ጠቅላይ ቤተ ክህነት: ዘመናዊውን የኹለትዮሽ የሒሳብ ሥርዐት ተግባራዊ አደረገ፤ “ቤተ ክርስቲያን ስትተችበት የነበረውን የነጠላ ሒሳብ አሠራር አስቀርቷል” /ጽ/ቤቱ/
- የሥርዐት ለውጡ÷ ጽ/ቤቱ፣ ከሐምሌ 2002 – ሰኔ 2005 ዓ.ም. ያለውን የሒሳብ አሠራሩን በውጭ ኦዲተሮች ካስመረመረ በኋላ የተሰጠውን አስተያየት ተከትሎ የተካሔደ ነው
- የፋይናንስ ፖሊሲው እና ማኑዋሉ፣ የቤተ ክርስቲያንን የምጣኔ ሀብት እና የሙዓለ ንዋይ አስተዳደር መመሪያዎች በሚያወጣው በቅዱስ ሲኖዶስ ተመርምሮ የተወሰነ ነው
- ከኹለትዮሽ የአመዘጋገብ ሥርዐት ጋር ጽ/ቤቱ በተከተለው ማእከላዊ የበጀት አሠራር (budget centralization)፤ ወጪ ቆጣቢ፣ ውጤታማ እና ቀልጣፋ ሥራ መከናወኑ ተገልጧል
- ትግበራው÷ የሠራተኞችን ሞያዊ ብቃት ከማሻሻሉም በላይ በሕግ ተቀባይነት ያለውና ለቁጥጥር አመቺ የኾነ የሒሳብ አሠራር ለመዘርጋት እንዳስቻለ ተጠቁሟል
- ከትግበራው በፊት፣ የጽ/ቤቱ ሒሳብ በውጭ ኦዲተር ሲመረመር፣ “የሒሳብ አያያዝ ሥርዐት ያልተዘረጋለትና በተለመደው የሒሳብ መርሕ መሠረት ያልተሠራ በመኾኑ ሞያዊ አስተያየት ለመስጠት አይቻልም”(disclaimer) ሲባልበት ቆይቷል
- ነገ የሚጀመረው የሰበካ አስተዳደር አጠቃላይ ጉባኤ 34ኛ ዓመታዊ ስብሰባ፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ዘመናዊ አሠራር በኹሉም አህጉረ ስብከት እንዲተገበር የጋራ አቋም እንደሚያወጣ ይጠበቃል
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት፡–
- “ዘመናዊ ማኑዋል አዘጋጅቼ የሒሳብ ሠራተኞችን አሠልጥኛለኹ” ቢልም፣ በቅድሚያ ማኑዋሉ የተመሠረተበትን የፋይናንስ ፖሊሲ ለጠቅ/ቤተ ክህነቱ አቅርቦ በቋሚ ሲኖዶሱ አላጸደቀም
- “ዘመናዊ ሞዴላሞዴሎች ያስፈልጉኛል” በሚል ደረሰኞች እና ቅጾች እንዲታተሙለት ለቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ ያቀረበበት አካሔድም፣ መዋቅሩን የጣሰና ጠቅ/ቤተ ክህነቱ የማያውቀው ነው
- ሀ/ስብከቱ ለአንድ ጊዜ ብቻ እንዲያሳትም ተወስኖ ቢፈቀድለትም፤ የሰነዶቹን ዐይነት፣ ጥራትና ብዛት ለጠቅ/ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት ባለማሳወቁ ቁጥጥሩንና ክትትሉን አዳጋች አድርጎታል
- የሥልጠናው ተሳታፊዎች፣ “ምን እንደሚያወራ ለራሱም የገባው አይመስለንም” በሚል የአሠልጣኙን የሒሳብና በጀት ዋና ሓላፊ የኤልያስ ተጫነን ብቃት ክፉኛ ተችተዋል
- ትችቱ፣ የሰው ኃይል ዝግጅቱን አጠራጣሪ አድርጎታል፤ ከተጨባጭ ርምጃ ይልቅ የየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ዲስኩር የበዛበት “የለውጥ ሒደት”ም ከተጠያቂነት የማምለጫ እና በሥልጣን የመሰንበቻ ከንቱ ፕሮፓጋንዳ እንደኾነ አሳይቷል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን፡-
- ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት የሒሳብና በጀት መምሪያ እንዲሁም ከቁጥጥር አገልግሎቱ ጋር በመግባባት የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ ተግባራዊ ማድረጉ ተገልጧል
- “Modified Cash Base” እና “Accrual Base” የተሰኙ የኹለትዮሽ የሒሳብ አሠራር መርሖዎችን የሚከተለው ማኅበሩ፣ ካለፈው በጀት ዓመት አንሥቶ በጽ/ቤቱ ሞዴላሞዴሎች እየተጠቀመ ነው
- ከዋናው ማእከል እስከ ማእከላት ድረስ የሚጠቀምባቸው የገቢ እና ወጪ ሞዴላሞዴሎች፣ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ዕውቅና ያላቸውና ለቁጥጥርም አመቺ ኾነው እንዲታተሙ ተደርጓል
