የቀድሞ የኢህአፓ ታጋይ አስማማው ኃይሉ አረፈ

“ያልተዘመረለት ትልቅ ሰው ነው” (የዌ. ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት)

    የቀድሞ የኢህአፓ ብርቱ ታጋይ እንደነበር የሚገርለት አንጋፋው ደራሲ አስማማው ኃይሉ (አያ ሻረው)፤ ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ባለፈው ረቡዕ በስደት በኖረባት አሜሪካ ህይወቱ አለፈ፡፡ አስማማው፤ “ከጎንደር ደንቢያ እስከ ዋሽንግተን” (ክፍል አንድና ሁለት) በተሰኙ ልብወለድ መፃህፍቱ በይበልጥ የሚታወቅ ሲሆን አምስተኛ የሥነ ፅሁፍ ሥራውን በቅርቡ ለአሳታሚዎች እንደሰጠ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በአሲምባ በረሃ ለአራት አመታት በትግል የቆየ ሲሆን፤ በ1975 ዓ.ም የኢህአፓ ሰራዊት ሲበተን በስደት ወደ ሱዳን ሄዶ ጥቂት ዓመታት ከቆየ በኋላ ወደ አሜሪካ አቅንቷል፡፡ ለረዥም ዓመታት በአሜሪካ በስደት የኖረው ደራሲው፤ በተለይ ከሶስትና አራት አመታት ወዲህ “ከጎንደር ደንቢያ እስከ ዋሽንግተን፤ ክፍል አንድና ሁለት”፣ “ኢ.ህአሰ፣ አሰብ ክፍል አንድና ሁለት” የተሰኙ አራት መፃህፍትን ለንባብ ያበቃ ሲሆን “አያ ሻረው” የተሰኘ የግጥም ሲዲ ማሳተሙንም የቅርብ ወዳጁ ደራሲና ሀያሲ አለማየሁ ገላጋይ ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡ አስማማው በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ አምስተኛ መፅሃፉን የረዥም ልብ ወለድ ሥራ ለአሳታሚዎች ከሰጠ በኋላ ልቡን ታሞ ቦሌ አካባቢ በሚገኘው አዲስ የልብ ህክምና ማዕከል ገብቶ እንደነበር ያስታወሰው አለማየሁ፤ ወደ አሜሪካ ከሄደ በኋላ ግን በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን ደውሎ እንደነገረው ይገልፃል፡፡
ሌላው የአስማማው የቅርብ ወዳጅ በኢትዮጵያ የዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አቶ አቤይቱ መላኩ ስለሁኔታው ሲያስረዱ፤ አስማማው ቀደም ሲል የካንሰር ህመም አጋጥሞት በህክምና መዳኑን ጠቁመው፣ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ በመጣበት ወቅት በሳንባ ህመም መያዙንና ቦሌ በሚገኘው አዲስ የልብ ህመም ህክምና ማዕከል አስገብተው እንዳሳከሙት፣ ከህመሙም ድኖ ወደ አሜሪካ መመለሱን ገልፀዋል፡፡ አሜሪካ ከሄደ በኋላ እንደተሻለው ገልፆልኝ ነበር የሚሉት አቶ አቤይቱ፤ ሆኖም እንደገና ታሞ ኮሎምቦስ ኦሃዩ በሚገኝ ሆስፒታል ገብቶ መታከሙን ተናግረዋል፡፡ ከዚያም ፊላደልፊያ ሄዶ እዚያም መታመሙንና ሳንባው ውሃ ቋጥሮ ለህልፈት መዳረጉን አቶ አቤይቱ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡ ቀብሩ የትና እንዴት ይከናወን በሚለው ጉዳይ ላይ ከዘመድ ወዳጆቹ ጋር እየመከሩ መሆኑንም አክለው ገልፀዋል፡፡ “አስማማው ያልተዘመረለት ትልቅ ሰው ነው” ያሉት አቶ አቤይቱ፤ “የእሱ ስራና ታሪክ በአግባቡ ሊዘከር ይገባል” ብለዋል፡፡
ሌላው የቅርብ ወዳጁ፤ ደራሲና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ በበኩሉ፤ “አስማማው ብዙ ፅሁፍና ታሪክ ማምረት በጀመረበት ወቅት መሞቱ ያስቆጫል” ሲል በሀዘን ተሞልቶ ተናግሯል፡፡