የይድነቃቸው ተሰማን ራእይ ‹‹አተላ›› ሲውጠው! (አሌክስ አብርሃም)

Yidnekachew Tessema
(አሌክስ አብርሃም)

ባጭሩ ይድነቃቸው ተሰማ ከ1914 – 1979 የኖረ ‹‹የአፍሪካ የእግር ኳስ አባት›› እሰከመባል የደረሰ ታላቅ የስፖርት ሰው ነው !! የኢትዮጲያም ሆነ የአፍሪካ እግር ኳስ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ለመድረሱ ይድነቃቸው ስም በጉልህ ምክንያት ሁኖ ሊጠቀስ ይችላል። ይድነቃቸው ተሰማ ስለኳስ የሚያትት እና በቲዎሪ የሚያደነቁር ሰው አልነበረም …1935 የመጀመሪያው የአገራችን እግር ኳስ ክለብ ሲመሰረት በታዳጊ ተጨዋችነት ተሰልፏል!! በዚህ አላቆመም ለብሔራዊ ቡድናችንም ተመረጠ እንጅ!!ከአስራአምስት ጊዜ በላይም ተሰልፎ ለብሄራዊ ቡድኑ ተጫውቷል!የተጨዋችነት ዘመን እንዳበቃ … አሰልጣንም ሆኖ አስገራሚ ቡድን መመስረት ችሎ ነበር!! ኢትዮጲያ እስካሁን ህልም የሆነባት የ1962 ዓ/ም ሶስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ የአገራችን አሸናፊነትም የተፈፀመው በይድነቃቸው መሪነት ነበር !! ከዛስ …ከዛማ …አስገራሚው ጉዳይ ጀመረ። ለአገራችን ብሎም ለአፍሪካ እግር ኳስ ታላቅ ነገርን ማድረግ ጀመረ !1955/56 ዓ/ም አካባቢ የመጀመሪያውን ስፖርት ቢሮ አስከፍቷል !ይህም ለአሁኑ ስፖርት ፌዴሬሽን መሰረት የጣለ ጉዳይ ነው።

እንግዲህ ይህ ታላቅ ሰው ስሙ ከሚጠቀስበት ታላቅ ነገር አንዱ የአልኮል መጠጥ እና የሲጋራ ማስታወቂያዎች ወደስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ድርሽ እንዳይሉ ያደርግ የነበረው ጥረት ነው … ይግረማችሁና ይህን ሃሳቡን ክፉኛ የተቃወሙ የአልኮል መጠጥ አምራቾች አከፋፋዮች ጋር ሃይለኛ ግጭት ውስጥ ሁሉ ገብቶ ነበር። እንደውም ይድነቃቸው 1953 ዓ/ም ከተተኮሰበት ጥይት መትረፍ ችሏል !! ታዲያ በቃ የራሱ ጉዳይ ይሄን ጣጠኛ የኢትዮጲያ ኳስ ተውና እርፍ በል ተብሎ ሲመከር እንዲህ አለ ‹‹የኢትዮጲያ እግር ኳስ ተዳክሞ ከማይ ሞቴን እመርጣለሁ›› እንዳለውም ገፋበት…ኢትዮጲ ግብፅና ሱዳን የአፍሪካን እግርኳስ ኮንፈደሬሽን ሲያቋቁሙ የኛ ይድነቃቸው ለምስረታው ዋና ምሰሶ ነበር። የዛሬው የአፍሪካ ዋንጫ እንግዲህ በኛው ሰው ግፊት የተጀመረ አሃጉራዊ የስፖርት ውድድር መሆኑን ልብ በሉ !
ታዲያ የዚህ ሰው ታላቅ እራእይ ጤነኛ ጠንካራ ከአልኮል መጠጦችና ተዛማጅ ሱሶች የራቀ ስፖርተኛ ማፍራት ነበር …. ራሱ መሰረቱን በጣለው ‹‹ፌዴሬሽን›› አፈር ድቤ በላ እንጅ ! አሁን ስታዲየም ብትሄዱ በክብር የተኮፈሰው የአተላ ማስታወቂያ ነው … የስፖርት አድራጊ ፈጣሪዎቹ ታላላቆቹ የስካር ፋብሪካዎች ናቸው። ይሄ ብቻ አይደለም …ጭራሽ የኢትዮጲያ ፕሪሚየር ሊግን ስም … ፌዴሬሽኑ በስድስት ሚሊየን ብር ሸጦ ‹‹የምንትስ ቢራ ፕሪሚየር ሊግ›› እንዲባል መወሰኑ ተሰምቷል ! የይድነቃቸው ራእይ አልቆለታል!አተላ እንደኖህ ዘመን ውሃ ምድራችንን ሲሞላት ከበላያችን ሊንሳፈፍ የሚችለው ብቸኛ ነገር ….የሚያድነን መርከብ ሳይሆን በስካራችን የናጠጡ የስካር ፋብሪካ ባለቤቶች ብቻ ናቸው !! ነገ ባንዲራችን መሃል ላይ የቢራ ጠርሙስ ታትሞ የማይውለበለብበት ምክንያት የለም …ሩቅ ይምሰለን እንጅ ነገ ቤተእምነቶቻችን ዩኒቨርስቲዎቻችን የአተላው ሰለባ የማይሆኑበት ምክንያት የለም።

በቀጣዮቹ ሃያ ዓመታት የኢትዮጲያችን ትልቁ ጠላት የቢራ እና ሌሎች አልሎል መጠጦች ፋብሪካዎች እንደሚሆኑ አትጠራጠሩ ! ፌዴሬሽኑ ገንዘብ ቸግሮት ይሆናል …ግን ትውልድን ለአተላ ሸጦ ገንዘብ ማግኘት ከአንድ ፌዴሬሽን ያውም የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የማይጠበቅ ወራዳ ተግባር ነው !! ያውም ከሱስ ነፃ የሆነ ወጣት …አገርን የሚወክል ብሔራዊ አደራ የሚሸከም ስብስብ እፈጥራለሁ ከሚል ፌዴሬሽን አይጠበቅም። መቸም ነፃ አገር ፍትሃዊ እና የህዝብ ድምፅ የሚሰማበት ቢሆን ኑሮ አገራችን ….እነዚህን የፌዴሬሽን ሰዎች ከነአተላ ማስታወቂያቸውና ‹‹ከነደም ዋጋቸው›› ስፖርት ማዘውተሪያዎቻችን አካባቢ ድርሽ እንዳይሉ እንደቆርኪ ጠርጎ ማባረር በተገባ ነበር። ግን ምን ያደርጋል … ትውልድን ደም ሸጠው ጤነኛ ትውልድ ሊፈጥሩ ይሄው ፕሪሚየር ሊጉን ‹‹የአተላ ፕሪሚየር ሊግ ›› ሊያስብሉት ጉዳያቸውን ጨራርሰዋል!! አገራችንን ወደትልቅ የመጠጥ ጋንነት የመቀየሩ ስራ በተሳለጠ ሁኔታ እየተፈፀመ ነው። ይሁንና አሁንም ‹‹በልክ መጠጣት›› በሚል የጅል ፈሊጥ ትውልዱ ላይ የሚቀልዱ ጅሎች በጅልነታቸው ጅል ሞት እየጋበዙ ነው።

መጠጥ በማንኛውም መጠን በማንኛውም ሁኔታ ፀያፍ ነው !!