- “ማኅበሩ በ2007 ዓ.ም. የቅ/ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት በትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት በታተመ የገቢ መሰብሰቢያ ደረሰኝ በመጠቀም ላይ ነው፤ በበጀት ዓመቱ ከአባላት ወርኃዊ አስተዋፅኦ፣ ከቅዱሳት መካናት ልማት፣ ከማኅበራዊ አገልግሎትና ከስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራሞች የተገኘ ገቢ ብር 21,914,349.31፤ ለልማት አገልግሎትና ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት የወጣ ወጪ ብር 21,726,982.17 ኾኖ ከወጪ ቀሪ ብር 187,367.14 በልዩነት አስመዝግቧል፡፡” /የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሪፖርት/
(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ 16 ቁጥር 822፤ ቅዳሜ ጥቅምት 6 ቀን 2008 ዓ.ም.)
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ማእከል የኾነው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ የኹለትዮሽ የሒሳብ አመዘጋገብ ሥርዐትን በመከተል አሠራሩን ዘመናዊ ማድረጉ ተገለጸ፡፡
ቤተ ክርስቲያን፣ ዘመናዊውን የኹለትዮሽ የሒሳብ አሠራር ሥርዐት/Double entry accounting system/ እንድትከተል የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት በባለሞያዎች ያካሔደውን የፋይናንስ ፖሊሲ እና ማኑዋል ጥናት በቋሚ ሲኖዶስ በማስወሰን ባሳለፍነው የ2007 ዓ.ም. በጀት ዓመት ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩ ታውቋል፡፡ በዚኽም “ቤተ ክርስቲያኒቱ ዘወትር ስትወቀስበትና ስትተችበት የነበረውን፣ ለቁጥጥር የማያመቸውንና በሕግም ተቀባይነት የሌለውን የነጠላ ሒሳብ አሠራር” ጽ/ቤቱ ማስቀረቱ ተገልጧል፡፡
በፖሊሲው ላይ የተመሠረቱ እና ከማኑዋሉ ጋር የሚስማሙ የሒሳብ ሰነዶች እና ቅጻቅጾች ተዘጋጅተው ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን የጽ/ቤቱ የሒሳብና በጀት መመሪያ ሠራተኞችም ለትግበራው የሚያስፈልጉ ልዩ ልዩ ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡
የተቋሙን አጠቃላይ ሀብት እና ዕዳ በማወቅ የፋይናንስ እና የንብረት አጠቃላይ አስተዳደሩንና እንቅስቃሴውን ለቁጥጥር ግልጽ ለማድረግ፤ ተፈላጊውን መረጃ በሪፖርት በማውጣት እና በመተንተን ተገቢ ውሳኔ ለመስጠት ምቹ የሆነውን የሁለትዮሽ አመዘጋገብ ተግባራዊነት ተከትሎ፣ ጽ/ቤቱ ማእከላዊ የበጀት አሠራር በመከተሉ ወጪ ቆጣቢ እና ውጤታማ ሥራ ለማከናወን መቻሉ ተገልጧል፡፡
ከ16 የጽ/ቤቱ መምሪያዎች እና ድርጅቶች፣ በጀታቸውን በራሳቸው እያንቀሳቀሱ ሲሠሩ የነበሩ የሰባት መምሪያዎች እና ድርጅቶች የገቢ እና ወጪ ሒሳብ፣ በአንድ ቋት ተጠቃልሎ በኹለትዮሽ አመዘጋገብ ዘዴ በመሠራቱ ከሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ የተሠራው ሒሳብ ተመርምሮ ተዘግቷል፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ በየጊዜው በሚታየው የዋጋ ግሽበት ተጎጂ ኾና የቆየች ሲኾን በሕጋዊ እና አስተማማኝ የግዢ ሥርዐት ዓመታዊ ግዥ በመፈጸም ዕቃዎች በመጋዘን እንዲቀመጡ በማድረግ ከጉዳቱ ለመዳን መቻሉ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞች