የአ/አበባ ሀ/ስብከት: ከጽ/ቤቱ የሕንጻ ኪራይ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ አልሰበሰበም፤ የሒሳብና በጀት ሓላፊው ኤልያስ ተጫነ ዋነኛ ተጠያቂ ናቸው
- እስከ 360 ሺሕ ብር ከፍተኛ ውዝፍ ያለባቸው ተከራዮች እንደሚገኙበት ታውቋል
- በቤተ ዘመድ የተሸፋፈነው የክፍያው አሰባሰብ የአስተዳደር ጉባኤ አባላቱን አወቃቅሷል
- በፍሳሽ እና በቃጠሎ አደጋ የተጎዳው ሕንጻ ከዕድሳት ዕጦት ደኅንነቱ ለአደጋ ተጋልጧል
* * *
- ሓላፊው፣ በደንቡ መሠረት ለአስተዳደር ጉባኤው የሒሳብ ሪፖርት አቅርበው አያውቁም
- የበጀት ዓመቱ የኻያ በመቶ የፈሰስ ሪፖርታቸውም በጥንቃቄ እንዲመረመር ተጠይቋል
- ከሓላፊነታቸው እንዲነሡ በፓትርያርኩም በተደጋጋሚ ቢጠየቅም እንዲቀጥሉ ተደርጓል
* * *
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት፣ ለተለያዩ አገልግሎቶች ከአከራያቸው የሕንጻው ክፍሎች ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የኪራይ ክፍያ አለመሰበሰቡ ተገለጸ፤ ጽ/ቤቱ፣ ተከራዮች ውዝፋቸውን ከነመቀጫው አጠናቀው እንዲከፍሉ የቀናት ገደብ በመስጠት ቢያስጠነቅቅም ዕዳውን ለማስከፈል አልቻለም፡፡
የሀገረ ስብከቱን ሕንጻ ለቢሮ፣ ለሕክምና እና ለሱቅ አገልግሎቶች ከተከራዩ ስድስት ተከራዮች ያልተሰበሰበው አጠቃላይ ክፍያ ብር 675 ሺሕ 244 ከ31 ሳንቲም ያህል እንደኾነ ጽ/ቤቱ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር መጨረሻ ከጻፈው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ማስጠንቀቂያው ከደረሳቸው ተከራዮች መካከል፣ ከሰኔ ወር 2005 ዓ.ም. ወዲህ ኪራያቸውን ሳይከፍሉ የቆዩና እስከ 360 ሺሕ ብር ከፍተኛ ውዝፍ ያለባቸው እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡
ተከራዮች ደብዳቤው በደረሳቸው በሦስት ቀናት ውስጥ ውዝፍ ዕዳቸውን ከነመቀጫው ከፍለው ለጽ/ቤቱ ካላሳወቁ ቢሮዎቻቸውና ሱቆቻቸው እንደሚታሸጉ ነሐሴ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ቀነ ገደቡ ካለፈም በኋላ እንደሚጠበቀው ተግባራዊ ሳይኾን ከወር በላይ ማስቆጠሩ ተገልጧል፡፡
በከፍተኛ የክፍያ ዕዳ ከሚታወቁ ተከራዮች መካከል ከአንዳንድ የሀገረ ስብከቱ የአስተዳደር ጉባኤ አባላት ጋር ግንኙነት ያላቸው እንደሚገኙበት ምንጮቹ ጠቁመው፤ አጀንዳው በአስተዳደር ጉባኤው ስብሰባ ላይ ቀርቦ በታየበት ወቅትም “የገቢ አሰባሰቡ በዝምድና የተሸፋፈነ ነው” በሚል ሓላፊዎቹን እርስ በርስ አወቃቅሶ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
“ኪራዩ በወቅቱ ቢሰበሰብ፣ በጊዜው የነበረውን ዋጋ ያህል ቤተ ክርስቲያኒቱ ልትሠራበትና ልታተርፍበት የምትችልበት ገንዘብ ለግለሰቦች መጠቀሚያ ኾኗል፤” የሚሉት የሀገረ ስብከቱ ምንጮች፣ የፋይናንስ እና በጀት ዋና ክፍሉን ቀዳሚ ተጠያቂ አድርገዋል፡፡
ዋና ክፍሉ ከኪራዩ የሚሰበሰበውንና የቀረውን ገቢ በየጊዜው በሪፖርት በማሳወቅ ክፍያው እንዳይወዘፍ ማድረግ የሚገባው ቢኾንም አለማቅረቡ የሓላፊውን የሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነን ድክመት እንደሚያሳይ ምንጮቹ አስረድተዋል፡፡የሀገረ ስብከቱ ቀንደኛው የሙስና ቴክኒሻን የኾኑት ሊቀ ጠበብት ኤልያስ፣ በደንቡ መሠረት ወቅቱን ጠብቀው ለቁጥጥር ዋና ክፍሉ እና ለአስተዳደር ጉባኤው ማቅረብ የሚገባቸውን የሒሳብ ሪፖርት በታሪክ አቅርበው እንደማያውቁ ምንጮቹ ይናገራሉ፡፡
