በአመራር ክህሎት እና በፋይናንስ አስተዳደር የከፍተኛ ሓላፊዎች ሥልጠና ተሰጠ
- የአቅም ግንባታ ፕሮጀክቱ፣ በአህጉረ ስብከት እና በአጥቢያ ሠራተኞች ሥልጠና ይቀጥላል
- “ለቤተ ክርስቲያን መልካምነትም ኾነ ውድቀት መሪዎች ትልቁን ድርሻን ይወስዳሉ፡፡”
/ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል/

በመንፈሳዊ አመራር እና በዘመናዊ የሙዓለ ንዋይ አስተዳደር፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን አቅም በማጎልበት ክሂሎታቸውን ለማዳበር ያስችላል የተባለ የከፍተኛ ሓላፊዎች ሥልጠና በልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ተሰጠ፡፡
በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እና በመላው አህጉረ ስብከት፤ እስከ 200 ለሚደርሱ የመምሪያ፣ የድርጅት እና የዋና ክፍል ሓላፊዎች እና ምክትል ሓላፊዎች የተሰጠው ሥልጠና፤ የዘመናዊውንና የመንፈሳዊውን አመራር ዕውቀትና ክህሎት በማስጨበጥ እንዲሁም ሌሎች ተተኪ መሪዎችን በማፍራት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ታምኖበታል፡፡
የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር አጠቃላይ ጉባኤ 34ኛ ዓመታዊ ስብሰባ መጠናቀቅ ተከትሎ፣ ከጥቅምት 12 – 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት አዳራሽ የተካሔደውን የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና በንግግር የከፈቱት የኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፤ በቤተ ክርስቲያናችን የሚታየውን የአመራር ክሂሎት ክፍተት ለመሙላት እንዲህ ያሉ ሥልጠናዎች የመሪነትን ዕውቀትና ጥበብ ከማስገኘት አንጻር ወሳኝ ድርሻ ይኖራቸዋል፤ ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ፣ በኹለንተናዊ የልማት እና የማኅበረሰብ ችግሮች ዙሪያ ከሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ጎን ለጎን ቤተ ክርስቲያን በኹሉም መስክ የተሟላ አገልግሎት እንድትሰጥ ለማድረግ የአቅም ክፍተቶችን ለይቶ ሥልጠና እንደሚሰጥ የጠቀሱት ብፁዕነታቸው፤ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለመወጣት የመሪነት ክህሎት አቅም ግንባታ ፕሮጀክት መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡
የአኹኑ ሥልጠና፣ በውሳኔ አሰጣጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ ባላቸው ከፍተኛ ሓላፊዎች ላይ ያተኮረ ቢኾንም በማናቸውም ደረጃ ለሚገኙ አመራሮች እና ሠራተኞች ከፍ ያለ ጠቀሜታ ስላለው፤ የአቅም ግንባታ ፕሮጀክቱ በአህጉረ ስብከት፣ በገዳማት እና አድባራት ሓላፊዎች እና ሠራተኞች ላይ ቀጣይነት እንደሚኖረው ብፁዕነታቸው ጠቁመዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን፣ ሀገርን በመምራት ታሪክ ውስጥ በጎ ተጽዕኖ በመፍጠር ጉልሕ ሚና እንደነበራት ያስታወሱት ብፁዕነታቸው፤ በሃይማኖት መሪዎቿ ጥበብ እና የመንፈስ ብርታት፣ ጠንካራ አገልግሎት እና ጸሎት የሚገጥሟትን ፈተናዎች አልፋ እምነቷንና ታሪኳን ለትውልዱ እና ለሀገር እንዳበረከተች፤ የቀደምት አባቶቻችን የአመራር ስልት መንፈሳዊም ዓለማዊም ይዘቶች ያሉት መኾኑ ስለ አስተዳደር ይሰጡት የነበረውን ትኩረት እንደሚያሳይ አስረድተዋል፡፡ ይኹን እንጂ እኒያ ጥንታዊ የአስተዳደር ስልቶች በዘመናዊ ሕገጋት እየተሻሩ፣ አንዳንዶቹም ትኩረት የሚሰጣቸው በመጥፋቱ ለአስተዳደር መዘበራረቆች ምክንያት ኾኗል፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን፣ በዘመናት ውስጥ አልፋ የመጣችባቸው ጥንካሬዎቿ ዛሬ በፈታኝ ኹኔታ ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት ብፁዕነታቸው፤ በዚኽ ረገድ መንፈሳዊ መሪዎች አዎንታዊውን ብቻ ሳይኾን አሉታዊውን ሚና በመጫወት በድርሻቸው ተጠያቂ እንደኾኑ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