የደመወዝ ክፍያ፣ የቤቶች እና ሕንጻዎች ኪራይ አሰባሰብ በባንክ በኩል በማስፈጸም ሒደቱን ቀልጣፋ በማድረግ ውጤታማ ሥራ መሠራቱ ተመልክቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገር ውስጥ እና በውጭ ለተቋቋሙት 50 አህጉረ ስብከት የበላይ ሓላፊ እና አመራር ሰጪ የኾነው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋነኛ የፋይናንስ ምንጭ፣ ቤተ ክርስቲያን በየአጥቢያው ባቋቋመቻቸው ሰበካ ጉባኤያት ከምእመናንና ከበጎ አድራጊዎች በአስተዋፅኦ ክፍያ፣ በስጦታ፣ በስእለት እና በሙዳየ ምጽዋት የሚሰበሰበው የገንዘብ ፈሰስ ነው፡፡
ከ34 ዓመታት በፊት በሳንቲም ደረጃ የተጀመረውና ከየአህጉረ ስብከቱ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ ፈሰስ የሚደረገው የ35 በመቶ(ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የ65 በመቶ) የሰበካ ጉባኤያት ገቢ፣ በበጀት ዓመቱ ከብር 125 ሚሊዮን በላይ/125,785,279.95/ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን ካለፈው ዓመትም ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው ተመዝግቧል፡፡ ከአጠቃላይ ገቢው ውስጥ ከብር አምስት ሚሊዮን በላይ/5,381,655.29/ በልማት ገቢ የተደረገ ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ ከ66,668,379.25 ገቢ ማድረጉ የተገለጸው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት 16,432,074.68 ብልጫ ማስመዝገቡ ተጠቅሷል፡፡
የገቢዋ ዕድገት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ልማታዊ አገልግሎቶቿን በራስዋ አቅም ለማከናወን የሚያስችላት ሲኾን ለዚኽም ጠቅላይ ጽ/ቤቱ መከተል የጀመረው ዘመናዊው የኹለትዮሽ የሒሳብ አያያዝ እንዲኹም የበጀት ማእከላዊነት በተዋረድ በኹሉም አህጉረ ስብከት እና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ተግባራዊ እንዲኾን ሲጠየቅ ቆይቷል፡፡
የቤተ ክርስቲያንን የገንዘብ አያያዝ እና አጠቃቀም ሥርዐት÷ ዘመናዊ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መልኩ ማደራጀት ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሦስት ዐበይት ሥር ነቀል የለውጥ ርምጃዎች አንዱ ሲኾን በየዓመቱ በሚካሔደው የሰበካ አስተዳደር አጠቃላይ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባዎችም፤ የእግዚአብሔር ገንዘብ በተገቢው የሒሳብ አያያዝ ሥርዐት በጥንቃቄ ተመዝግቦ ለሚገባው አገልግሎት እና ልማት እንዲውል፤ ቤተ ክርስቲያን በራሷ ምእመናንና ልማት ላይ የተመሠረተ ሉዓላዊ ክብሯ እንዲጠበቅ በጋራ አቋሞችና ውሳኔዎች ሲጠየቅ ቆይቷል፡፡
በቀጣዩ ሰኞ በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ የሚጀመረውና ከ800 ያላነሱ የመላው አህጉረ ስብከት ልኡካን የሚሳተፉበት 34ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባም፤ ትግበራው እና ተሞክሮው በኹሉም አህጉረ ስብከት እና አጥቢያዎች ተስፋፍቶ ቤተ ክርስቲያናችን ለዓለም ተቋማት የመልካም ምሳሌ መነሻ እና መድረሻ የኾነ አሠራር የምታስፋፋበትና የምታጠናክርበት የጋራ አቋም እና ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡
