እስቲ ሐቁን እንመስክር፡ ብአዴን/ኢህዴን ማን ነው?
ዛሬ ጧት አንድ የብአዴን ባለስልጣን ፍፁም የበታችነት ስሜቱን በሚሳብቅ መልኩ “ብአዴን ከአንድ ጀግና ህዝብ የራሱን ዐላማ አንግቦ የተነሳ፣ ብዙ ጀብዶች የፈፀመ፣ ብዙ መስዋዕትነት የከፈለ፣ በራሱ ዐላማ የቆመ ፓርቲ እንጅ የማንም ተለጣፊ ሆኖ አያውቅም” ሲል ኢቢሲ ሰማሁ፡፡ እሰየው! እንዳፉ ያድርግለት!
እውነት ግን ኢህዴን/ብአዴን ማነው? እስቲ ትንሽ እንፈትሸው፤
ስለብአዴን የበረኸ ትግል ሳስብ የማያልፉት የለም ምናምን ስሰማ ትዝ የሚለኝ የአስገደ ገ/ስላሴ ጋህዲ 3 መፅሐፍ ነው፡፡ መቸም አስገደ አንድ ቀን ወደ አማርኛ እንደሚተረጉመው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በእርግጥም እንቅስቃሴ ላይ እንደነበረና ትንሽ የፋይናንስ እክል እንዳዘገየው አውቃለሁ፡፡
ጋህዲ-3 እንደሚነግረን፤
– ኢህዴን/ብአዴን ከምስረታው 1873 ጀምሮ እስከ 1983 ዐ.ም
– 100% ቀለብ፣ ትጥቅና ማንኛውም የሚያስፈልገውን ነገር የሚያገኘው ከህ.ወ.ሐ.ት ነበር፡፡ ለአንድ የህ.ወ.ሐ.ት ታጋይ 500 ግራም ቀለብ የቀን ራሽን የነበረ ሲሆን ለአንድ የኢህዴን/ብአዴን ታጋይ ደግሞ 800 ግራም ዱቄት የቀን ቀለብ ተመድቦለት ነበር፡፡ በዐመትም ሁለት የወታደር ልብስ ይሰጠው ነበር፡፡
– 98% ወታደራዊ ስልጠና የሚያገኘውም ከህ.ወ.ሐ.ት ነበር- ከምስረታው እስከ መጨረሻዋ ሰዐት
– የመጓጓዣ ግልጋሎትም 100% ከህ.ወ.ሐ.ት ነበር የሚያገኘው፡፡ ከ1977 ረሐብ በኃላ በተለይም በ1980ዎቹ ህ.ወ›ሐ.ት በርካታ መቶዎች ተሸከርካሪዎች ሲኖሩት ኢ.ህ.ዴ.ን ግን ምንም አልነበረውም፡፡ የነዳጅና ሌላ ሌላ ወጪም ሙሉ በሙሉ በህ.ወ.ሐ.ት የሚሸፈን ነበር፡፡
– የኢ.ህ.ዴ.ን የውጪ ጉዞ ወጪም 100% በህ.ወ.ሐ.ት የሚሸፈን ነበር፤
ብቻ 100 በ100 የህ.ወ.ሐ.ት ጥገኛ ነበር፡፡
ሌላው የሚገርመው ነገር 1983 ዐ.ም ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ አዲስ አበባ ሲቆጣጠር የነበረው የሐይል ሚዛን ነው፡፡ በአስገደ ስሌት መሰረት ህ.ወ.ሐ.ት አዲስ አበባ ሲገባ መደበኛ ሰራዊት፣ አዲስ ምልምሎች፣ የአካባቢ ሚሊሻዎች፣ ሲቪል አጋር ሁሉም ተደምሮ 223 ሺሕ ገደማ ሐይል ነበረው፡፡ ኢ.ህ.ዴ.ን ደግሞ ጠቅላላ 4500 ብቻ ነበረው፡፡ ከዚህም በመደበኛነት ውጊያ ላይ የነበረው 300 ሰው ብቻ ነው! ዘኢትገርም!
