ነጻ ጋዜጦችን ከገበያ ለማስወጣት የሚዳረገው ጫና ተባብሶ ቀጥሏል

በመንግስት ላይ የሰሉ ሂሶችንና መንግስትን የሚያጋልጡ ዘገባዎችን በማቅረብ የሚታወቁ የፕሬስ ውጤቶች እየተዋከቡ ነው፡፡ እነዚህን የፕሬስ ውጤቶች ከገበያ ለማስወጣት መንግስት የተለያዩ ጫናዎችን እንደሚያደርግም ታውቋል፡፡ ጫናው ከበዛባቸው የፕሬስ ውጤቶች አንዱ የሆነው የፍትህ ጋዜጣ አሳታሚ ድርጅት የተርን ኦቨር ታክስ በአግባቡ አላሳወቀም በሚል የ80ሺህ ብር ቅጣት ከተጣለበት በኋላ 16,000 ብር እንዲከፍል ተደርጓል፡፡ ያለፈው ሰኞ ዕለት ደግሞ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ በዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ ክስ ተመስርቶበት ማዕከላዊ ከቀረበ በኋላ በ5000 ብር ዋስ ተለቋል፡፡ ዶ/ሩ ክሱን የመሰረቱቱ ታህሣሥ 28 ቀን 2003 ዓ.ም የታተመው የፍትህ ጋዜጣ “የቦንጋው ሰው” በሚል ርዕስ ባወጣው ፅሑፍ ላይ ስሜ ጠፍቷል በሚል ነው፡፡ 20 ነጥቦች የያዘው ክስ የዘረዘራቸው ጉዳዮች ጋዜጣው የዶ/ሩን ስም በምን መልኩ እንዳጠፋ የማያሳዩ መሆናቸውን የሚገልፀው የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ፅሑፉን ያዘጋጀው ዶ/ር አሸብር በፓርላማ ላይ ከተናገሯቸውና ከሚዲያዎች ጋር ካደረጉት ቃለምልልስ በመነሳት መሆኑን ይናገራል፡፡ በጋዜጣው ላይ በተለያየ መልኩ እየደረሱ ያሉት ችግሮች መንስኤ ምን እንደሆነ ከሰርካዲስ የዜና አገልግሎት ለቀረበለት ጥያቄ “እነሱ የሚፈልጉት አይነት ማዕቀፍ ውስጥ ስላልገባን እንድንሸማቀቅና ህትመታችን እንዲቋረጥ ስለሚፈልጉ የሚያደርጉት ነው” በማለት መልስ ሰጥቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከዶ/ር አሸብር ክስ በስተጀርባም ቢሆን በጋዜጣው ላይ የተቀናጀ ጥቃት ለማድረስ የታሰበ ነገር እንዳለ ጥርጣሬ እንዳለውም ገልጿል፡፡

የአለም አቀፍ የጋዜጠኞች ተከራካሪ ተቋም /CPj/ ተሸላሚ በሆነው ዳዊት ከበደ ባለቤትነት የሚታተመው የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣም በሰራተኞቹ ላይ የስነልቦና ጫና የሚያደርስ ጥቃት ተከፍቶበታል፡፡ አፍቃሬ ኢህአዴግ እንደሆነ በሚታወቀው ዛሚ 90.7 ሬዲዮ ጣቢያ ላይ የጣቢያው ባለቤት በሆነችው በወ/ሮ ሚሚ ስብሀቱ በሚዘጋጀውና ‘የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ’ በተሰኘው ፕሮግራም በተለይ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ላይ ያነጣጠረ የስም ማጥፋት ዘመቻ መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ መንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከአመት በፊት በአዲስ ነገር ጋዜጣ ላይ ያደርግ እንደነበረው በሀገር ክህደትና በሽብርተኝነት የሚወነጅል አይነት ይዘት ያላቸውን ዘገባዎች አውራምባ ታይምስ ጋዜጣን አስመልክቶም በማውጣት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት የአውራምባ ጋዜጣ አሳታሚ ብሉ ሀርዝ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ጉዳዩን ወደሚመለተው የፍትህ አካል ለመውሰድ በዝግጅት ላይ መሆኑም ታውቋል፡፡

