ከ8 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለረሃብ ተጋልጧል

መስከረም ፳፬ (ኅያ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መንግስት እና አለማቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች በኢትዮጵያ 4 ሚሊዮን 500 ሺ ህዝብ በረሃብ መጠቃታቸውን ይፋ ቢያደርጉም፣ በከተሞች የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ዜጎች ቁጥር ሲጨመር አጠቃላይ የተረጅዎችን ቁጥር ከ8 ሚሊዮን በላይ ሊያደርሰው እንደሚችል መረጃዎች አመልክተዋል።
በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ሪፖርት ሲደረግ የቆየው በገጠሩ የሚታየው ችግር ብቻ ነው። ይሁን እንጅ የከተማና የኮንስትራክሽን ልማት ሚኒስትር መኩሪያ ሃይሌ ባለፈው ሳምንት በካፒታል ሆቴል በአንድ ስብሰባ ላይ በሰጡት መረጃ፣ ከድህነትና ስራ አጥነት ጋር ተያይዞ በከተሞች ብቻ ለምግብ እጥረት የተጋለጡ 4 ሚሊዮን 700 ሺ ዜጎች መኖራቸውን ይፋ አድርገዋል።
የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ከተሞች አዲስ አበባን ጨምሮ 11 ናቸው። መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ 10 ቢሊዮን ብር መመደቡን እንዲሁም ምግብ ከማቅረብ ባሻገር የሚሰሩና የማይሰሩትን በመለየት ስልጠና ለመስጠት መታቀዱንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተሞች አካባቢ ከዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ወጣቶች ጭምር ለስራአጥነት እየተዳረጉ መምጣት ማህበራዊ ችግሩን ያባባሰ ሲሆን፣ ገዥውን ፓርቲም ድንጋጤ ላይ ጥሎታል።
በአገሪቱ የተከሰተውን ረሃብ ለመታደግ አንዳንድ አገሮች እርዳታ መስጠት ቢጀምሩም በቂ እንዳልሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። እስካሁን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምግብ ፕሮግራም፣ ኖርዌይና እስራኤል እርዳታ ለግሰዋል። ከዚህ ቀደም ከፍተኛ እርዳታ በማቅረብ የሚታወቁት አሜሪካና ካናዳ እስካሁን በይፋ የሰጡት እርዳታ ስለመኖሩ የታወቀ ነገር የለም።
ድርቁ አስከፊ በሆነባቸው በኦሮምያ ፣ አፋርና ደቡብ እንዲሁም በምስራቅ ጎጃም አካባቢዎች እንስሳት በመግብ እጥረት እየሞቱ ሲሆን፣ በትግራይ ደግሞ ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ በሽታ ተከስቷል።
መንግስት የአለማቀፍ እርዳታ እየጠየቀ ባለበት ወቅት፣ አሁንም ከፍተኛ ወጪ እያወጣ በአላትን እያከበረ ነው። ባለፈው አመት ለብሄር ብሄረሰቦች ቀን፣ ለባንዲራ ቀን፣ ለመከላከያ ሰራዊት ቀን፣ ለህወሃት 40ኛ አመት ምስረታ፣ ለኦህዴድ 25ኛ አመት በአል እና ለሌሎችም የፖለቲካ ስልጠናዎች በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ አድርጓል። በሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ በሰሜንና ደቡብ ጎንደር እንዲሁም በምስራቅ ጎጃም የገጠር ቀበሌዎች ዜጎች ከፍተኛ የምግብ እጥረት አጋጥሞአቸው እርዳታ በሚጠይቁበት ወቅት፣ ክልሉን አስተዳድረዋለሁ የሚለው ብአዴን፣ 35ኛ አመት በአሉን ለማክበር በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ መመደቡንና ጋዜጠኞችንና አርቲስቶችን ወጪያቸውን በመሸፈን የተለያዩ ቦታዎችን በማስጎብኘት ላይ መገኘቱ የክልሉ መነጋገሪያ ሆኗል።
ገዢው ፓርቲ በአገሪቱ ውስጥ የተከሰተው ረሃብ እንዳይታወቅበት ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን አረና ፓርቲ አስታውቋል። ድርጅቱ የአገራችንና የክልላችን ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ የሚመለከት በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ “በ40ኛው የህወሓት ምስረታ በአል ከአጠቃላይ ታራሹ መሬት ግማሹ በመስኖ እየለማ ነው እንዳልተባለ በትግራይ ክልልና በብዙዎች ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተጋርጦ ያለው የድርቅ ችግር መንግስት ችግሩ ለማሳነስና ለመደበቅ እየሞከረ ቢሆንም ችግሩ ተገቢውን አትኩሮት እንዲሰጠው የድርቁ ተጠቂዎች በረሃብ እየተጠቁ ሰለሆኑ ከብቶቻቹሁን ሽጡ ከማለት ከብቶቻቸውን የሚያድኑበት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲደረግ የእንስሶቹ ምግብ እንዲቀርብላቸው በትግራይ ህዝብ ደም የተገኘው የትእምት ሃብትም ግዜ ሳይጠፋ የህዝቡን ችግር በመፍታት የራሱን ሚና በወቅቱ እንዲጫወት ” ሲል ጥሪ አቅርቧል።
አረና አያይዞም “አገራችን ኢትዮጵያ ትሁን ትግራይ በአሁኑ ግዜ የመልካም አስተዳደር ችግር ፣ የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ችግር፣ የፍትህ እጦት፣ የስራ እጦት፣ የወጣቶች ስደት፣ ሙስና ፣ የሚድያ አፈና፣ የፖለቲከኞች፣ የጋዜጠኞችና ፀሓፊዎች አፈና፣ እስራት፣ ሰፊ አገሪቱን አካባቢ የሚሸፍን የዝናብ እጥረት፣ ድርቅና ርሃብ ተደማምረው የአገራችን ህዝቦች ቀውስ ውስጥ ” ገብተዋል ብሎአል።