ጋህዲ- 3፡ ገፅ 163- 165
መፅሐፉ በገፅ 149- 151 እንደሚያትተው (በአጭሩ) ደግሞ ከኢ.ህ.አ.ፓ መፈራረስና በህ.ወ.ሐ.ት መመታት በኃላ በህይወት የቀሩትና እጃቸውን ለህ.ወ.ሐ.ት የሰጡ ጥቂቶቹ ገሚሱ ሱዳን ለመግባት ሲወስን ገሚሱ ደግሞ አዲስ ፓርቲ አቋቁሞ ከህ.ወ.ሐ.ት ጎን ለመዋጋት መወሰኑን ተከትሎ ይሀንን የኢህዴን ፓርቲ ምስረታ የሚያማክሩና በበላይነት የሚቆጣጠሩ ስየ አብርሀና አባይ ፀሀየ ነበሩ፡፡ ለስልጠና ዝግጁ የሆኑትን 65 የሚሆኑትን በነሐድጉ ከበደ፣ ጀላኒ ፈረጅና ሐለፎም ቸንቶ በሚባሉት አሰልጣኞች ወታደራዊ ስልጠና የተሰጣቸው ሲሆን ይሀንን በበላይነት የሚከታተሉት አቶ (አሁን ዶ/ር) አረጋዊ በርሀ (በሪሁ በርሀ)፣አቶ አባይ ፀሃየና አቶ ስየ አብርሀ ነበሩ፡፡ (ምናልባት ይህንን የፈጠረባቸው የበታችነት ስሜት ይሆን ብአዴን እነስየን ሲያዩ መምጰርጰራቸው)… መቸም እነእንትና ይህንን የነእንትና ስራና ታሪክ ለነእንትና ለማሸከም ሲጣጠሩ ብንታዘብም እውነቱ ይኼ ነው፡፡
ከላይ እንደገለፅኩት ኢህዴኖች ስልጠና ሲጀምሩ 65 የነበሩ ሲሆን እየተንጠባጠቡ ሄደው ስልጠናውን ሲጨርሱ 39 ብቻ ቀሩ፡፡ ስልጠናውን ሲጨርሱም ዐብዪ ዓዲ ላይ በሬዎች ታርደው ድል ያለ ድግስ ተደርጎ ነው ደምበኛ የምርቃት ስነ-ስርዐት የተካሄደው፡፡ አኢ.ህ.ዴ.ን የሚለው ኦፊሴላዊ ስምም ያገኙት ከዚያ በኃላ ባሉት ቀናት ነው፡፡
ኢ.ህ.ዴ.ን ህወሐት ቀደም ባሉ ተከታታይ ውጊያዎች ነፃ ባወጧቸውና እነሱ ሐራ መሬት በሚሏቸው የሰቆጣ አውራጃ ቦታዎች ዋግ ሕምራ፣ ጃን አሞራ፣ በየዳ፣ ሰሀላ፣ ደረስጌ፣ ሰላምጌ፣ ታርናሽሄ፣ ፍየልውሀ ወ.ዘ.ተ እንዲንቀሳቀሱ የራሱ የህ.ወ.ሐ.ት የሆኑትን 30 የአከባቢው ሚሊሻዎች፣ ሁለት ጠንካራ ሐይሎችና (እያንዳንዱ መቶ መቶ ሰው የሚያጠቃልል) 8 የፕሮፖጋንዳ ባለሙያዎችን ሁሉ ጨምሮላቸው የበረኸ ትግል አስጀመራቸው፡፡ አቶ በረከትና አቶ ካሳ ተ/ብርሀን በድፍረት ሰቆጣ ነፃ አወጣናት ምናምን ሲሉ ለሚሰማ የህ.ወ.ሐ.ት ታጋይ እልም ያለ ፌዝ እንደሆነም መፅሐፉ ያሳያል፡፡