ሊቀ ጠበብት ኤልያስ፣ ከዐሥር ዓመታት በላይ ባስቆጠሩበት ሓላፊነት፣ ገዳማትና አድባራት ለሀገረ ስብከቱ የሚያደርጉትን የኻያ በመቶ ፈሰስ ከአማሳኞች ጋር አየር ባየር እየተቃረጡ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የተጭበረበረ ሪፖርት በማቅረብ ከ120 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ባለዕዳ ያደረጉ ናቸው፡፡
አዲስ ተመድበው የሚመጡ ዋና ሥራ አስኪያጆችን በሙስና በማበሳበስ እንዳስለመዱት፣ አኹንም በጥቅም የተቆራኟቸውና ከሓላፊነታቸው እንዳይወገዱ ሎቢ የሚያያደርጉላቸው ዋና ሥራ አስኪያጁ የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ “በታሪክ ከፍተኛ መጠን ያለው” በሚል ሰሞኑን ዲስኩር ያበዙበት የበጀት ዓመቱ የገዳማትና የአድባራት የፈሰስ ሪፖርትም፣ በሥልጣን ለመሰንበት ከመቋመጥ ያለፈ ዓላማ የሌለው በመኾኑ በዚኹ ዐይን በጥንቃቄ መመርመር እንደሚገባው ምንጮቹ ያሳስባሉ፡፡
ከሓላፊነታቸው እንዲነሡ በፓትርያርኩ ጭምር ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብባቸውም በሎቢ እንዲቀጥሉ የተደረጉት ሊቀ ጠበብት ኤልያስ፣ በአዲስ አበባ – ለቡ እና በመቐለ የፎቆች፣ አራት የኮንዶሚኒየም የንግድ ቤቶችና የደለበ የባንክ ተቀማጭ በምዝበራ ያካበቱበትን ሓላፊነት ለማስጠበቅ የተጭበረበረ ሪፖርት ከማቅረብ አልፈው አስከፊ ወንጀል ከመፈጸም እንደማያመነቱ ይነገርባቸዋል፡፡
በ2003 ዓ.ም. የንቡረ እድ አባ ገብረ ማርያም አስተዳደር ወቅት፣ በብቃት ማነስና በታማኝነት ጉድለት በተነሡበት ወቅት፣ ለአጭር ጊዜ በቦታቸው ተክተው ከነበሩት ግብረ ገቡና ሞያተኛው መሪጌታ ይትባረክ ካሴ ድንገተኛ አሟሟት ጋር በተያያዘ በሚበዙት የጽ/ቤቱ ሠራተኞች ስማቸው በነፍሰ ገዳይነት የሚነሣውም በዚኹ የግፍ ተግባራቸው ሳቢያ ነው፡፡
እስከ ዛሬ ይፋ ያልወጣው የመሪጌታ ይትባረክ ካሴ ድንገተኛ አሟሟት፣ በሰው እጅ ተመተው በተፈጸመባቸው ግድያ እንደኾነ ወድቀው ከተገኙበት ወደ ሆስፒታል ገብተው በተደረገው ምርመራ መረጋገጡን የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች ይናገራሉ፤ ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ወደ ቦታው የተመለሱበት ኹኔታም ጥርጣሬቸውን እንደሚያጠናክረው ያስረዳሉ፡፡
ጭካኔአቸው በዚኽ ደረጃ የሚገለጸው ሓላፊው፣ ዛሬም ከዋና ሥራ አስኪያጁና ከቁጥጥር ዋና ክፍሉ ጋር በመመሳጠር የሚፈጽሟቸውን ምዝበራዎች ሊያውቁብንና ሊነቁብን ይችላሉ ያሏቸውን የሀ/ስብከቱን ሠራተኞች አግባብነት በሌለው የዘፈቀደ ዝውውር ከጽ/ቤቱ በማራቅ ማንላታቱን ቀጥለውበት ይገኛሉ፡፡
በ2001 ዓ.ም. በወቅቱ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል አስተዳደር፣ በ20 ሚሊዮን ብር ወጪ ተሠርቶና በቀድሞው ፓትርያርክ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የጽ/ቤቱ ሕንጻ ባለቤት አልባ እስኪሰኝ ድረስ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚታይበት ተመልክቷል፡፡
በምንጮቹ እንደተጠቆመው÷ በ2006 ዓ.ም. በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ግቢ ቃጠሎ በደረሰበት ወቅት በደቡብ ምዕራብ የሚያዋስነው የሕንጻው መስኰትና ኮርኒሱ ተሰነጣጥቀዋል፤ ረግፈዋል፤ ከሊቀ ጳጳሱ ቢሮ ወደ ታች እንዳለ በስብሷል፤ ጣሪያው፣ ኮርኒሱ፣ መስኰቱና በአጠቃላይ የጂፕሰም ሥራዎቹ ላይ ነው ጉዳቱ የሚታየው፤ እንኳን አዲስ ሕንጻ ሊገነቡና ሊያለሙ ቀርቶ ያለውም ወደ መፍረሱ ተቃርቧል፤ ብዙ ወጪ የወጣበት ሕንጻ ባለቤትና ተመልካች አልባ ኾኗል፤ አስቸኳይ ዕድሳት ካልተደረገለትም ደኅንነቱን አስጊ ያደርገዋል::
ምንጭ፡- አዲስ አድማስ፤ ቅጽ 16 ቁጥር 821፤ መስከረም 29 ቀን 2008 ዓ.ም.
