በሌሉበት ሞት የተፈረደባቸው የደርግ አባል በሆላንድ ታሰሩ

በጎጃም በርካታ ሰዎች እንዲረሸኑና በጅምላ እንዲቀበሩ አድርገዋል ተብሏል

በደርግ የአገዛዝ ዘመን ዜጎችን በመግደል፣ በማሰርና በማሰቃየት ተከስሰው ሞት የተፈረደባቸው አንድ ስማቸው ያልተገለጸ የቀድሞ የደርግ ባለስልጣን፤ በሆላንዷ ከተማ አምስቴልቪን በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኤንኤል ታይምስ የተባለው የአገሪቱ ድረገጽ ትናንት ዘገበ፡፡
በሆላንድ የሚገኘው የአለማቀፍ ወንጀሎች ምርመራ ቡድን አቃቤ ህግ፣ ግለሰቡ እ.ኤ.አ በ1978 ባስተላለፉት ትዕዛዝ፣ በጎጃም አካባቢ ታስረው የነበሩ በርካታ ሰዎች ተረሽነው አስከሬናቸው በጅምላ መቃብር እንዲቀበር ተደርጓል ማለታቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡ተጠርጣሪው ከሁለት ሳምንታት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደዋሉ የጠቆመው ዘገባው፣ አምስቴልቪን ከተማ ውስጥ በሚገኘው የግለሰቡ መኖሪያ ቤት ውስጥ በተደረገ ፍተሻ የተለያዩ ማስረጃዎች የተገኙ ሲሆን በሄግ የሚገኘው ፍርድ ቤትም ከትናንት በስቲያ በዋለው ችሎት፣ ግለሰቡ ለ90 ቀናት በእስር ላይ እንዲቆዩ ወስኖባቸዋል ብሏል፡፡የሆላንድ ፖሊስ ግለሰቡ የተጠረጠሩባቸውን የወንጀል ድርጊቶች ስለመፈጸማቸው ምርመራ ማድረግ መጀመሩን ዘገባው ገልጾ፣ ፖሊስም የምስክሮችን ቃል መቀበሉንና ተጠርጣሪው ድርጊቶቹን ስለመፈጸማቸው ምስክርነታቸውን ከሰጡ ግለሰቦች አብዛኞቹ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን  እንደሆኑ አስታውቋል፡፡ምስክሮቹ በሰጡት ቃል ግለሰቡ በጎጃም አካባቢ የደርግ ባለስልጣን ሆነው ባገለገሉባቸው አመታት የተጠቀሱትን የወንጀል ድርጊቶች ስለመፈጸማቸው ተናግረዋል ያለው ዘገባው፣ የሆላንድ የወንጀል ምርመራ ባለስልጣናትም ግለሰቡን ለሞት ቅጣት ያበቃቸውን የወንጀል ክስ የተወሰነ መረጃ ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት መረከቡን ገልጧል፡፡የአለማቀፍ ወንጀሎች ምርመራ ቡድን፣ በደርግ የአገዛዝ ዘመን በደብረ ማርቆስና በመተከል እስር ቤቶች ውስጥ የግድያና የስቃይ ድርጊቶችን በፈጸሙ ግለሰቦች ላይ ትኩረት በማድረግ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ ዘገባው አስታውቋል፡፡
61 አመታቸው እንደሆነ የተነገረላቸው እኒሁ ባለስልጣን፤ ከጥቂት አመታት ወዲህ ነዋሪነታቸውን በሆላንድ እንዳደረጉና የአገሪቱ ዜግነት እንደተሰጣቸው ያስታወሰው ዘገባው፣ ግለሰቡ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤት በሌሉበት የእድሜ ልክ እስራትና የሞት ቅጣቶች እንደተጣሉባቸውም ገልጧል፡፡