የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የመክፈቻ ጸሎት ተካሔደ፤ “የአዲስ አበባን ጉዳይ በጽሞና መፈተሽ፣ መነጋገር፣ ማረም አለብን” /ብፁዕ አቡነ ገብርኤል/
ሲኖዶስ ማለት፡-
- ሲኖዶስ፣ ቃሉም ሥራውም የምሥራቃውያን ነው
- ቃሉ ግሪክኛ ኾኖ የአንድነት ስብሰባ ማለት ነው
- የእኛ ቤተ ክርስቲያን ከምሥራቃውያን አንዷ ነች
- ቤተ ክርስቲያናችን ሐዋርያዊትና ሲኖዶሳዊት ነች
የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ፡-
- የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ እንደ ማንኛውም ጉባኤ አይደለም፤ የቤተ ክርስቲያን የበላይ መሪዎች ስብሰባ ነው፤ በመንፈስ ቅዱስ ስለሚመራ ቅዱስ ሲኖዶስ ተብሎ ነው የሚጠራው፤
- ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል እንደተባለው፤ መኑ ይብልዎ ሰብእ ለቅዱስ ሲኖዶስ፤ ካህናት እና ምእመናን ቅዱስ ሲኖዶስን ምን እያሉት ነው፤ እያመሰገኑን ነው? እያሙን ነው?
- ሰዎች የሚሉን ብዙ ነገር ነው፤ በቅዱስ ፓትርያርኩ ሊቀ መንበርነት፣ በጽሞና፣ በሰከነ ኹኔታ በውይይት መፍትሔ መፈለግ፣ ማጽዳት አለብን፤
- መልካም ነገርም ክፉ ነገርም በአዲስ አበባ ይከሠታል ይባላልና መፈተሸ፣ መነጋገር፣ ማረም አለብን፤ መፈተሽ የሚችል ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፤ ፓትርያርኩ ሊቀ መንበር ስለሆኑ የእርሳቸው ብቻ ሳይሆን የኹሉም ድርሻ ነው፡፡ /ብፁዕ አቡነ ገብርኤል/

ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በበላይነት የሚመራው እና የሚጠብቀው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የመጀመሪያውን ዓመታዊ የምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባውን ከነገ ጀምሮ ያካሒዳል፤ የጉባኤው የመክፈቻ ጸሎት፣ ዛሬ ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም. ሠርክ፣ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ተከናውኗል፡፡
በመክፈቻ ጸሎት ሥነ ሥርዐቱ፣ የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ገብርኤል እንደተናገሩት÷ በዓለም በተጋድሎ ላይ ያለችው ቤተ ክርስቲያን በአኹኑ ወቅት የደረሱባት ችግሮች እያደር ሳይባባሱ፤ ቅዱስ ሲኖዶስ በፍቅር፣ በውይይት እና በሰላም ሊያስተካክላቸው የሚገቡ ነገሮች መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