መፅሐፉ በግልፅ እንደሚያሳየው በግዜው ኢህዴን በብዙ መልኩ አቅም ያልነበረውና የሆነ ሀይል እፍ ቢልበት ድርግም ብሎ ሊጠፋ የሚችል ሐይል ስለነበረ ህ.ወ.ሐ.ት የኢህዴን በህይወት መዝለቅ አስፈላጊነት በመረዳት እዳይሞት እንዳይከፋው ጠብቆና ተንከባክቦ በርካታ ጠባቂ ተመድቦለት፣ ስንቅም ምንም ሳይጓደልበት፣ የተኩስ ድምፅም እምብዛ ሳይሰማ አዲስ አበባ የደረሰ ቡድን ነው፡፡ በመፅሐፉ በ21 ገፆች (147-168) በዝርዝር የተፃፈው የኢ.ህ.ዴ.ን/ብ.አ.ዴ.ን.ና ህ.ወ.ሐ.ት አስገራሚ የአባትና ሞልቃቃ ልጅ ዐይነት ግንኙነት በርካታ አስገራሚ ዝርዝር ጉዳዮችን ይዟል፡፡
በሌላ በኩል በያኔው ጊዜ ከጠርናፊዎቻቸው አንዱ የነበረና በጊዜው ከከፍተኛ የህ.ወ.ሐ.ት አመራሮች አንዱ የነበረ አመራርና ( ኃላ በ1993 ዐ.ም የህ.ወ.ሐ.ት ክፍፍል አንጃ ተብለው በነመለስ ከተመቱቱ አንዱ ነው) ሌሎች የህ.ወ.ሐ.ት አባላት እንደሚነግሩን ደግሞ ብአዴን 1979 ዐ.ም ሙሉ ለሙሉ ፈርሶ ትግሉን ሊያቆም ጫፍ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ እነ በረከት፣ አዲሱ፣ ተፈራና ሌሎች አመራሮች ሁሉ ጨምሮ ትግሉን ለማቆም ከወሰኑት ውስጥ ነበሩ፡፡ በጊዜው ጥቂቶች ተደብቀው በሱዳን በኩል ሲወጡ የሚበዙቱ ግን በዋናነት በአቶ ታምራት ላይኔ ከፍተኛ ጥረት፣ በህ.ወ.ሐ.ት አመራሮች ልመና ትግሉን እንዲቀጥሉ ሆኗል፡፡ በጊዜው ሰንጋ በሬ ታርዶ ተደግሶ ሆዳቸውን ማጠርቃት ተችሎ ነበር፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮም በህ.ወ.ሐ.ት የሚሰፈርላቸው ቀለብ በዐይነትና በጥራት ተሻሽሎ፣ በዐመት የሚሰጣቸው ዩኒፎርምም መጠኑ ጨምሮ፣ እስከ መጨረሻዋ ሰዐትም በህ.ወ.ሐ.ት ሰራዊት እየተጠበቁ፣ ብርድ ፀሐይ ይሁን ጥይት እንዳያገኛቸው ከፍተኛ እንክብካቤ እየተደረገላቸው ከቤተ-መንግስት ደረሱ፡፡
የትላንቱ እውነታ ይኼ ነው፡፡ እርግጥ ነው፤ በአሁን ሰዐት ብአዴን በብዙ መልኩ አሁን ሙሉ ለሙሉ በዝርፊያ፣ በስካርና፣ በዝሙት፣ በውሸት ናላውን ከዞረበት ህ.ወ.ሐ.ት የተሸለ ቁመና አለው፡፡ ትላንት ያን ያክል የደመቀ ታሪክም ባይኖረው ዛሬ የተሻለ ራዕይ፤ ህዝባቸውን የሚያከብሩ፣ እየዘረፉም ቢሆን የተወሰነ ነገር የሚሰሩ የተሻሉ ሰዎችም አሉት፡፡ የህ.ወ.ሐ.ትን ያክል በቁሙ የሞተ፣ የሙሉ ሰዐት ዋሾና ሌባ፣ የደናቁርት ስብስብ ወደመሆን ደረጃ ግን አልወረደም፡፡ብአዴን የህ.ወ.ሐ.ትን ያክል በሕዝብ ላይ ከፍተኛ ንቀት፣ ጭካኔ ይኖረዋል ብየም አላስብም፡፡