የወታደሮቻችን ነገር (ዳንኤል ክብረት)

የመቅደላው ጀግና ዐፄ ቴዎድሮስ በመጨረሻዋ ሰዓት ለጄኔራል ናፒየሪ በጻፉት ደብዳቤ አበክረው የጠየቁት ነገር ከሁለት ቀናት በፊት በተደረገው ውጊያ የወደቀውን የወዳጃቸውንና የጦር መሪያቸውን የፊታውራሪ ገብርዬን አስከሬን ለመቅበር እንዲፈቀድላቸው ነበር፡፡ ‹‹ፊታውራ ገብርዬን የኔን ወዳጅ ሳላነሣው ያደርኩ ከሞትኩኝ ሁሉንም አብረው ይቅበሩኝ ብየ ነበር፡፡ ቁሜ ከዋልኩ ግን ልቅበረው ይፍቀዱልኝ›› ይላል ደብዳቤው፡፡ ለሀገሩና ለወገኑ በክብር የተሠዋ አስከሬኑም የክብር ዕረፍት ይሻዋልና፡፡
በኢትዮጵያ የቅርብ ዘመን ታሪክ የተሠዉ ወታደሮችን በክብር የመዘከር፣ በክብር የመቀበልና በክብር የመቅበር ሥነ ሥርዓት አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ በኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት የተሠዉ ስንት ወታደሮች ናቸው? የተሠዉትስ ወታደሮች መርዶ እንዴት ተነገረ? የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውስ እንዴት ተከናወነ? ሚዲያውስ ለዚያ ምን ዓይነት ሽፋን ሰጠው? የሁል ጊዜ ጥያቄዬ ነው፡፡ እኔ ሳልሰማና ሳላውቅ ተከናውኖ ካልሆነ በቀር፡፡ ለምንስ አስከሬናቸው በወታደራዊ ሥነ ሥርዓት ታጅቦ፣ ሰንደቅ ዓላማ ለብሶ፣ ብሔራዊ መዝሙር እየተዘመረ፣ ሕዝቡ ወደ አደባባይ በነቂስ ወጥቶ አላከበርናቸውም? እያልኩ እጠይቃለሁ፡፡
የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር በአፍሪካ ልዩ ልዩ ሥፍራዎች ዘምቷል፡፡ ሲዘምትም በክብር እንደተሸኘ በሚዲያዎቻችን አይተናል፡፡ እነዚህ ዘማቾች ሁሉም በሰላም ነው የተመለሱት? የተሠዋ ካለ ለምን ይፋዊ በሆነ ሀገራዊ ሥነ ሥርዓት አስከሬኑን ተቀብለን አልቀበርነውም? ፖለቲካው ተፈርቶ ከሆነ ለግዳጅ የተሠማራ ወታደር ወይ በድል መመለስ፣ ወይ መማረክ፣ ወይ መቁሰል አለያም መሠዋት እንደሚያጋጥመው እንኳን እኛ ታሪካችን በጦርነት የተሞላው ቀርቶ ሌሎችም ያውቁታል፡፡
ታድያ የሀገሬ ወታደሮች አልተሠዉም፣ አልቆሰሉም፣ አልተማረኩም? የሄዱት ሁሉ ሰላም ናቸው? ከሆኑ መልካም፡፡ ግን ቦታውም የነ አልሸባብ ቦታ፣ ሁኔታውም ጦርነት፣ ሰዎቹም ወታደሮች ናቸውና ቢያንስ መሞትና መቁሰል አይቀርም፡፡ የአሜሪካና የአውሮፓ ሚዲያዎች በአፍጋኒስታን፣ በኢራቅና በሶርያ ጦርነት የተሠዉትንና የቆሰሉትን ማንነት እንደሚናገሩት፣ በክብርም ሲቀበሩ እንደሚያሳዩት፣ የኛዎቹ የተሠዉት በክብር ሲቀበሩ፣ የቆሰሉት በክብር ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ለምን እንደ ሕዝብ አናያቸውም? ለመሆኑስ በክብር የተሠዉ የኢትዮጵያ ወታደሮች መቃብር የት ነው?
ወደኋላም ተመልሰን ከአድዋ ጦርነት በኋላ የሆነውን ስናስታውስ በእንዳ ኢየሱስ ያለው የአባቶቻችንን መቃብርና ከዚያ እልፍ ብሎ የሚገኘውን የጣልያኖች መቃብር መመልከቱ ብቻ በቂ ነው፡፡ በእንዳ ኢየሱስ የሚገኘው የአድዋ ዘማቾች አባቶቻችን መቃብር ለመሥዋዕትነታቸው የማይመጥን ነው፡፡ አልፎ አልፎም ፈርሶ እናየዋለን፡፡ የጣልያኖቹ መቃብር ግን በክብር ታጥሯል፡፡ ጠባቂም ተመድቦለታል፡፡ መቃብሩንም ለማየት የጣልያን ኢምባሲ ፈቃድ ይጠይቃል፡፡
በአሥራ ሰባቱ የደርግ ዓመታት የዘመቱት ወታደሮች ኢትዮጵያ የመለመለቻቸው፣ ያሠለጠነቻቸውና ያዘመተቻቸው ነበሩ፡፡ ምንም ጦርነቱ የእርስ በርስ ጦርነት ቢሆንም፡፡ የተሠዉት አብዛኞቹ ወታደሮች ለቤተሰብ መርዶ አልተነገረም፡፡ በተለይ ኤርትራ በረሃ የቀሩት መጨረሻቸው ምን እንደሆነ አልታወቀም፡፡ ጦሩ ሲበተን ወደ ቤተሰባቸው መምጣት የቻሉት ቁርጣቸው ታወቀ፤ ከዚያ ውጭ ያሉት ግን አሁንም ለቤተሰብና ለሀገር ጥያቄ እንደሆኑ ናቸው፡፡


