴን አሜሪካኖ የተባለው የሮክ የሙዚቃ ቡድን አባላት፣ ጊታራቸውን እያስጓሩ መድረኩ ላይ ነግሰዋል፡፡

ተመልካቹም ሞቅ ያለውን ሙዚቃ በፍቅር ያጣጥማል፡፡
.
.

ጥቂት ቆይቶ ግን…

አዳራሹን የሚያናውጠው የባንዱ የጊታር ድምጽ፣ እንደ ነጎድጓድ በሚያስተጋባ ድንገተኛ የተኩስ እሩምታ ተሸፈነ፡፡

ባታላንክ በሽብር ታመሰ፡፡

በሙዚቃው ምትክ ዋይታ እና እሪታ፣ ለቅሶና ሲቃ ተደመጠ፡፡

ሙዚቀኛውም፣ ተመልካቹም፣ ሁሉም ከመጣበት ድንገተኛ መዓት ራሱን ለማዳን፣ ደመነፍሱ በመራው አቅጣጫ ተራወጠ፡፡
.

እዚህ መሃል…
ኤልሳ ዴልፕላስ አለች…
ከራሷ አስበልጣ የምትወደውን፣ አንድ ለእናቱ ልጇን ሉዊስን እቅፍ አድርጋ ይዛ፣ በፍርሃት እየተንቀጠቀጠች አለች፡፡

ሉዊስ ከእናቱ እቅፍ አምልጦ፣ ሮጦ ከአዳራሹ ሊወጣ ሞከረ፡፡

እናትዬው እየጮኸች ተከተለችው፡፡
.

በዚህ ሁሉ መሃል ብዙ ነገር እየሆነ ነበር…

በህዝቡ ላይ የጥይት አረር የሚያርከፈክፈው ጨካኝ ሰው፣ የጠመንጃውን አፈሙዝ ወደ ተረኛው ሟች አቅጣጫ አዙሮት ነበር፡፡

የገዳዩ ዒላማ፣ የ5 አመቱ ብላቴና ሉዊስ ላይ አርፎ ነበር፡፡

ሰውዬው ያለርህራሄ ምላጩን ስቦ ነበር!

ተኩሶ ነበር!…

የሚገርመው ግን…

ደመነፍሷን ወደ ሉዊስ መሮጥ የጀመረቺው ኤልሳ ዴልፕላስ፣ ከሰውዬው ጥይት ቀድማ ልጇ ላይ ደረሰች!…

እናትዬዋ ተሳካላት!…

አሸባሪው ለልጇ የቆጠረውን ጥይት፣ እሷ በደረቷ ተቀበለችው!…

በደም አበላ ተነክራ፣ ልጇን እንዳቀፈች ወለሉ ላይ ተዘረረች፡፡
.

ሰውዬው አሁንም ይተኩሳል…
አፈሙዙን ወደ ሌላ ኢላማ ይመልሳል…

ቀጣዩ ኢላማ፣ የኤልሳ ዴልፕላስ እናት ናቸው…

አነጣጥሮ ቆጠረባቸው…

እሳቸውም እንደልጃቸው፣ ደም እያዘነቡ ወለሉ ላይ ከልጃቸው አለፍ ብለው ተዘረሩ፡፡
.
.
.
የፓሪሱን ባታክላን ቲያትር ቤት ያጥለቀለቀው ድንገተኛ የሽብር ማዕበል፣ ብዙዎችን ቀጥፎ አለፈ፡፡

89 ሰዎች ሞቱ፤ ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩም ክፉኛ ቆሰሉ፡፡

ከሞቱትና ከቆሰሉት መካከል ግን…

ብላቴናው ሉዊስ አለ…

ለሱ የታለመችን ጥይት በደረቷ የተቀበለችለትን፣ ህይወቷን የከፈለችለትን፣ ነገዋን የሰዋችለትን፣ ቀዝቅዛ የወደቀችውን የእናቱን የኤልሳ ዴልፕላስን አስከሬን አቅፎ አምርሮ እያለቀሰ፡፡
.

አሁን…

ሉዊስ ሆስፒታል ውስጥ በደህና ሁኔታ ይገኛል…

እናቱ ኤልሳም መቃብር ትውረድ እንጂ፣ ከፓሪሱ ኤፍል ታወር በላይ ከፍ ብላ የምትታይ፣ ዓለም ጽኑ ፍቅሯን እያየ የሚደመምባት፣ የእናት ፍቅር መገለጫ ህያው ሃውልት ሆና ቆማለች!
.
(ዘ ኢንዲፔንደንት ነው ትናንት የዘገበው)