2 Comments on “ከ8 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለረሃብ ተጋልጧል”

  1. it is more than 15 million.
    No enough food in cities.
    Only mafias enjoying the shortage of foods as development.

  2. እሥከመቼ ነው ወገን ለልመና ድርድር እየቀረበ የምንኖረው በምግብ

    ራሣችንን ችለናል ብለው እንዳህያ ሢያናፋ የነበሩ ጉጅሌዎች አሁን ነው

    እንደጅብ ጉድጓድ መቆፈርና መደበቅ የመረጡት ለምንሥ የክምችት እህል

    በፖርላማ ፀድቆ እንዲሸጥ ተደረገ የዶላር ጥማት በወገን ረሀብ መርካት

    እጅጉን ኢሠብአዊ ድርጊት ነው ከተጠያቂነት አያመልጡም ቀድሞ ጢሻ

    የገባነው መሬት ላራሹ እንዲሁም ገበሬው የዘመናዊ እርሻ ባለቤት ሆኖ

    ራሡን ከድህነት አረንቋ ለማውጣት ወያኔ ይህን ለውጥ አመጣ ብሎ ከበሮ

    በመደለቅ የሚሊኒየም ጎል ማሣካት ልባጩ የቀብር ልፈፋ ሆኖ ተገኝቷል

    ታድያ ይህ ጢሻ የከተታቸው ተጋድሎ እውነት ድርቅን ረሀብን ለማጥፋት

    ነው?ወይሥ ኢትዬጵያን ለመበታተን ትግራይን ነፃ ማውጣት የቱ ጋር እንዳሉ

    ፍረዱት ሟቹ መሪ ውሀ ማቆር ብሎ ከፍተኛ ወገን በወባ እንዳለቀ ድብቅ

    አጀንዳቸው ነበር ይህ አልነበረም ገበሬውን 1ለ5 በማደራጀት የወገንን

    ከረሀብ ማላቀቅ ሣይሆን የግንዛቤውን ድክመት ተጠቅመው የኮሮጆ

    ሥልብናን በማግኘት የወያኔን ግዛት ማሥቀጠል ከዚህ በዘለለ ሀቅ ሊሠወር

    አይችልም ከእሥታክሥቲኩ ዳታ ድንጋጤ የህዝብ ቁጥር ማሻቀብ አንፃር

    የወያኔ ጫንቃ ሊሸከመው በማይችለው የኢኮኖሚ ውዥቀት የወገንን

    እንደቅጠል መርገፍ እንደጥሩ አጋጣሚ ይወሥዱታል ይህን ሥናይ

    ለወገናችን ዘለቄታዊ መፍትሄ ለማምጣት የሚታገለው የሀገር ወዳድ

    ንቅናቄዎች በሙሉ ወደ አንድ አላማ ተሠባሥቦ ይህን ለወገን ደንታ

    የሌለውን ወንበዴ ድርጅት ማሥወገድ ይኖርብናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*