ፍትህና አውራምባ ታይምስ ጋዜጦች የተከፈቱባቸው የጥቃት ኢላማዎች የሚፈጥሩባቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳሉ ሆነው አሁንም ከገበያው ላለመውጣት እየተፍጨረጨሩ ቢገኙም ችግሮቹ ካቅማቸው በላይ የሆኑባቸውና ህትመታቸውን ለጊዜውም ቢሆን ለማቋረጥ የተገደዱ የህትመት ውጤቶችም አልጠፉም፡፡ ከነዚህ የህትመት ውጤቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የአዲስ ፕሬስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ መሀመድ ሀሰን ጋዜጣቸው ህትመቱን ካቋረጠባቸው ምክንያቶች ውስጥ የማስታወቂያ እጦት ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ይናገራሉ፡፡ ማታወቂያ የሚያስነግሩ ድርጅቶች እንደ አዲስ ፕሬስ አይነት ጋዜጣ ላይ ማስተወቂያ እንዳያስነግሩ የተለያዩ ተፅእኖዎች እንደሚደረግባቸው ያስረዱት አቶ መሀመድ ከዚህ ሌላ የጋዜጣውን አዘጋጆች የማስፈራራት ሙከራም እንደነበር ገልፀዋል፡፡ መንግስት በፕሬሱ ላይ እያደረገ ባለው በእነዚህና ሌሎች አፍራሽ ተፅእኖዎች ምክንያት እየተጎዳ ያለው አሳታሚው ብቻ ሳይሆን አንባቢውም ጭምር እንደሆነ ያስረዱት አቶ መሀመድ “አንባቢው እንደ ኢትዮ-ቻናል ያሉ የመንግስት ተለጣፊ ጋዜጦችን ብቻ እንዲያነብ ይፈለጋል፡፡” ይላሉ፡፡

አዲሱ የመገናኛ ብዙሀንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ከፀደቀ ወዲህ በመታተም ብቸኛ የፖለቲካ መፅሔት የሆነውና ተወዳጅነትን የተረፈው ቼንጅ መፅሔት ሌላው የችግሩ ሰለባ ነው፡፡ የመፅሔቱ ዋና አዘጋጅ አቶ ስለሺ ሀጎስ ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ መፅሔታቸው ያልታተመበትን ምክንያት በተመለከተ ላቀረብንላቸው ጥያቄ “በመንግስት ላይ ጠንካራ ትችቶችን ስለምናቀርብ ማስታወቂያ የሚያስነግሩ ድርጅቶች ለመፅሔታችን ማስታወቂያ ለመስጠት ይፈራሉ፡፡ በመሆኑም ማስታወቂያ ልናገኝ አልቻልንም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አቶ ስለሺ ጨምረው እንደገለፁት ያለማስታወቂያ በህትመት ሽያጭ ለመቀጠል ቢሞክሩም የወረቀት ዋጋ ውድነት የህትመት ዋጋውን ስላናረው የማይቻል ሆኖባቸዋል፡፡ የህትመት ዋጋ ከፍተኛ በመሆኑ የአንድ መፅሔት ዋጋ ካለፈው መስከረም ወር ወዲህ ከ5 ብር ወደ 8ብር መጨመሩን የገለፁት አቶ ስለሺ ህብረተሰቡ በዚህ ዋጋ መፅሔት መግዛት የማይችልበት የኑሮ ውድነት ውስጥ ስለሚገኝ ከመግዛት ይልቅ 50 ሳንቲም ከፍሎ በኪራይ ማንበብን እንደሚመርጥ አስረድተዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ከፍተኛ ኪሳራ እንዳደረሰባቸው ያልሸሸጉት ዋና አዘጋጁ “ኪሳራዉን ለመቋቋም የምንችልበት አቅም ላይ ባለመሆናችን በየወሩ ቀናችንን ጠብቀን ለመውጣት አልቻልንም” ብለዋል፡፡ ዋና አዘጋጁ አክለውም የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ወደህትመት ለመመለስ እንዲሞክሩ ጠቁመዋል፡፡

አቶስለሺ በመጨረሻ በተለይ የወረቀት ዋጋ ውድነቱ በዚሁ ከቀጠለ ኢትዮጵያ ማንበብና መረጃ ማግኘት ቅንጦት የሚሆንባት ሀገር እንደምትሆን ያላቸውን ስጋት የገለጹ ሲሆን ይህ ከመሆኑ በፊት መንግስት በጥልቅ ሊያስብበት እንደሚገባ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