‘ድርቁን ፖለቲሳይዝ አታድርጉት’ ከመባባል በፊት ቁጥር ቅነሳውን ምን አመጣው? Yohanes Molla
አቦ አታድርቁና! ስንቱን ነገር ፈትፍተን አጉርሰናችሁ እንችለዋለን?! ‘ድርቁን ፖለቲሳይዝ አታድርጉት’ ከመባባል በፊት ቁጥር ቅነሳውን ምን አመጣው? ያው ፖለቲሳይዝድ የሆነ ነገር ስለሆነ አይደል? ድርቅ (drought) የዝናብ መቅረት እንጂ የምግብ መጥፋት (famine) አይደለም። በትክክለኛ ትርጓሜው ሲታይም፥ መንግስት ሕዝብን እንዲያገለግል የሚሾም፣ አስተናባሪ እንጂ ውለታ የሚውል ወይም ቁጭ ብሎ መቀለብ የሚገባው ባለጊዜ አይደለም።
85% ገበሬ፣ ግብርና መር ኢኮኖሚ፣ ልማታዊ ዴሞክራሲ፣ ተሸላሚ ሚሊየነር ገበሬ፣ እየተባለ ሲደሰኮር፥ ዛሬም ከማሳ ወደ አፍ ነው የሚኖረው። ዛሬም ዝናብ እየተደገፍን ነው የምንኖረው። ይኸው ዛሬ የተራበው ገበሬ እና በረሀቡ የተነሳ እድገታቸውና ጤንነታቸው የሚስተጓጎል ህጻናት ልጆቹ ናቸው (ከሞት የሚተርፉት) አገግመው ሞፈርና ቀንበር ጠምደው በሬ ሊገፉ የሚታገሉት።
ደግሞ ስንቴ ተብሎ ያታከተው የከተማ ውስጥ ረሀብስ አለ አይደል? ንጹህ ነጠላ ለብሰው ለልመና ከቤት ስለሚወጡና በሰው ዐይን ሲገረፉ ስለሚውሉ እናቶች ስንቴ ተወራ? በየት/ት ገበታቸው ላይ ፍንግል ስለሚሉ ህጻናትስ ስንት ነገር ተባለ? (በራፌ ላይ አለ አይደል፥ የጎረቤት ደግነት ሲሳይ ካልሆነው በቀር እራት የማያውቅ ቤተሰብ?) እንዲህም ሆኖ ግን ዛሬም አንተማመንም። በዘመነ ኢንተርኔትና ሉላዊነትም ለመሸዋወድ እንባጠሳለን።
ደግሞ በየፓርቲውና በየሁኔታው ለድግስና ለፈንጠዝያ የሚበተነው የሕዝብ ገንዘብም አለ። ሰሞኑን አይደል የብአዴን ድግስ? የባንዲራ ቀን ከተከበረስ ብዙ ዘገየ እንዴ? ለብሔር ብሔረሰብ በዓል ዝግጅትስ ሽር ጉዱ ተጀምሮ የለ? በልማት፣ በገጽታ ግንባታና ጸረ ሽብር ስም የሚበጀተውም የትየለሌ ነው። እንዳሻቸው ኖረው ጡረታ ለሚወጡ 6 ባለስልጣናትም በነፍስ ወከፍ 25 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ መኖሪያ ቤት እየተገነቡ የመሆናቸው ወሬ የተሰማውም ባሳለፍነው ሳምንት ነው። ከግልገል እስከ ከፍተኛ ባለስልጣናት የተያዙ ከተማ የሚያህሉ ቦታዎች፣ የተገነቡ ህንጻዎችና አትራፊ ተቋማትም አሉ።
ለቀድሞው ፕሬዝዳንት አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ የመኖሪያ ቤትስ፥ የአንድ ኢንዱስትሪን የተጣራ ገቢ የሚያስንቅ ብር (በወር በ400 ሺህ) የኪራይ ወጪ ይደረግ የለ? (ብሩ መውጣቱ ካልቀረ፥ በማን አለብኝነት እና ካከራዩ ጋር የመጠቃቀም ውል ቢኖር እንጂ ግዢ ጠፍቶ ነው? ግዢ ቢፈጸም፥ ቢያንስ ደግ ቀን ሲመጣ ወደ ሕዝብ ንብረትነት ገቢ ለማድረግም ይቀል ነበር።) ስንቱን ቆጥረንና ዘርዝረን እንዘልቀዋለን?
ይህ በእንዲህ እንዳለስ፥ የረሀቡን ወሬ መደበቅና ማስተባበልን ምን አመጣው? ገና ከብቶች መሞት መጀመራቸው ሲወራ አይደል፥ ‘አርብቶ አደሩ ውሀ በጊዜ ስለማያጠጣ ነው’ የሚል አሳፋሪ ማብራሪያ የተሰጠው? የተራበውስ ‘ራቱን በጊዜ ስለማይበላ ነው’ ሊባልልኝ ነው? ድርቅ የተከሰተውስ ‘ገበሬው የዝናብ ውኀ ስለማይደቅን ነው’?
ነጻ ጋዜጠኞችን ማቀናጨር ባይኖር ኖሮ፥ ቢያንስ እንዲህ ያለ ነገር ይፈጠር ነበር? ወዲህ ‘ከእኛ ቁጥጥር ውጭ አይደለም’ ይባላል፤ ወዲያ ወደ በለጸጉት የልመና እጅ ይዘረጋል፤ አይጣረስም?