ፈጣንና ውስብስብ ለውጦች እጅግ በበዙበትና የቤተ ክርስቲያን ፈተናዎች ባዩለበት በአኹኑ ዘመን የሚገኙትን ምእመናንና ሀብቶችዋን ለማስተዳደርና የታሪክ ሒደቷን በታላቅነት ለማስቀጠል፣ ከመንፈሳዊ ሕይወት እና ዕውቀት ባልተናነሰ በመሪነት ላይ የሚሰጡ ሥልጠናዎች ለአንድ መሪ እንደሚያስፈልጉ የተለያዩ ጥናቶች እና የአኃት አብያተ ክርስቲያናት ተሞክሮዎች እንደሚያመላክቱ ብፁዕነታቸው በንግግራቸው አስገንዝበዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ለሥልጠናው ተሳታፊዎች እንዳስረዱት፣ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጊዜው የሚጠይቀውን ዘመኑን የዋጀ አመራር ለማስፈን፣ እውነተኛ የግምገማ ሥርዐት በማካሔድ ሥራችንንና የአሠራር ሒደታችንን እንደ ተቋም መፈተሽ ያስፈልገናል፡፡ የግምገማ ሥርዐቱ ቤተ ክርስቲያንን ማእከል ማድረግ የሚገባው ሲኾን ሦስት እይታዎች ይኖሩታል፡፡
በመጀመሪያ፣ የሥራ አፈጻጸሙ በዕቅዱ እና በክንውኑ ይገመገማል፡፡ ኹለተኛው፣ በውጤታማነቱና በሀብት አጠቃቀሙ ላይ ተመሥርቶ ምላሽ ይሰጣል፤ ምክክር ይደረጋል፡፡ በሦስተኛው እይታ ደግሞ በቤተ ክርስቲያኗ ሥራ አመራር ላይ የተፈጠሩትን ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች የሚፈትሽ ሲኾን በአብዛኛው ግን ድክመቶችን የሚመለከት ነው፡፡ በዚኽም ክፍተቶች የሚለዩበት በመኾኑ በአዎንታዊ መልኩ የአቅም ግንባታ ተግባር ለመፈጸም መሠረት ይጥላል፡፡
በቤተ ክርስቲያናችን ለሚታዩት የመልካም አስተዳደር እና የሥነ ምግባር ችግሮች በዋናነት ሊጠቀሱ የሚችሉት የአቅም ውሱንነት እና የአመራር ክህሎት ማነስ እንደኾነ የዘረዘሩት ብፁዕነታቸው፤ ለቤተ ክርስቲያን መልካምነትም ኾነ ውድቀት መሪዎች ትልቁን ድርሻ የሚወስዱ በመኾኑ በአመራር ከሂሎት እና ጥበብ ላይ የሚደረግ ማናቸውም እንቅስቃሴ በተገቢው መንገድ እና ጥንቃቄ መመራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አመራር ሰጭ የኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ፤ የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎች የሚያስፈጽሙ አካላትን የመንፈሳዊ አመራር ብቃት ለማሳደግ እና የአመራር ክህሎታቸውን ለማጎልበት ድጋፍ የመስጠት ዓላማ ያለው ፕሮጀክቱ፤ በኹሉም ዘርፍ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዐቱን በመፈተሽ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ለማስፈን፤ የገንዘብ እና ንብረት ብክነትን ለመከላከል እንደሚያግዝ፤ በጎ እና ዘላቂ ተጽዕኖ በመፍጠር ሌሎች ተተኪ መሪዎችን ለማፍራት ትልቅ ሚና ለመጫወት እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡
በመሪነት ክህሎት ላይ በማተኮር በመስኩ ባለሞያዎች ለሦስት ቀናት የተሰጠው የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ዙር የአቅም ግንባታ ሥልጠና÷ መንፈሳዊ አመራር፣ ዘመናዊ የሙዓለ ንዋይ አስተዳደር እና ማኅበራዊ አስተዋፅኦ የሚሉት ሦስት ዐበይት አርእስተ ጉዳዮችን እንደያዘ በብፁዕነታቸው ንግግር ተመልክቷል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን፤ ከተቋቋመበት ከታኅሣሥ ወር 1964 ዓ.ም. ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ በተሰጠው ሥልጣንና ተግባር መሠረት፣ ከለጋሽ ድርጅቶች በሚገኝ ርዳታ በሚያዘጋጃቸው የድርጊት መርሐ ግብሮች ሥራዎቹን ከዳር ለማድረስ ይንቀሳቀሳል፡፡
በአደረጃጀቱ የቤተ ክርስቲያኗን መዋቅር ተከትሎ በሃይማኖታዊ ይኹን በማኅበራዊ ዘርፎች ከአራት ዐሥርት ዓመታት በላይ ሲያከናውናቸው በቆያቸው ተግባራት፤ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከነበረባቸው የኑሮ ችግር እንዲላቀቁ የበኩሉን ድርሻ አበርክቷል፤ እያበረከተም ይገኛል፡፡ በአኹኑ ወቅት ኮሚሽኑ በተቀናጀ የገጠር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት፤ በንጹሕ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት መርሐ ግብር፤ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠርያ ፕሮግራም፤ የስደተኞች እና ተመላሾች ጉዳይ ፕሮግራም ያሉት ሲኾን በመላ አገሪቱ 23 ዋና ዋና ፕሮጀክቶችን ቀርጾ በ468 ሠራተኞች በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